ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላት ተቃውሞ ለምን ጠነከረ?

የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

ሱዳን ለአስርት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል የማያባራ ውዝግብ በቀጠለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሃል አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች።

ለዓመታት ያህል የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሱዳን እይታ (አቀራረብ) የነበረው ሁኔታውን ሰፋ አድርጎ በማየት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተጠራጣሪነትና የጠብ አጫሪነት ሚናን መጫወት ጀምራለች።

ይሄ ለውጥ በብዙ መልኩ ለረዥም ዓመታት ሱዳንን የገዟትን ኦማር አል-በሽር ከስልጣን መገርሰስን ተከትሎ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲያሻግራት በጊዜያዊነት የመጣው የሽግግር መንግሥት ላይ ወታደራዊው ሥርዓት ከፍተኛ ጫና ነፀብራቅ ነው።

በተለይም ያለ ሦስትዮሽ ስምምነት ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት በመጪው ክረምት እጀምራለሁ ማለቷ ጋር ተያይዞ ዲፕሎማሲያዊው ግፊት ከፍ ብሏል።

ሁለቱ አገራት ግብጽና ኢትዮጵያ ስለ ሕዳሴ ግድብ ሲያነሱ የህልውናቸው መሰረት ባደረገ መልኩ ነው።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ብርሃን ለተነፈገው 60 በመቶ ሕዝቧ ብርሃን ያመጣል እንዲሁም ለልማቴ ቁልፍ ነው ትላለች።

ግብጽ በበኩሏ ግድቡ አገሪቷ የምታገኘውን የውሃ መጠን እንደሚቀንስና የሕዝቧን ህይወት መሰረት ያናጋዋል ትላለች።

ሁለቱን አገራት በሚያገናኘው ወንዝ መካከል የምትገኘው ሱዳን በበኩሏ ቆፍጠን ያለ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፍ ጀምራለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ
Getty
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

የሚመነጨው ኃይል ሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል

  • የግንባታ ወጪከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ

  • ግንባታው የተጀመረው2003 ዓ.ም.

    Source: ሮይተርስ

    የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት የበላይ የሆኑት የሌተናል ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን አማካሪ የውሃ ጦርነት እንደሚነሳ ገልፀዋል፤ "ከሚታሰበው በላይ የከፋ ይሆናል" በማለት አስጠንቅቀው "ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ እስካላገኘ ድረስ ጦርነት አይቀሬ ነው" ብለዋል።

    ግድቡ በመጀመሪያ ተቀባይነት ነበረው

    ወደ ኋላ አስራ አራት ወራትን መለስ ብለን ብናጤን ከመዲናዋ ካርቱም በግድቡ ጉዳይ የተለያዩ ድምፆች ይሰሙ ነበር።

    በአውሮፓውያኑ የካቲት 2020 የውሃ ሚኒስትሩ ያሲር አባስ ግድቡ ምን ያህል ለሱዳን ጠቃሚ እንደሆነ አብራርተው ነበር።

    ምናልባት መስተካከል ካለባችው አንዳንድ ጥቃቅን ጉዳዮች በስተቀር የሕዳሴ ግድብ የናይልን ፍሰት በተመጠነ መልኩ እንደሚያደርገውና ሦስተኛ የእርሻ ወቅትን በአገሪቷ ሊያስጀምር ይችላል ሲሉ ተደምጠው ነበር።

    ከዚህም በተጨማሪ በቀን ውስጥ 12 ሰዓታት ያህል የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚቋረጥባት ሱዳን በአስተማማኝና በረከሰ ዋጋ አቅርቦት ማግኘት ነው ተባለ።

    ነገር ግን በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ይካሄድ በነበረው የሦስቱ አገራት የኪንሻሳው ድርድር ፍሬ አልባ መሆኑን ተከትሎ የውሃ ሚኒስትሩ ያሲር አባስ ኢትዮጵያ አገራቱ የሚያወዛግቧቸው ጉዳዮች ሳይፈቱ በውሃ ሙሌቱ የምትቀጥል ከሆነ የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ ይጥላል በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ሱዳን ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን በምን ያህል ጊዜ እንደምታከናውን እንዲሁም ግድቡ የሚቋጥረው የውሃ መጠንን በተመለከተ መመሪያ ሳይሆን አሳሪ የሆነ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ትፈልጋለች።

    ከዚህም በተጨማሪ ለወደፊቱ አለመግባባቶች ቢፈጠሩ እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ የሚለውም ላይ ግልፅ ያለ ሁኔታ መኖር አለበት ትላለች።

    ያሲር አባስ በቅርቡ ለቢቢሲ ኢትዮጵያ ውሃውን ለእርሻ መጠቀም እፈልጋለሁ ብላለች በማለት ገልፀው ይህም ሁኔታ እስካሁን የነበሩ ድርድሮችን የበለጠ እንደሚያወሳስባቸው ተናግረዋል።

    "ያለ ምንም ስምምነት የሕዳሴ ግድብ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ሕዝቦች ከባቢ ሁኔታም ሆነ ለሕዝቡ አኗኗር አደጋ ነው" በማለት አክለዋል።

