ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለው ከውሃ የሚሰራው ምግብ

የፊንላንድ ተመራማሪዎች ከምንም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለው ምግብ በማምረት ላይ ናቸው።
ምርቱም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከአኩሪአተር ከሚሰሩ ምግቦች ጋር በዋጋ መፎካከር እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ለዚህ ፕሮቲን ምርት ጥቅም ላይ የሚውለው ኤሌክትሪክ ከጸሀይ ብርሀን አልያም ከንፋስ ኃይል የሚገኝ ከሆነ ደግሞ ምንም አይነት ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ወደ ከባቢ አየር ሳይለቁ ማምረት ይቻላል።
የእነዚህ ተመራማሪዎች ስራ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ የሚሆን ከሆነ ከግብርና ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ አማራጭ እንደሚሆን ይታሰባል።
በአሁኑ ሰዓት ተመራማሪዎቹ የምርምር ስራቸውን ለማከናወን 5.5 ሚሊየን ዩሮ የሚደርስ ገንዘብ ፈሰስ ለማድረግ የተስማሙ ባለሃበቶች ያሉ ሲሆን በኤሌክትሪክ ዋጋ ላይ ተመስርተው ደግሞ ከአኩሪ አተር የሚሰሩ ምግቦችን የመተካት ዓላማ ሰንቀዋል።
ከምንም ማለት በሚቻል መልኩ የሚሰራው የፕሮቲን ዱቄት ምንም አይነት ጣእም የሌለው ሲሆን ተመራማሪዎቹም ቢሆኑ ሆነ ብለን ነው ምላስ ላይ ሊስተዋል የሚችል ጣእም እንዳይኖረው ያደረግነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በትልልቅ የእርሻ ማሳዎች ውስጥ የሚመረቱ እንደ አኩሪ አተር ያሉ ተክሎችን ፍሬዎች የሚመገቡ ከብቶችም ቢሆኑ ይህንን የፕሮቲን ዱቄት መኗቸው ቢያደርጉ ላቅ ያለ ውጤት እንደሚገኝበት ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።
ምናልባት ይህ ፕሮቲን በከፍተኛ ደረጃ ተመርቶ የዓለማችንን የምግብ ፍላጎት የመቅረፍ እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ዓለማችን ወዴት እየሄደች እንደሆነ ማሳያ ሊሆን የሚችል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ሙሉ በሙሉ በቤተ ሙከራዎች ውስጥ ምንም አይነት አፈርም ሆነ ተፈጥሯዊ ሂደቶችን ያልተከተሉ የምግብ ምርቶች የወደፊቱ ተስፋችን ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሄ ምርት ጠቋሚ ነው ብለዋል።
እ.አ.አ. በ 1960ዎቹ ወደ ጠፈር ለሚጓዙ ባለሙያዎች ተብሎ ምርምሩ የተጀመረው ይህ የምግብ አማራጭ በ 2022 ሙሉ በሙሉ ለምግብነት ብዙ ሆኖ ለገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
ነገሮች ሁሉ በታሰበላቸው የሚሄዱ ከሆነና የምርቱ ፍላጎት ከፍተኛ ከሆነ ደግሞ በ 2025 ትልቅ ማቀነባበሪያ ለመክፈት ታስቧል።
'ሶሌይን' የሚል ስያሜ የተሰጠው የፕሮቲን ዱቄት የማምረት ሂደት ኤሌክትሮሊሲስ የሚባል ሂደትን በመከተል ውሃን ለሁለት በመክፈል ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ሄይድሮጂኑ ከውሃው ተለይቶ ይወጣል። በመቀጠልም ሃይድሮጂኑን፣ ከአየር የሚገኘውን ካርቦን ዳይኦክሳይድና ሌሎች ንጥረ ነገሮች አፈር ውስጥ የሚኖሩት ባክቴሪያዎች እንዲመገቡት ይደረጋል። ታዲያ መጨረሻ ላይ ባክቴሪያዎቹ የፕሮቲን ዱቄቱን ያመርታሉ።
ይህን ምርት ለማምረት ከፍተኛ ግልጋሎት የሚሰጠው ኤሌክትሪክ ደግሞ ዋጋው በቀነሰና ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ መገኘት ሲጀምር የፕሮቲን ዱቄቱ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ።
ግብርና እና አሳ ማጥመድ ዓለማችንን በከፍተኛ ሁኔታ እየበዘበዙ ነው ብለው የሚያምኑት ተመራማሪዎቹ ይህ ምርት ብዙ ነገሮችን ቀላል እንደሚያደርግ ተስፋ ሰንቀዋል።
''የምግብ ምርት ዓለማችንን በአስፈሪ ሁኔታ እያራቆታት ነው። በፍጥት እየተቀየረ የመጣው የአየር ጸባይም ቢሆን ለግብርና ተብሎ ከሚጨፈጨፈው ደን ጋር በቀጥታ ይገናኛል'' ብሏል ከተመራማሪዎቹ አንዱ።
አክሎም ''ምድራችን ወደፊት ለሰዎች መኖሪያነት ምቹ ሆና ትቀጥላለች ብዬ አላስብም። ይህን መሰል ግኝቶች ግን ተስፋ ይሰጡኛል'' ብሏል።












