አውስትራሊያ፡ ለምን የአሥር ዓመት ታዳጊዎች ይታሰራሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውስትራሊያ ውስጥ በወንጀል ለመጠየቅ ትንሹ እድሜ ዓሥር ነው። ጠበቆች፣ ሐኪሞች እንዲሁም የአቦርጂናል መብት ተሟጋቾች ይህ ሕግ እንዲቀየር ንቅናቄ እያደረጉ ይገኛሉ።
ንቅናቄው በወንጀል ለመጠየቅ ትንሹ እድሜ 14 መሆን አለበት ይላል።
ባለፈው ወር የአገሪቱ ከፍተኛ ሕግ አውጪዎች ጉዳዩን በተመከተ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እስከ ቀጣዩ ዓመት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል የአውስትራሊያ መዲና አስተዳደር (አውስትራሊያን ካፒታል ቴሪቶሪ) ትንሹ በወንጀል መጠየቂያ እድሜ 14 እንዲሆን ወስኗል።
የተቀሩት የአገሪቱ ግዛቶችም ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ የንቅናቄው መሪዎች ይፈልጋሉ።
ትንሹ በወንጀል መጠየቂያ እድሜ ዓሥር መሆኑ ለምን ተቃውሞ አስነሳ?
ከብዙ አገሮች አንጻር አውስትራሊያ ሰዎችን በወንጀል ተጠያቂ የምታደርግበት እድሜ ትንሽ ነው።
የዓሥር ዓመት ልጅ በቁጥጥር ስር ሊውል፣ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ወይም ሊታሰርም ይችላል።
ጀርመንን እንደ ማነጻጸሪያ ብንወስድ አንድ ሰው በወንጀል የሚጠየቅበት ትንሹ እድሜ 14 ነው። ፖርቹጋል ውስጥ 16፣ ላክሰምበርግ ውስጥ ደግሞ 18 ነው።
በሌላ በኩል ኢንግላንድ እና ዌልስ ውስጥ ትንሹ በወንጀል መጠየቂያ እድሜ 10 ነው።
የተባበሩት መንግሥታት አምና ባወጣው መርህ መሠረት ትንሹ በወንጀል መጠየቂያ እድሜ 14 መሆን አለበት።
በአውስትራሊያው ሕግ የበለጠ ተጎጂ የሆኑት ቀደምት ማኅበረሰቦች ናቸው።
አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ እአአ ከ2018 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ከ10 እስከ 13 ዓመት የሆናቸው 600 ልጆች ማረሚያ ቤት ይገኛሉ።
ከነዚህ 65 በመቶው ቀደምት ማኅበረሰቦቹ አቦርጂናሎች እና ቶረስ ስታሪት አይላንደሮች ናቸው።
ከመላው አውስትራሊያ ቀደምት ማኅበረሰቦች 3 በመቶ ብቻ ናቸው።
አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ የቀደምት ማኅበረሰብ ልጆች የመታሰር እድላቸው ከተቀሩት አውስትራሊያውያን 17 በመቶ ይጨምራል።
በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ይህ ቁጥር 43 በመቶ ነው።
‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ ሕዝቡን አነሳስቷል
አውስትራሊያ ሕጓን እንድትቀይር ለዓመታት ሲጠየቅ ነበር።
ሰኔ ላይ ‘ሬይዝ ዘ ኤጅ’ ወይም እድሜውን ከፍ አድርጉት የሚል ንቅናቄ ተጀምሮ ነበር።
በአሜሪካ ለጥቁሮች መብት የሚሟገተው ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ ከአሜሪካ አልፎ በበርካታ አገራት ያሉ ትግሎችን አቀጣጥሏል።
አውስትራሊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ ጥቁሮች ሞትና የዘር መድልዎን የተመለከቱ ተቃውሞዎችም እንደ አዲስ ተነሳስተዋል።
በአገሪቱ የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው በርካታ አውስትራሊያውያን ሕጉ እንዲሻሻል ይፈልጋሉ።
ባለፈው ዓመት የ12 ዓመት አቦርጂናል ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ክንፍ ንግግር ካደረገ በኋላ ዓለም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቷል።
ዱጃን ሆሳን የተባለው ታዳጊ ጄኔቫ ውስጥ “ትልልቅ ሰዎች የ10 ዓመት ታዳጊዎችን ማሰር እንዲያቆሙ እፈልጋለሁ” ሲል ንግግር አድርጓል።
አቦርጂናሎችን ያማከለ የትምህርት ሥርዓት ቢዘረጋ፤ ታዳጊዎችን ከመታሰር እንደሚታደግም ተናግሯል።
ልጆችን ማሰር የወንጀል መጠንን እንደማይቀንስ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በልጅነታቸው የሚታሰሩ ልጆች ለወደፊትም በማረሚያ ቤት ሕይወታቸውን የማሳለፍ እድላቸው ሰፊ እንደሆነም ያክላሉ።
የአውስትራሊያ የሕክምና ባለሙያዎች ከጤና አንጻር ሰዎች በወንጀል የሚጠየቁበት እድሜ ከፍ እንዲል ይፈልጋሉ።
ልጆች ሊታሰሩ ሳይሆን የህክምና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ያመለክታሉ።
ሕግ አውጪዎች እስካሁን ውሳኔ ላይ አልደረሱም
ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን በተመለከተ የደረሰበትን ውሳኔ ባለፈው ወር ያሳውቃል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።
ነገር ግን ውሳኔው የሚገለጽበት ወቅት ተራዝሟል።
ዓቃቤ ሕግ ማርክ ስፒክማን ባለፈው ወር ለጋዜጠኞች “በወንጀል መጠየቂያ ትንሹ እድሜን ከፍ ማድረግ ወይም አለማድረግ የመርህ ጉዳይ ነው። እድሜው ከፍ ካለ ግን አማራጭ መቀመጥ አለበት” ብለዋል።
ልጆች ወንጀል ሲፈጽሙ በምን መንገድ ሁኔታውን መቆጣጠር እንደሚቻል አማራጭ መቀመጥ አለበት ይላሉ ዓቃቤ ሕጉ። የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ልጆችን ከማሰር ውጪ ብዙ አማራጮች አሉ ሲሉ ይከራከራሉ።
ቀደምት ማኅበረሰቦች እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ሕብረተሰቡን ያማከለ ንግግርን ነው።
ከመጠጥና አደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ ችግር የሚገጥማቸው ልጆችና ቤተሰቦቻቸው የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሚናገሩም አሉ።
የመብት ተሟጋቾች ድጋፍ እያገኙ መምጣታቸው ሕጉ እንዲቀየር ያግዛል ብለው ያምናሉ።
የወንጀል ነክ ጉዳዮች መምህሩ ክሪስ ከነን፤ “ዘረኝነትን ለማስወገድና ፍትሕ እንዲሰፍን ሰዎች በወንጀል የሚጠየቁበት እድሜ ከፍ ማለት አለበት” ብለዋል።












