ስልጣን በውርስ? ልጆቻቸውን ለስልጣን ያጩት የአፍሪካ መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Vincent Fournier/Jeune Afrique-REA
የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሱ ንጌሶ ልጃቸውን ዴኒስ ክሪስቴልን ሚኒስትር አድርገው ሾሙ። ይህንን ሹመት ሚዲያዎች እንዲሁ በቀላሉ አላዩትም። ፕሬዚዳንቱ ልጃቸውን ሊተኩ በዝግጅት ላይ ናቸው በማለትም ነው ሪፖርት ያደረጉት።
ስልጣን ዘላለማዊ እንዳለመሆኑ መጠን እንዲህ አይነት መተካካት ሊከሰት ይችላል። ለአርባ አንድ ዓመታት አገሪቷን የገዙት የ77 ዓመቱ ፕሬዚዳንት በቀጣዮቹ ዓመታትም እንዲያስተዳድሩ በመጋቢት ወር ምርጫ አሸንፌያለሁ ብለዋል።
በቀጣዮቹ ዓመታትም ስልጣናቸውን አሳልፈው ለመስጠት ምንም አይነት ፍንጭ ባያሳዩም የአሁኑ የስልጣናቸው ወቅት ሲያልቅ ልጃቸውን ለመተካት እንደሚያስቡ አንዳንድ ፍንጮች እየተሰሙ ነው።
የልጃቸው ዴኒስ ክሪስቴል በኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚዳንት መሆን አዲስ ነገር አይሆንም፤ በተለይም በማዕከላዊ አፍሪካ አካባቢ እንደሚታየው የልጆች ስልጣን መውረስ ተመሳሳይ እንጂ።
በጎረቤት አገር ጋቦን የወቅቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ ኦንዲምባ አገሪቷን ከአውሮፓውያኑ 1967 አስከ 2009 የመሯት የኦማር ቦንጎ ልጅ ናቸው።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2001 የተገደሉት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የነበሩትን ላውረንት ዴዜሪ ካቢላን በመተካት ልጃቸው ጆሴፍ ካቢላ ለ17 ዓመታት በስልጣን ቆይተዋል።
የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቲዎዲሮ ኦቢያንግ ወደ ስልጣን የመጡት ጨቋኙ አጎታቸውን ፍራንሲስኮ ማሺያስ ንጉዌማን ከስልጣን በማስወገድ ነበር። አጎትየውም በ1979 ወደ ስልጣን የመጡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ልጃቸው እሳቸውን እንዲተካቸው ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው ሾመውታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከአማፂያን ጋር ሲዋጉ ቆስለው ባለፈው ወር ህይወታቸው ያለፈው የቻዱን ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢን በመተካት ልጃቸው ማህማት የሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት መሪ ሆኗል። ልጃቸው የጦር ጄኔራል ነው።
በካሜሮንም እንዲሁ የስልጣን ሽግግር እንዲመጣ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። እንቅስቃሴው በማን እንደተጀመረ ግልፅ ባይሆንም የ88 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ፓውል ቢያ ልጃቸውን ፍራንክ ቢያን እንዲተኩት ዘመቻም ተጀምሯል። ፕሬዚዳንቱ ለሰባት ዓመት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የተመረጡ ቢሆንም ግማሹንም ጊዜ ገና አላጠነቀቁም።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከፖለቲካ ራሱን አግልሎ በግል ቢዝነስ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ፍራንክ ከዚህ ዘመቻ ጀርባ እጁ በፍፁም እንደሌለበት የቅርብ ሰዎቹ ይናገራሉ። ነገር ግን ዘመቻውን የመቃወም፣ የማስተባበልም ሆነ አባቱን በስልጣን የመተካት ፍላጎትንም በጭራሽ አላሳየም።
