የሕዳሴው ግድብ፡ ኢትዮጵያ ከሕዳሴው ግድብ ሙሌት የሚያደናቅፋት ኃይል እንደሌለ ገለጸች

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water, Irrigation and Energy

ኢትዮጵያ በመጭው የክረምት ወራት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሙከራ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ይህን ያለችው በመጭው ክረምት ለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት ነው።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ከግድቡ ሙሌት እና ግንባታ ጋር ተያይዞ የአሠራር ሂደቱን "ምንም ዓይነት ኃይል እንደማያደናቅፈው" ገልጿል።

ኢትዮጵያ ትናንት ረቡዕ የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን አስታውቃለች።

የግድቡ ተደራዳሪዎች ቴክኒክ ቡድን አባል በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) ለብሔራዊ ጣቢያው በሰጡት አስተያየት የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የግድቡ የሲቪል ግንባታ 91.8፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታው 54.5 በመቶ እንዲሁም የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራው ደግሞ 55.2 በመቶ መድረሱንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚቀረው 20 በመቶ ግንባታ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ በቀጣዩ ክረምት ኢትዮጵያ የምታከናውነው የውሃ ሙሌት አገራቸው ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንደማይኖረው መናገራቸው የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ታላቁ የአስዋን ግድብ በቂ ውሃ በመያዙ የሕዳሴ ግድቡ በመጪው ክረምት ውሃ መያዙ ግብጽን አይጎዳም ሲሉ ነው ሳሚ ሽኩሪ የተናግሩት።

የሕዳሴ ግድቡ በመጪው ክረምት ውሃ ከመያዝ በተጨማሪ በተያዘው ዓመት መገባደጃ ላይ ቅድመ ኃይል እንደሚያመነጭም በለጠ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት የሕዳሴው ግድብ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዘ መንግሥት የገለጸ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ካቆረው 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ውሃ ጋር በዓመቱ መጨረሻ የውሃውን መጠን ወደ 18 ቢሊዮን ከፍ ያደርገዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበርና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ሴሸዴኪ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሦስቱን አገራት ሊያግባባ የሚችል አዲስ ሃሳብ ማቅረባቸው ተስምቷል።

የሦስቱን አገራት መሪዎች ተዘዋውረው ያነጋገሩት ፕሬዝዳንቱ ላመነጩት ሀሳብ ውጤታማነት የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ሕብረት ድጋፋ እንደሚያደርጉ አል ሞኒተር የተባለ የዜና ተቋም ዘግቧል።

ሀሳቡ በግድቡ ሙሊት ዙሪያ ኢትዮጵያ የጊዜ ሰሌዳዋንና የውሃውን መጠን መረጃ የምትሰጥበት ሆኖ አገራቱ ከሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያስችላል ነው የተባለው።

በአባይ ወንዝ ላይ የተመሠረቱት ግብጽ እና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ውሃ ሙሌትና ግንባታ በፊት በቅድሚያ ከስምምነት ላይ መደረስ እንደሚገባ በተደጋጋሚ አቋማቸውን ገልጸዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ10 ዓመታት በፊት ሲጀመር የጀመረው ይኸው የሕዳሴው ግድብ ድርድር ለበካታ ጊዜያት ያለስምምነት መቋረጡ በቀጠናው ስጋት ፈጥሯል።