ደቡብ አፍሪካዊቷ እናት በአንድ ጊዜ 10 ልጆችን ተገላገለች

የፎቶው ባለመብት, AFRICAN NEWS AGENCY (ANA)
ደቡብ አፍሪካዊቷ እናት በአንድ ጊዜ አስር ልጆችን በመውለድ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰንን ያዘች።
ጎሲያሜ ታማራ ሲቶሌ የተባለችው እናት ባለቤት እንደተናገረው መጀመሪያ ላይ ስምንት ልጆችን እንደጸነሰች በተደረገላት ምርመራ በታወቀ ጊዜ በጣም ተደንቆ እንደነበር ገልጿል።
"አሁን ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶችን ተገላግላለች። በጣም ደስ ብሎኛል። በጣም ስሜታዊ ሆኛለሁ ብዙ መናገር አልችልም" ሲል ባልየው ቴቦሆ ተናግሯል።
የ37 ዓመቷ እናት ሲቶሌ ቀደም ሲል መንታ ልጆችን የወለደች ሲሆን አሁን ስድስት ዓመታቸው ነው።
አስሩ ልጆች ሰኞ ዕለት ምሽት ፕሪቶሪያ ውስጥ የተወለዱት በ29 ሳምንታቸው በቀዶ ህክምና ሲሆን እናትየው በመልካም ጤንነት ላይ ትገኛለች።
የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናትም ሲቶሌ አሰር ልጆችን እንደተገላገለች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የተለያዩ ክብረ ወሰኖችን የሚመዘግበው ጊነስ ወርልድ ሪከርድም የአስሩ ልጆች መወለድን ከመመዝገቡ በፊት ማጣራትን እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ በርካታ ልጆችን በመውለድ የዓለምን ክብረ ወሰን የያዘችው እናት አሜሪካዊት ስትሆን በ2009 (እአአ) ስምንት ልጆችን በአንድ ጊዜ ተገልግላለች።
ባለፈው የግንቦት ወር የ25 ዓመቷ የማላዊ ዜጋ የሆነችው ሃሊማ ሲሴ ዘጠኝ ልጆችን ወልዳ ሞሮኮ ውስጥ በሚገኝ ክሊኒክ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ተነግሮ ነበር።
በርካታ ልጆች የተጸነሱባቸው አብዛኞቹ እርግዝናዎች ከጊዜያቸው በፊት ወሊድ እንደሚያጋጥማቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከሦስት በላይ የሆኑ ልጆችን መውለድ ብዙም የተለመደ ባይሆንም በአብዛኛው የሚከሰቱት የህክምና ድጋፍ ሲታከልባቸው ነው።
አስር ልጆች የተወለዱበት ይህ ክስተት ግን ምንም አይነት የህክምና ተሳትፎ ሳይኖርበት ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ጽንሶቹ እንተፈጠሩ ጥንዶቹ ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በፊት እናት ሲቶሌ ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው "በመጀመሪያ አካባቢ እርግዝናዋ ከባድ ስለነበር" በጤናማ ሁኔታ መውለድ እንድትችል ትጸልይ እንደነበረና ምን ሊከሰት እንደሚችል በመጨነቅ በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ማሳለፏን ተናግረዋለች።
"ህጻናቱ እንዴት ብለው በማህጸን ውስጥ ሊቆዩ ይችላሉ? በህይወት ሊወለዱ ይችላሉ?" ስትል እራሷን ስትጠይቅ የቆየችው እናት፤ ሐኪሞች ግን ማህጸን በመለጠጥ አስሩንም ልጆች የመያዝ አቅም እንዳለው በመግለጽ ምንም እንደማይፈጠር ሲነግሯት ቆይተዋል።
ስምንት ልጆችን እንዳረገዘች በታወቀበት ጊዜ እናት ሲቶሌ የእግር ህመም ያሰቃያት የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ ሁለቱ ልጆች በተገቢው ቦታ ላይ እንዳልነበሩ ሐኪሞች ገልጸው ነበር።
"ሐኪሞቹ የተከሰተውን ችግር ካስተካከሉ በኋላ ጤናማ ነበርኩ። ልጆቼን ወልጄ ለማቀፍ በጣም ጓጉቻለሁ" በማለት ለአንድ ጋዜጣ ቀደም ሲል ተናግራ ነበር።
ባለቤቷ በጣም ደስተኛ እንደሆነና በፈጣሪ ከተመረጡ ሰዎች መካከል የሆነ ያህል እንደተሰማውና ክስተቱንም "እጅጉን የተደነቅኩበት ተዓምር ነው" ብሎታል።