ስልጣን መወራረስ አዲስ ነገር አይደለም። በማዕከላዊ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም የቡሽና የኬኔዲ ቤተሰቦችን እንመልከት።
በቅርቡም በኡጋንዳ የወቅቱን ፕሬዚዳንት ዩዌሩ ሙሴቪኒ ልጃቸው ሙሆዚ ካይኔሩግባ በመጪው 2026 በፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ተወዳዳሪ እንዲሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች ተከፍተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ነገር ግን ስልጣን የመወራረስ ጉዳይ በምዕራብ አፍሪካ በተለይ የተንሰራፋ ይመስላል። እነዚህ አካባቢዎች በነዳጅ የታደሉ ከመሆናቸው አንፃር የፖለቲካው ትስስር፣ የፔትሮሊየም ምጣኔ ሀብትና የኢምፓየር ግንባታ የተቆራኙ ናቸው።
አመራሮቹ የነዳጁንም ምንጭ መቆጣጠር ስለሚያስችላቸው በውስጣቸውም መቆራቆዝ በርካታ ጊዜ ይፈጠራል።
ለምሳሉ ያህል በኦቢያንግ ቤተሰቦች መካከል ግጭቶች አንዳሉ ይሰማል። አንዳንድ የቤተሰብ አባላት የፕሬዚዳንቱ ልጅና የነዳጅ ሚኒስትሩ ገብርኤል ምቤጋ ኦቢያንግ ሊማ አማራጭ ፕሬዚዳንት እንዲሆን ይፈልጋሉ።
ጋቦን፡ የቤተሰብ ቁርሾ
በአውሮፓውያኑ 2016 በጋቦን ምርጫ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የቀድሞው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጂን ፒንግ ፕሬዚዳንት አሊ ቦንጎን ያፋጠጠ ነበር።
እነዚህ ፖለቲከኞች የጋብቻ ዝምድና አላቸው። የፕሬዚዳንት አሊ ቦንጎ እህት ፓስካሊን የጂን ፒንግ የቀድሞ ባለቤት ናት፤ ይህም ማለት ፕሬዚዳንት አሉ የጂን ፒንግ ሁለት ልጆች አጎት ናቸው።
ነገር ግን ጂን ፒንግ በዋነኝነት የፖለቲካ አጀንዳቸውን ወደፊት በማምጣት በአገሪቱ የለውጥና እውነተኛ ዲሞክራሲ መሪ ነኝ በማለት ነበር በተቃዋሚ መሪነት በምርጫ የተወዳደሩት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በዚያን ወቅት በነበረው ምርጫ የተሸነፉት ጂን ፒንግ ከአምስት ዓመታት በኋላም መሸነፋቸውን አይቀበሉትም።
በወቅቱ በርካቶች መራራ ያሉት የምርጫ ውድድርና የተአማኒነት ጥያቄ ያነሱበት ይህ ምርጫ በመጨረሻም ፕሬዚዳንት አሊን አሸናፊ አድርጓቸዋል።
ፕሬዚዳንት አሊ ቦንጎ ወደኋላ እየተመለከቱ አይደለም። በአሁኑ ወቅት ልጃቸውን ኑረዲን ቦንጎ ቫለንቲንን የፕሬዚዳንት ጉዳዮች ዋነኛ አስተባባሪ አድርገው በአውሮፓውያኑ 2019 ሾመውታል።
ልጃቸውን ከመሾማቸው ከዓመት በፊት ፕሬዚዳንት አሊ ቦንጎ ስትሮክ ታመው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለህክምና አቅንተው ነበር። በዚያን ወቅት የአገሪቱ ኤታማዦር ሹም ብሪስ ላክሩቼ አሊሃንጋ ፕሬዚዳንቱን ተክተው ሥራቸውን ሲያከናውኑ ነበር።
