የኒውዚላንዷ ከተማ ኦክላንድ የአለማችን ምቹ መኖሪያ ተባለች

የኦክላንድ ከተማ

የኦሳካ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኦሳካ ከተማ

የኒውዚላንዷ ከተማ ኦክላንድ የአለማችን ምቹ የመኖሪያ ከተማ ተባለች።

በየአመቱ የሚደረገው የከተሞች ደረጃ አመዳደብ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ነገሮች ተቀይሮበታል ተብሏል።

ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት 140 ከተሞች ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የትኞቹ ምቹ የትኞቹስ አስቸጋሪ በሚል ዝርዝሮቹን አስቀምጧል።

ለከተሞቹ ምደባ እንደ መስፈርት የተቀመጡትም መረጋጋት፣ መስረተ ልማት፣ ትምህርትና የጤና ተቋማት አቅርቦት ናቸው።

ምንም እንኳን እነዚህ መስፈርቶች ከዚህ ቀደምም ይሰራባቸው የነበሩ ቢሆንም በዘንድሮው ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንድ ቁልፍ ምክንያት ተደርጎ ተቀምጧል።

ይህም ማለት በወረርሽኙ ክፉኛ የተመቱት የአውሮፓ ከተሞች ደረጃቸው ሲያሽቆለቁል አውስትራሊያ፣ ጃፓንና ኒውዚላንድ የመሳሰሉት አገራት በደረጃ ከፍ የማለት ሁኔታ አሳይተዋል።

እነዚህ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአፋጣኝ ለመግታት ከጅምሩ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የእንቅስቃሴ ገደብ የለባቸውም።

የአውሮፓ ህብረት አገራት ክትባት የጀመሩት ዘግየት ብለው ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ከደረጃው ዝቅ ብለዋል ተብሏል።

ኦክላንድ በምቹ ከተማነት በአንደኛ ደረጃ ስትቀመጥ፣ በሁለተኛ ደረጃ የጃፓኗ ኦሳካ፣ በሶስተኛ ደረጃ የኦስትራሊያ አዴላይዴ ይከተላሉ።

የኦሳካ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኦሳካ ከተማ
አዴላይዴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአዴላይዴ ከተማ

"ኦክላንድ በአንደኛነት ደረጃ የተቀመጠችው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በአመርቂ ሁኔታ በመግታት የከተሜው ነዋሪ ኑሮውን በተመቸ ሁኔታ እንዲኖር በማድረግ ነው" ብሏል ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት

በዚህ አመት የአውሮፓ ከተሞች ደረጃ ያሽቆለቆለ ሲሆን ለበርካታ አመት አመት አንደኛ የነበረችው የኦስትሪያዋ ቪየና በዘንድሮው በ12ኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

የጀርመኗ ሃምቡርግ ደግሞ በ47 ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን በርካታዎቹ የጀርመንና የፈረንሳይ ከተሞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት የጤና ስርዓታቸው ተዛብቷል በዚህም ምክንያት ደረጃቸውም በከፍተኛ ሁኔታ ሊወርድ ችሏል።

በተጨማሪም አገራቱ የኮሮናቫይረስን ለመግታት የጣሏቸው መመሪያዎች እንቅስቃሴን በመገደብ የከተሜውን የመኖር ሁኔታ ምቾት አሳጥተውታል ብሏል የዳሰሳ ጥናቱ።

ምንም እንኳን ከላይ ያለው ደረጃ ቢቀያየርም ለመኖር አስቸጋሪ ተብለው በአንደኝነት የተቀመጠችው የሶሪያዋ ደማስቆ ናት።

በሶሪያ ባለው የርስበርስ ጦርነት ምክንያት ህይወት በደማስቆ ፈታኝ አድርጎታል።

ሌሎቹ አስቸጋሪ ተብለው የተመደቡት አገራት በግጭትና ሌሎች ምክንያቶች የጤና ስርዓታቸውና መሰረተ ልማታቸው የተቃወሱ ናቸው ተብሏል።

አስሩ የ2021 ምቹ ከተሞች

  • ኦክላንድ፣ ኒወዚላንድ
  • ኦሳካ፣ ጃፓን
  • አዴላይዴ፣ አውስትራሊያ
  • ዌሊንግተን፣ ኒውዚላንድ
  • ቶክዮ፣ ጃፓን
  • ፔርዝ፣ አውስትራሊያ
  • ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ
  • ጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ
  • ሜልቦርን፣ አውስትራሊያ
  • ብሪስባን፣ አውስትራሊያ
line

አስሩ የ2021 አስቸጋሪ ከተሞች

  • ደማስቆ፣ ሶሪያ
  • ሌጎስ፣ ናይጄሪያ
  • ፖርት ሞረስቢ፣ ፒኤንጅ
  • ዳካ፣ ባንግላዴሽ
  • አልጀርስ፣ አልጀሪያ
  • ትሪፖሊ፣ ሊቢያ
  • ካራቺ፣ ፖኪስታን
  • ሃራሬ፣ ዚምባብዌ
  • ዱላ፣ ካሜሮን
  • ካራካስ፣ቬንዙዌላ