የአሜሪካ የምርጫ ኃላፊዎች የትራምፕን ተጭበርብሯል ክስ ውድቅ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የምርጫ ኃላፊዎች የዘንድሮው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ "በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው" በማለት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ተጭበርብሯል ክስ ውድቅ አድርገዋል።
"በምርጫው ስርአት ውስጥ የተሰረዙ፣ የጠፉ እንዲሁም የተቀየሩ ድምፆች የሉም። በምንም መንገድ ምርጫው ክፍተት አልታየበትም" በማለት የምርጫው ኮሚቴው አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሳቸው የተሰጡ 2.7 ሚሊዮን ድምፆች ያለ ምንም ማስረጃ ጠፍተዋል መባሉን ተከትሎ ነው ኮሚቴው ይህንን የተናገረው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ ላሸነፉት ዲሞክራቱ ጆ ባይደንም ስልጣን ማስረከብ አለባቸው ተብሏል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተደረገውን የአሜሪካ ምርጫ ማን ሊያሸንፍ ይችላል የሚለውን ዋነኞቹ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቀድመው ተንብየው ነበር።
ጆ ባይደን በአሪዞና አሸንፈዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምፃቸውን ወደ 290 ከፍ ያደርገዋል፤ ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ያገኙት የኤሌክቶራል ኮሌጅ አጠቃላይ ውጤት 217 ነው።
አሪዞና ከጎሮጎሳውያኑ 1996 በኋላ ዲሞክራትን ስትመርጥ ለመጀመሪያ ጊዜም ነው ተብሏል።
ውጤቱን በፀጋ አልቀበልም ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ቁልፍ በሚባሉ የአሜሪካ ግዛቶች ክስ ጀምረዋል። ተጨባጭ ማስረጃ የሌላቸው ሰፊ ማጭበርበር ተፈፅሟልም እያሉ ነው።
ከምርጫው ሳንወጣ ዝም ብላ የነበረችው ቻይና ለተመራጮቹ ጆ ባይደንና ካማላ ሃሪስ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክት አስተላልፋለች።
"የአሜሪካውያንን ምርጫ እናከብራለን" በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አስታውቋል።
ሩሲያ በበኩሏ ኦፊሴላዊ ውጤትን እንደምትጠብቅ ተናግራለች።