    የሱዳን የውሃ ሃብት ሚንስትር
    Getty
    ከስምምነት ሳይደረስ፤ የግድቡ ውሃ ሙሌት መጀመር ለታችኛው የተፋሰስ አገራት ስጋት ነው . . .
    ያሲር አባስ
    የሱዳን የውሃ ሃብት ሚንስትር

    የሕዳሴ ግድብ ሙሌቱ የአባይ ወንዝን ፍሰት መጠን የሚቀንሰው ከሆነ ከግብጽ በላይ የምትጎዳው ሱዳን ናት የሚሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ግብጽ በአስዋን ግድብ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ተቀማጭ ውሃ እንዳለት በመግለፅ ነው።

    እነዚህ ሱዳን እንደ ምክንያትነት የምታቀርባቸው መረጃዎች ለረዥም ዘመናት የሚታወቁ ጉዳዮች ነበሩ። ነገር ግን የተቀየረ ጉዳይ ቢኖር የአልበሽርን መውደቅ ተከትሎ የመጣው በሲቪልና በወታደራዊው አመራር መካከል የትኛው የበለጠ የኃይል ሚዛን አለው የሚለው ነው።

    በተጨማሪም በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር መካከል በአልፋሽጋ የተነሳው የግዛት ይገባኛል ውዝግብ ሱዳን ለኢትዮጵያ እንዳትወግን ካደረጓት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሹ ሊሆን ይችላል።

    በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ድንበር በትክክል ባይሰመርም፤ የቅኝ ግዛት ውሎች አልፋሽጋ የሱዳን ግዛት መሆኑን ያሳያሉ። ይሁን እንጂ በስፍራው ኢትዮጵያውያ ይኖሩ የነበረ ሲሆን ግብርም ይገብሩ የነበሩት ለኢትዮጵያ መንግሥት ነበር።

    በአውሮፓውያኑ 2008 ኢትዮጵያ ግዛቱ የሱዳን እንደሆነ ዕውቅና ብትሰጥም ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ቀጥለዋል።

    ከቅርብ ወራት በፊት ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተነሳው ግጭት ፊቷን ባዞረችበት ወቅት ሱዳን ይህንን ክፍተት በመጠቀም ወታደሮቿን ወደ አልፋሽጋ እንዲሰማሩና እንዲቆጣጠሩ አድርጋለች።

    የሱዳን ወደ ግብ መጠጋት

    የሱዳን መንግሥት በድንበር አካባቢው የሚደረገው ወታደራዊ እርምጃ ሕዝቡ እንዲደግፍ ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

    የዚህም ዘመቻ አካል የሆነው በአገሪቷ ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ግለሰቦችን ወደ ድንበር አካባቢ መውሰድ እንዲሁም ስመጥር ዘፋኞች በወታደራዊ መለዮ በካርቱም እንዲዘፍኑ ማድረግ ይገኝበታል።

    በሰሜናዊ ሱዳንም የአገሪቱ አየር ኃይል ከግብጽ ጋር በጋራ ስልጠና በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

    "ኢትዮጵያን ለመሸንቆጥ የሚያደርጉት ሙከራ በደንብ ግልፅ ነው" በማለት የቀድሞ ብርጋዲየር ማህሙድ ጋሌንደር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ኢትዮጵያ በበኩሏ በተደጋጋሚ የሕዳሴ ግድብ በሱዳን ላይ ምንም አይነት ጉዳት አያስከትልም በማለት ሱዳን ስጋት እንዳያድርባት ለማድረግ ሞክራለች።

    በባለፈው ሳምንት እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሁ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ "በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉዳት የማስከተል ምንም አይነት አላማ የላትም" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረው እንዲያውም በባለፈው ዓመት የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ምክንያት "ጎረቤት አገር ሱዳንን ሊያጥለቀልቃት ከነበረው ክፉኛ ጎርፍ ታድጓታል" ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ከመጪው የክረምት ወር ከሚደረገው ሙሌት በፊት መረጃ መለዋወጥን በተመለከተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    የቀጣይ ድርድሮች አስፈላጊነት በጠነከሩበት በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት ሱዳንም ሆነ ግብጽ ከማስፈራራታቸው ቆጠብ የሚያደርጋቸው አልሆነም።

    እንዲያውም ከሰሞኑ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ሕጋዊ መፍትሄ ለማግኘትና ለዚህም አጋሮች ለማግኘት በአህጉሪቷ እየዞሩ ነው።

    "የግድቡ አሰራርና የውሃ ሙሌቱ የሦስቱን አገራት ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ" እንዲሆን ለማድረግ በሚልም ነው የሚኒስትሩን ጉብኝት በተመለከተ የግብጽ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ያተተው።

    የሱዳኑ ጄኔራል ቡርሃን በበኩላቸው በባለፈው ሳምንት ከአንድ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዲሁ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ይህ ይሁን እንጂ የዲፕሎማሲያዊ ጫና ቢጠነክርም፣ ውሳኔ ላይ ተደረሰም አልተደረሰም በመጪው ክረምት በሚዘንበው ዝናብ የግድቡ ሙሌቱ መከናወኑ የሚቀር አይመስልም።