ፕሬዚዳንቱም ከህመማቸው አገግመው ተመለሱ ኤታማዦር ሹሙን ከስልጣናቸው አነሷቸው፤ በኋላም ከሥራ ተባረሩ በሙስና ወንጀልም በቁጥጥር ስር ዋሉ። ኤታማዦር ሹሙ ግን ይህንን ይክዳሉ።
በአሁኑ ወቅት ልጃቸው ኑረዲን በዚህ ቁልፍ በሚባል ቦታ ላይ ተቀምጧል። አባቱንም በየቀኑ ያገኛል። የፕሬዚዳንቱንም ፍላጎቶች ለማስፈፀምና በጉዳዮች ላይ ለመወሰን ስልጣን አለው።
በተለይም የፕሬዚዳንት አሊ የጤና ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው በሚባልበት በአሁኑ ወቅት ኑረዲን በስልጣን ሊተካቸው ይችላል የሚሉ ጉዳዮች ጎልተው እየወጡ ነው።
ኑረዲን በዩናይትድ ኪንግደም ስመ ጥር በሆነው ኤተን ኮሌጅ ነው የተማረው፤ ወጣትነቱ እንዲሁም ያለው የዘመናዊነት ሁኔታው የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Steve Jordan/AFP/Getty Images
የፈረንሳይ የሙስና ምርመራ
ወደ ቻድ ስንመለስ ደግሞ ለሦስት አስርት ዓመታት አገሪቱን የመሯት ኢድሪስ ዴቢ የሞቱት ከአንድ ወር በፊት ነው። በእሳቸው ቦታ የተተካውን ልጃቸውን ማሃማት ከፍተኛ ተግዳሮቶች ተጋርጠውበታል።
በሽግግሩ ምክር ቤት ውስጥ ያሉትን ወታደራዊ አጋሮቹ ጋር በመሆን በአገሪቱ የቆየን ወታደራዊ ልማድ ለማስቀጠል የጎሳዎች ድጋፍ ማግኘት አለበት።
በሌላ በኩልም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ በኩል ለፖለቲካ ውይይቶችና ትርጉም ያለው ዲሞክራሲ እንዲመጣ ጥረት እንዲያደርግ ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኢኳቶሪያል ጊኒ ደግሞ ሌላኛው ስጋትና ሁኔታዎችን የተወሳሰበ ያደረገው ፈረንሳይ በአመራሮቹ ላይ በማነጣጠሯ ነው። የአገሪቷ መሪዎች ከሙስና በተገኘ ገንዘብ ንብረቶች በፈረንሳይ ገዝተዋል በሚልም የሙስና ምርመራ ጀምሬያለሁ ብላለች።
የቦንጎም ሆነ የንጌሶ ቤተሰቦች በዚህ ኢላማ ሆነዋል። 13 የሚሆኑ የነዚህ ቤተሰብ አባላት እንዲሁም በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ ቤት ጠበቃ ሆኖ ይሰራ የነበረና በርካታ የፈረንሳይ ዜጎች የወንጀል ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2015 የፈረንሳይ ዳኛ በፓሪስ የሚገኙ ሁለት ንብረቶች በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የነዚህ ንብረት ትክክለኛ ባለቤቶችም የሳሱ ንጌሶ የወንድም ልጅ ዊልፍሪድ ንጌሶ ናቸው በሚል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቅንጡ የሚባሉ 15 መኪኖችም እንዲሁ እንዲያዙ ተወስኗል። ዊልፍሪድም ይፋዊ የሆነ ምርመራ ተከፍቶበት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአውሮፓውያኑ 2016 ሳሱ ንጌሶ የተከፈተባቸው ምርመራ ውድቅ እንዲሆን የሞከሩ ሲሆን ይህንን ጉዳይም ቃል አቀባያቸው ፕሬዚዳንቱን ለማሳጣት የሚደረግ ትልቅ ማጭበርበር ነው በማለት ወርፈዋቸዋል።
