ኢራን የአልቃይዳው መሪ ቴህራን ውስጥ አልተገደለም አለች

በኬንያና በታንዛንያ የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባሳለፍነው ነሀሴ ወር ላይ አንድ የታጣቂው አልቃይዳ ቡድን መሪ በዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ ተገድሏል መባሉን ኢራን አስተባብላለች።

ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የአልቃይዳ ምክትል መሪ የሆነውና ቁልፍ ሰው ነው የሚባልለት አብዱላህ አህመድ አብዱላህ በአሜሪካ ጥያቄ መሰረት በቴህራን በሚገኝ አደባባይ በእስራኤል ወታደሮች ተተኩሶበት ተገድሏል።

ኢራን በበኩሏ ምንም አይነት የአልቃይዳ 'አሸባሪዎች' በአገር ውስጥ እንደማይገኙ አስታውቃለች።

አብዱላህ አህመድ በአውሮፓውያኑ 1998 በአፍሪካ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የደረሱ ጥቃቶችን አቅዷል እንዲሁም አቀነባብሯል የሚል ክስ ይቀርብበት ነበር።

በቅጽል ስሙ አቡ ሙሃሙድ አል ማስሪ በመባል የሚታወቀው የአልቃይዳ ምክትል መሪ ከሴት ልጁ ጋር በመንገድ ላይ በመጓዝ ሳለ በሞተር ሳይክል የመጡ ሁለት ቅጥረኛ ነብሰ ገዳዮች ተኩሰው ገድለዋለቸዋል ሲል ኒው ዮርክ ታይምስ አንድ ማንነቱ ያልታወቀ የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊን ዋቢ በማድረግ ዘግቦ ነበር።

በሪፖርቱ መሰረት ኢራን የእብዱላህን ሞት ለመሸፋፈን እንደሞከረች የተገለጸ ሲሆን የኢራን እና የሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የተገደለው ግለሰብ አንድ ሊባኖሳዊ የታሪክ መምህርና እንደሆነና ሴት ልጁም አብራው እንደተገደለች ዘግበዋል።

ነገር ግን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱን ያጣጣለው ሲሆን ''አንዳንድ ጊዜ ኒው ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ በሐሰት ኢራንን ከመሰል ቡድኖች ጋር ለማገናኘት ይሞክራሉ፤ ሐሰተኛ መረጃዎችንም ለመገናኛ ብዙሀን አሳልፈው በመስጠት ቡድኖቹ ለሚፈጽሙት የሽብር ጥቃት ኃላፊነት ላላመውሰድ ይሞክራሉ'' ይላል ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ።

የእስራኤል ቻናል 12 የተባለው ጣቢያ በበኩሉ የደህንነት ኃላፊዎችን በመጥቀስ ''የአብዱላህ ሞት በእስራኤል እና አሜሪካ የጋራ ፍላጎት የተደረገ እንደሆነና የአልቃይዳ ኃላፊው በመላው ዓለም የሚገኙ ይሁዳውያንን ለመግደል በርካታ ሙከራዎችን አድርጓል'' በማለት ዘግቧል።

የአሜሪካ የደህንነት መስሪያቤት ባወጣው ወቅታዊ መረጃ የአልቃይዳ መሪዎች "የቡድኑን ዓለም አቀፍ አደረጃጀት እያጎለበተና በምዕራቡ ዓለም ላይ ጥቃት እንዲፈፅሙ እያበረታታ ነው" ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት በያዝነው ዓመት መግቢያ ላይ ያወጣው የሽብርተኝነት መረጃ "አልቃይዳ በውስጥ ለውስጥ ራሱን እያደራጀ ከምንግዜውም በላይ ጠንካራ እየሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃም እያደገ መጥቷል" ይላል።

የአሜሪካ ደህንነት ኃይል ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት፣ የቢንላደን መገደልና የአይኤስ ቡድን መጠናከር አልቃይዳ አዳዲስ ዘዴዎችን እንዲጠቀም አስገድደውታል።

አልቃይዳም አሁን ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና ደቡብ እስያ ቅርንጫፎች አለው።

ለአልቃይዳ መሪነት ራሳቸውን ያስገበሩት አማፂ ቡድኖች በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥ በስውር የሚንቀሳቀሱ ናቸው።