አውስትራሊያ ከቻይና ተመላሾችን ራቅ ወዳለች ደሴት ማጓጓዝ ጀመረች

አውስትራሊያ ዜጎች በዉሃን አየር ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, ABC NEWS/WEIBO

የምስሉ መግለጫ, አውስትራሊያ ዜጎች በዉሃን አየር ማረፊያ

አውስትራሊያ ከቻይና ተመላሽ ዜጎቿን ራቅ ወዳለች ደሴት ማጓጓዝ ጀመረች።

ከቻይናዋ ዉሃን ግዛት የተነሱት የአውስትራሊያ ዜጎች የስደተኞች ማቆያ ቦታ ተደርጋ ወደምትታወቀው ክርሲማስ ደሴት እየተጓጓዙ ነው።

ደሴቷ ከአውስትራሊያ በ2700 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ደሴቷ ጥገኝነት የጠየቁ ስደተኞች ለማቆያ ስፍራነት አገልግሎት ስትሰጥ ነበር።

በአሁኑ ወቅት 4 የሴሪላንካ ዜግነት ያላቸው የቤተሰብ አባላት ብቻ ናቸው በደሴቷ ላይ እየኖሩ የሚገኙት።

ከቻይና እየተጓጓዙ ያሉት አውስትራሊያውያን ለሁለት ሳምንት በደሴቷ ላይ ይቆያሉ።

89 ታዳጊዎችን ጨምሮ ዛሬ ጠዋት 243 ዜጎች እና የአውስትራሊያ ቋሚ ነዋሪዎች ወደ ደሴቷ ለመጓዝ አውሮፕላን መሳፈራቸውን የአውስትራሊያ መንግሥት አስታውቋል።

ከ600 በላይ የአውስትራሊያ ዜጎች ቫይረሱ በተከሰተበት ሁቤይ ግዛት ውስጥ ይኖራሉ። የተቀሩ ዜጎችን ለማጓጓዝ ተጨማሪ በረራዎች እንደሚዘጋጁ መንግሥት አስታውቋል።

የህክምና መስጫ ስፋራዎች ቀደም ብለው በክሪስማስ ደሴት ላይ ተዘጋጅተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AUSTRALIAN GOVERNMENT

የምስሉ መግለጫ, የህክምና መስጫ ስፋራዎች ቀደም ብለው በክሪስማስ ደሴት ላይ ተዘጋጅተዋል።

የአውስትራሊያ መንግሥት ስደተኞች ለማቆያ በሚጠቀምበት ደሴት ላይ ዜጎቹን ለይቶ ለማቆየት መወሰኑ ከበርካቶች ትችት ተሰንዝሮበታል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት በደሴቱ ላይ ያዘጋጀው የህክምና መስጫ ስፍራዎች ደረጃ ዝቅ ያለ ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው።

መንግሥት ግን 24 ዶክተሮችን እና ነርሶችን ማስማራቱን እና ከዚህ ቀደም እያንዳንዱ ከቻይና የሚጓጓዝ ዜጋ ወይም ቋሚ ነዋሪ እንዲከፍል ተጠይቆ የነበረው 1ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር እንዲቀር ተወስኗል ብሏል።

24 ዶክተሮችን እና ነርሶችን ወደ ደሴቷ መሰማራታቸውን መንግሥት አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, AUSTRALIAN GOVERNMENT

የምስሉ መግለጫ, 24 ዶክተሮችን እና ነርሶችን ወደ ደሴቷ መሰማራታቸውን መንግሥት አስታውቋል።

በአውስትራሊያ 12 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ሶስቱ ከቫይረሱ ድነው ከሆስፒታል ወጥተዋል።

እስካሁን በጠቅላላው 360 ሰዎች በላይ በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን፤ ከ17ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል።

አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ጃፓን ዜጎቻቸውን ከቻይና ካስወጡ አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።