የፈረንሳይ ዳኞች ግን በዚህ ፍንክች አላሉም። በአውሮፓውያኑ 2017 የፕሬዚዳንቱ ልጅ ጁሊየንና ባለቤቷ ጋይ ጆንሰን፣ ሌላ የወንድም ልጅ ኤድጋር፣ የባለቤታቸው እህት ካትሪን ኢግናንጋ ምርመራ ተጀምሮባቸዋል ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2008-09 አጠራጣሪ በተባለው 22.4 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ዝውውርም መሪዎቹ ተወንጅለዋል።
ኢኳቶሪያል ጊኒና ቅንጡ መኪኖቿ
የኢኳቶሪያል ጊኒ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ልጅ ሌላኛው ቲዎዶሮ በፓሪስ የሚገኘው ቅንጡ ቤቱ በአውሮፓውያኑ 2012 በፖሊስ ተከበበ። ሁለት ቡጋቲ ቬይሮንስና ሮልስ ሮይስ ፓንቶም የተባሉት መኪኖቹም ተያዙ።
መኪኖቹን በመያዝ ብቻ አልበቃም ቲዎዶሮ ራሱ 30 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንዲከፍሉ ታዘዘ።
በዚህ የተበሳጨው መንግሥት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ወሰደው። መከራከሪያውም ፎች ማንሽን የተባለው በፈረንሳይ የሚገኘው ቤት 107 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያወጣና የአገሪቱም ኤምባሲ እንደሆነና ከምንም ነገር የሚጠብቃቸው የዲፕሎማሲያዊ ጥበቃ አለ በሚልም ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ነገር ግን ባለፈው ታኅሣሥ ፍርድ ቤቱ ይህንን መከራከሪያ ውድቅ አድርጎታል። የፈረንሳይ ፓርላማ በበኩሉ እነዚህ የተያዙ ንብረቶች በአገሪቱ ለሚገኙ መሰረተ ልማቶች ሊውሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውሳኔ እያረቀቀ ነው።
እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ግን በደንብ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
በስዊዘርላንድ፣ ጁኔቫ የሚገኙ ባለስልጣናትም እንዲሁ በቴዎዶርና በሁለት ግለሰቦች ላይ ገንዘብ በማዘዋወር፣ የሕዝብ ሃብትን ያላግባቡ በመጠቀም በሚል ክስ ከፍተው ከሁለት ዓመት በፊትም ነው ጉዳዩ የተቋጨው። በዚህም መሰረት 25 ቅንጡ መኪናዎች አንዲሸጡ ታዘዘ ገንዘቡም ለእርዳታና ለልማት ድርጅቶች እንዲውል ተወሰነ።
ከተሸጡት መኪኖችም መካከል ላምቦርጊኒ ቬኖኖ ሮድስታል በ9.1 ሚሊዮን ዶላር፣ ጥቁር ካርበን ኮይኒግሴግ 5.2 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠዋል።
ሰባት ፌራሪዎች፣ ሁለት ላምቦርጊኒ፣ አምስት ቤንትሊ፣ ማዘራቲ፣ አስተን ማርቲን፣ ማክላረን የተባሉት መኪኖች በ26 ሚሊዮን ዶላር በጨረታ ተሸጡ።
ግማሹ የተገዙት ስማቸው ያልተጠቀሰ ግለሰብ ሲሆን እሳቸውንም ወክሎ አንድ ጀርመናዊ ነው የተጫረተው።
ነገር ግን ከአምስት ወራት በኋላ በኢኳቶሪያል ጊኒ መዲና ማላቦ ቲዎዶሮ በጨረታ ከተሸጡት አንደኛዋ መኪና ሲነዳ ታየ፤ ፎቶውንም በኢንስታግራም ቢለጠፍም በኋላ ግን አጥፍቶታል።
ምንም እንኳን በነዚህ አገራት ስልጣን በውርስ የማስተላለፍ ሁኔታዎች ቢታይም እየተቀየረች ባለችው አፍሪና ለውጥን በሚሻ ወጣት መካከል የዘለቄታዊነቱን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።

*የዚሀ ፅሁፍ አዘጋጅ በለንደን የሚገኘው ቻታም ሃውስ የአፍሪካ ፕሮግራም አማካሪው ፓውል ሜሊ ናቸው












