ተጠቃሚዎች የማይከፍሉበት ቁርስ ቤት

ቲሊያ አዲና ልጇ ኤታን በሳምንት ሶስት ቀን ቁርስ ቤቱን ይጎበኛሉ

የፎቶው ባለመብት, Phil Coomes

የምስሉ መግለጫ, ቲሊያ አዲና ልጇ ኤታን በሳምንት ሶስት ቀን ቁርስ ቤቱን ይጎበኛሉ

በሰሜን ምስራቅ ለንደን በሚገኘው ካፌ ተጠቃሚዎች በልተውና ጠጥተው ሳይከፍሉ ውልቅ የሚሉበት ነው።

ካፌው በበጎ አድራጎት ድርጅቶች 'ደስ ያላችሁን፣ የምትችሉትን ክፈሉ ባትከፍሉም ችግር የለም' በሚል ብሂል በመላ እንግሊዝ ከተከፈቱ ካፌዎች አንዱ ነው።

ዳቦ ቶስተር ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Phil Coomes

በዚህ ካፌ እንቁላል፣ ዳቦ፣ ፖሬጅ ከሻይ ከቡና ጋር ለተጠቃሚዎች ይቀርባል። የብርቱካን ጭማቂም አይጠፋም። ወዲያ ወዲህ ብለው አረፍ ለማለትም ይሁን ጓደኞችን ቀጥሮ ሻይ ቡና ለማለት የነፃው ካፌ ምርጥ ቦታ እንደሆነ ተጠቃሚዎቹ ይናገራሉ። የነፃው ቁርስ ቤት ድባብ ደስ የሚልና አውዳመት አውዳመት የሚል ነው ያሉም አልጠፉም።

የኢንሹራንስ ባለሙያ የሆነው ጋይ ካፌው በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን እኩል የሚያደርግ ነው ይላል። ምክንያቱም ገንዘብ ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ማንም ወደ ካፌው ሄዶ ሻይ ቡና እያለ መጫወት ይችላልና።

የካፌው ደንበኛ የሆኑት ሺላና የስድስት ዓመት ህፃን ልጇ በሳምንት ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ጎራ ይላሉ።

"አንዳንዴ የምንመጣው ቀለል ያለ ቁርስ ለመብላት ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ገንዘብ ሲያጥረን ነው። ደግሞ እኔም ልጄም እዚህ ጓደኞች አፍርተናል" ትላለች ሺላ።

ካፌውን ለየት የሚያደርገው ተጠቃሚዎች በልተው ጠጥተው ሳይከፍሉ መውጣት የሚችሉበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ራሱን የሚያስተናግድበት መሆኑም ነው።

ከነፃው ካፌ ደጃፍ

የፎቶው ባለመብት, Phil Coomes

የካፌው ተጠቃሚዎች ወላጆች ፣ ህፃናት፣ አዛውንት፣ ባለሙያዎች፣ ጎልማሶችና አካል ጉዳተኞችና መሰሎች ናቸው። የካፍቴሪያውን የጋራ ትልልቅ ጠረጴዛዎች ተጋርተው ሰዎች ስለ ተለያዩ ነገሮች እንዲያወሩ የሚጋብዝ ነው የካፌው ሁኔታ።

የዚህ አይነት ካፌዎች የሚከፈቱት የዕለት ምግባቸውን ማግኘት የሚቸግራቸው ሰዎች ማእድ እንዲቋደሱ ነው። ብዙዎቹ ካፌዎች የሚጠቀሙት ሱፐር ማርኬቶች፣ ሬስቶራንቶችና ሌሎች የለገሷቸውን ምግቦች ነው።