የቻይናና አውስትራሊያ ውጥረት፡ አውስትራሊያዊቷ ዜና አንባቢ ቻይና ውስጥ ታገተች

አውስትራሊያዊቷ ዜና አንባቢ ቻይና ውስጥ ታገተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይና እና አውስትራሊያ መካከል ያለው ውጥረት እያየለ መጥቷል።

የቻይና ባለሥልጣናት የአውስትራሊያ ዜግነት ያላትን አንዲት ዜና አንባቢ በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ለቻይና መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲጂቲኤን የምትሠራው ቼንግ ሌይ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሪስ ፔይን እንዳሉት በቁጥጥር ሥር ከዋለችው አውስትራሊያዊት ጋዜጠኛ ጋር የቪድዮ ስልክ ልውውጥ ተደርጓል።

የአውስትራሊያ መንግሥት ቻይና የሚገኙ ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰበው ባለፈው ሐምሌ ነው።

አውስትራሊያና ቻይና በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግንኙነታቸው እየሻከረ መጥቷል። አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ መነሾ በይፋ ይጣራ ማለቷን ተከትሎ ነው ቻይና የተቆጣችው።

ቻይና ለሁለተኛ ጊዜ ከአውስትራሊያ የሚመጡ ወይኖች ላይ ምርመራ ይካሄድ ብላ አዛለች።

ባለፈው ሳምንት የአውስትራሊያ መንግሥት ክልሎች ከውጭ ሃገራት ጋር ያላቸውን ግንኙት ፌዴራል መንግሥቱ ማቋረጥ እንዲችል የሚያዝ ሕግ ለማውጣት እያቀደ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ቼንግ በቁጥጥር ሥር የዋለችው 'የሃገር ድህንነትን አደጋ ላይ በመጣል' በሚል ክስ እንደሆነ የአውስትራሊያው ኤቢሲ ዘግቧል።

ቻይና ውስጥ በዚህ ክስ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው እስከ ስድስት ወራት ድረስ ምርመር ሊደርግለትና ከእሥር ላይወጣ ይችላል።

ነግር ግን ቻይና በጉዳዩ ላይ ገና ማብራሪያ አልሰጠችም።

የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለጋዜጠኛዋ በቁጥጥር ሥር መዋል መረጃ የተሰጠው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።

ነባሯ ዜና አንባቢ አውስትራሊያ የሚኖሩ ሁለት ልጀች አሏት። ኤቢሲ ኒውስ እንደዘገበው ቤተበሶቿና ወዳጅ ዘመዶቿ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ስለ ቼንግ የሰሙት ምንም ነገር የለም።

ቤተሰቦቿ ከአውስትራሊያ መንግሥት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በቅርበት እየተነጋገሩ መሆኑን አሳውቀዋል።

ቼንግ ለሲጂቲኤን ለስምንት ዓመታት ያገለገለች ሲሆን 'ግሎባል ቢዝነስ' በተሰኘው የቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ አቅራቢ ሆና ትሰራለች።

ጋዜጠኛዋ በቻይና መንግሥት ቁጥጥር ሥር ከዋለች ወዲህ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ድረ-ገፅ ላይ ስለሷና ሥራዎቿ የሚያትተው ገፅ መጥፋቱ ተነግሯል።

ቻይና ባለፈው ዓመት ጥር ላይ የቻይናና አውስትራሊያ ዜግነት ያለው ያንግ ሄንገጁን የተባለ ፀሐፊ ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ይጥላል በማለት በቁጥጥር ሥር ማዋሏ አይዘነጋም።