እስራኤል በጋዛ የምትወስደውን እርምጃ አጠናክራ ቀጠለች

የእስራኤል ጦር ታንኮችን ጭምር ወደ ጋዛ ድንበር አስጠግቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ታንኮችን ጭምር ወደ ጋዛ ድንበር አስጠግቷል

አምስተኛ ቀኑን በያዘው የፍልስጤምና እስራኤል ፍጥጫ ፍልስጤም ታጣቂዎች ሮኬቶችን መተኮስ መቀጠላቸውን ተከትሎ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንደሚለው ጥቃቱ አሁንም ድረስ እየተካሄደ ሲሆን ወታደሮች በአየርና በእግረኞች በመታገዝ ጥቃቱን እየፈጸሙ ነው። ነገር ግን ወታደሮች ወደ ጋዛ አለመግባታቸው ተለግልጿል።

በጋዛ ሮኬቶች፣ ተዋጊ ጀቶችና ሄሊኮፕተሮች ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበር የቢቢሲ ዘጋቢ ተመልክቷል።

እስራኤል እና ፍልስጤማውያን ሰኞ ዕለት ወደለየለት ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ እስካሁን ከ100 በላይ ሰዎች ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ሲሆን እስራኤል ውስጥ ደግሞ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

በሌላ በኩል እስራኤል ውስጥ የሚገኙ አይሁዶችና አረቦችም ግጭት ውስጥ ገብተዋል። የእስራኤል ባለስልጣናት ነገሮች በዚህ መልኩ ከቀጠሉ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤኒ ጋንትዝ በበኩላቸው በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር እየተሰማራ እንደሆነና እስካሁንም ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ደግሞ መከላከያ ኃይሉ በጋዛ ታጣቂዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ አስፈላጊ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ እንዲቀጥል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በመግለጫውም ጋዛን የሚመራው ኢስላማዊው ቡድን ሃማስ ላደረሰው ጉዳት ከባድ ዋጋ ይከፍላል ብለዋል።

የእስራኤል ጦር ጋዛ ድንበር አቅራቢያ ሐሙስ ዕለት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር ጋዛ ድንበር አቅራቢያ ሐሙስ ዕለት

የሃማስ ቃል አቀባይ የሆኑት ግለሰብ በበኩላቸው ቡድኑ የምድር ጥቃት ለመፈጸም የሚወስን ከሆነ የእስራኤልን ወታደሮች መራር ትምህርት እንሰጣቸዋለን ሲሉ ተደምጠዋል።

የእስራኤል መንግሥት በእስራኤላዊያን እና አረቦች መካከል ከፍተኛ አመፅ መነሳቱን ተከትሎ በሎድ ከተማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።

በሎድ ከተማ በተነሳው አመፅ መኪኖች ጋይተዋል እንዲሁም 12 ሰዎች ተጎድተዋል። የከተማው ከንቲባም ስማቸው ከእርስ በእርስ ጦርነት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል።

ማክሰኞ ምሽት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሎድ ከተማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁን ይፋ አድርገዋል። የእስራኤል የድንበር ጠባቂ ፖሊሶችም ከዌስት ባንክ እንዲመጡ ተደርጓል።

በቴል አቪቭ አቅራቢያ ባለችው የሎድ ከተማ የሚኖሩ እስራኤላዊያን አረቦች የጀመሩት የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ረብሻ ተቀይሮ ፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወሩ ፖሊስ ከፍተኛ ድምፅ በሚያሰሙ ፍንዳታዎች ምላሽ ሰጥቷል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በሎድ ከተማ በርካታ የንግድ ሱቆች እና ምኩራቦች በእሳት ተያይዘዋል። ሮይተርስ እንደዘገበው አንድ አረብ እየነዳ በነበረበት ወቅት አይሁዶች መኪናውን በድንጋይ አጥቅተዋል።

የፍልስጤም ተዋጊዎች በበኩላቸው እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ባካሄደችው የአየር ጥቃት አንድ ህንፃ ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን ወደ ቴል አቪቭ ተኩሰናል ብለዋል።

የዚህ ሳምንቱ ግጭቱ ከአውሮፓውያኑ 2014 በኋላ ከባዱ የተባለ ሲሆን በርካታ ንጹሀን ዜጎችና መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገዱ ይገኛሉ።

የእስራኤል መከላከያ እስከ 7 ሺ የሚደርሱ ተጠባባቂ ወታደሮችን የጠራ ሲሆን ወደ ጋዛ ድንበር ደግሞ ወታደሮችን እና ታንኮችን ማስጠጋት ጀምሯል።

ግጭቱ አምስተኛ ቀኑን መያዙን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሁለቱም አካላት ግጭቱን ለማበረድ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።