ምርጫ 2013፡ ቦርዱ በተለያዩ ክልሎች መጪው ምርጫ የማይካሄድባቸውን ስፍራዎች አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Mustafa Ferhat Beksen
ኢትዮጵያ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በምታደርገው አገር አቀፍ ምርጫ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ምርጫ የማይካሄድባቸውን ቦታዎች ዝርዝር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ምርጫ የማይካሄድባቸው ቦታዎችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
በእነዚህ ስፍራዎች ምርጫ የማይካሄደው በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባለመጀመሩ፣ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ በመቋረጡና የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበ መሆኑን ቦርዱ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሰራር ችግር በማየቱ ማጣራት እንዲካሄድ የወሰነባቸው ቦታዎችም እንዲሁ ምርጫው እንደማይከናወን አስታውቋል።
ከእነዚህም ውስጥ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቦርዱ ምርጫ አይካሄድባቸውም ያላቸው የምርጫ ክልሎች መተከል፣ ሺናሻ ልዩ፣ ካማሺ እና ዳለቲ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል በሰባት ምርጫ ክልሎች ማለትም በቤጊ፣ በሰኞ ገበያ፣ አያና፣ ገሊላ፣ አሊቦ፣ ጊዳሚና ኮምቦልቻ ምርጫ የማይከናወንባቸው ሲሆን ፤ እነዚህ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ናቸው።
በአማራ ክልል ከዚህ ቀደም በፀጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ድምፅ መስጠት እንደማይከናወን ቢያሳውቅም በትናንትናው መግለጫ ምርጫ እንደማይካሄድ ተገልፃ የነበረችው ድልይብዛ ምርጫ ክልል ሰኔ 14 ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቋል።
በክልሉ በማጀቴ፣ በአርጎባ፣ በሸዋሮቢት፣ በኤፌሶን፣ በጭልጋ አንድና በጭልጋ ሁለት፣ በላይ አርማጭሆ እንዲሁም በአንኮበር የምርጫ ክልሎች ድምፅ እንደማይሰጥ ገልጿል።
ለዚህም ቦርዱ እንደ ምክንያትነት የጠቀሰው የአርጎባ ልዩ ምርጫ ክልል ላይ የሚመርጡ ዜጎች ለክልል ምክር ቤት በዚህ ምርጫ ክልል ድምፅ የሚሰጡ በመሆኑ እና በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለመመዝገባቸው ነው ብሏል።
ቦርዱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሰባት ምርጫ ክልሎች ምርጫ አይካሄድም ብሏል። በነዚህ ስፍራዎች ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የመራጮች ምዝገባ እንዳልተጀመረም አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ቀይ አፈር መደበኛ፣ ሱርማ ልዩ፣ ዲዚ ልዩ፣ የምርጫ ክልሎች ድምፅ እንደማይሰጥ ያሳወቀ ሲሆን፤ በተጨማሪም ማጀት መደበኛ፣ ጉራፈርዳ፣ ሽኮ፣ና ቴፒ የምርጫ ክልሎችም በእለቱ ድምፅ ይሰጥም ብሏል።
በሶማሌ ክልል በአሁኑ ወቅት 14 የምርጫ ክልሎች ላይ ድምፅ የመስጠት ሂደት ላይ ችግር አለ የሚል ሪፖርት ደርሶት በዚህም መሰረት ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።
አስራ አንዱ የምርጫ ክልሎች ምርመራ ላይ ያሉ መሆኑን ምርጫ ቦርዱ ገልፆ የመራጮች ምዝገባ ላይ መጠነ ሰፊ የአሰራር ችግር አለ በሚል የቀረበለትን ሪፖርት ለመገምገም አጣሪ ቡድን አሰማርቶ የማጣራት ተግባሩን ማከናወኑን በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
የአጣሪውን ቡድን ሪፖርት መሰረት በማድረግ ምርጫ የሚካሄድባቸውን የምርጫ ክልሎች እንደሚያሳውቅም ገልጿል።
በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው እና የማጣራት ሂደቱ ላይ የሚወሰኑ ተብለው በምርጫ ቦርዱ የተጠቀሱት አራቢ፣ ደግሃመዶ፣ ጎዴ፣ ጂግጂጋ 1፣ ጂግጂጋ 2፣ ቀብሪደሃር፣ ቀላፎ፣ ዋርዴር፣ ፊቅ፣ ገላዲንና ደገሃቡር ናቸው።
የመራጮች ምዝገባ ሂደት በክልሉ የተቋረጠባቸው ደግሞ አይሻ፣ ኤረርና ሽን የምርጫ ክልሎች ናቸው።
ግንቦት 28/2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ብሔራዊ ምርጫ፣ የመራጮች ምዝገባ እና ሌሎች ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠነቃቀቸው የተነሳ ምርጫው ለሁለት ሳምንታት እንዲገፋ ሆኖ ሰኔ 14 እንዲካሄድ ተወስኗል።
ኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ የምታካሂደው ምርጫ መካሄድ የነበረበት ባለፈው ዓመት ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው እንዲራዘም መደረጉ የሚታወስ ነው።












