ኮሮናቫይረስ፡ በሮማንያ ሆስፒታል የደረሰው የእሳት አደጋ የኮሮና ህመምተኞችን ቀጠፈ

የሮማኒያ ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሮማንያ በሚገኝ የኮሮናቫይረስ ህክምና ማዕከል በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ አስር የኮሮናቫይረስ ህመምተኞችን መግደሉን ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ በርካቶችም ክፉኛ ተጎድተዋል ተብሏል።

በሰሜን ምስራቅ ከተማ ፒያትራ ኒያምት ከተማ በሚገኝ የህዝብ ሆስፒታል ውስጥ የኮሮና ፅኑ ህመምተኞች ማቆያ ውስጥም ነው እሳቱ የተነሳው።

ህመምተኞቹን ለማዳን የሞከረው ዶክተር ሰውነቱ በእሳት በመቃጠሉ በሞትና በህይወት መካከል ነው ተብሏል።

የሮማንያ የጤና ሚኒስትር ኔሉ ታታሩ ለአገር ውስጥ ሚዲያ እንደተናገሩት እሳቱ የተነሳው በኤሌክትሪክ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው ብለዋል።

በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ሌሎች የኮሮና ህመምተኞች ኢያሲ ወደምትባል ከተማ ተዛውረው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል።

ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል የተባለው ዶክተር በርካታ የሰውነት ክፍሉ በእሳት የተቃጠለ ሲሆን በወታደራዊ አውሮፕላንም ወደ መዲናዋ ቡካሬስት ለበለጠ ህክምና መወሰዱን የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

"ከዶክተሩ በተጨማሪ ሌሎች የህክምና ባለሙያዎችም በእሳት ቃጠሎው አደጋ ደርሶባቸዋል" ብለዋል የጤና ሚኒስትሩ ኔሉ

በትናንትናው ዕለት ህዳር 5/2013 ዓ.ም የተነሳውን እሳት አደጋ ያስከተለውንም ጉዳትና ሌሎች ሁኔታዎች ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስትሩ ወደ ፒያትራ እንደሚያመሩ ተናግረዋል።

ስምንቱ ህመምተኞች የሞቱት እሳቱ በተነሳበት ሁለተኛ ፎቅ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በሚቀጥለው ክፍል ውስጥ የነበሩ ናቸው።

ሁሉም የኮሮናቫይረስ ህመምተኞች ሲሆኑ በርካቶች ደግሞ የኦክስጅን መተንፈሻ (ቬንቲሌተር) የተገጠመላቸው ናቸው።

እሳቱ በሆስፒታሉ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መዛመት እንደቻለ የገለፁት የጤና ሚኒስትሩ ለዚህም ለህመምተኞች የሚገጠመው ኦክስጅን በከፍተኛ ሁኔታ አስተዋፅኦ አድርገዋል ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተነሳበት እለት ጀምሮ በሮማኒያ 350 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 8 ሺህ 813 ሞቶች ተከስተዋል።

ከሰሞኑ አርብ ዕለት አገሪቷ 9 ሺህ 489 አዲስ ህመምተኞችን የመዘገበች ሲሆን፣ 174 ሞቶችና 1 ሺህ 149 ህመምተኞችም በፅኑ ማዕከል ውስጥ በአንድ ቀን ተከስቷል ተብሏል።