የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የሕዳሴ ውዝግብን ለመፍታት ለአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውዝግብን ለመፍታት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲደረግ ለግብጽና ለኢትዮጵያ መሪዎች ጥሪ አደረጉ።
ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በኮንጎዋ መዲና ኪንሻሳ ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ ይህ ውይይት የመጨረሻ ሙከራ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
በኪንሻሳ ላይ ሱዳን እና ግብጽ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ታዛቢዎችን ሚና ለመቀየርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በአደራዳሪነት እንዲገቡ ሃሳብ ቢያቀርቡም ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም።
ኢትዮጵያ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲሆን ትፈልጋለች።
ይህንን የኢትዮጵያ ሃሳብም ሰሞኑን ሩሲያ እንደምትደግፈው የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሩሲያ የሕዳሴ ግድብ ውዝግብ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲፈታ ፍላጎት አላት በማለት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ንግግር ያደረጉት በካይሮዋ መዲና ከግብጹ አቻቸው ሳሜ ሽኩሪ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሆነ ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ በመጪው ሰኔ ክረምት ሲገባ ሁለተኛ ዙር ሙሌቷን በእቅዷ መሰረት እንደምታከናውን አስታውቃለች። ነገር ግን ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ስምምነት ላይ መደረስ አለበት ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ የህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ከማካሄዷ በፊት ግብጽ እና ሱዳን ለመረጃ ልውውጥ ባለሙያዎች እንዲመድቡ ጠይቃለች።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ወቅት ለምታከናውነው የውሃ ሙሌት አገራቱ የግድብ ባለሙያዎችን ኢንዲመድቡ በይፋ መጋበዛቸውን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።
ኢትዮጵያ ይህን ጥሪ ያቀረበችው፣ ቀደም ሲል ሦስቱ አገሮች በተስማሙት ስምምነት መሠረት ነው። ሆኖም ከሰሞኑ በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ላይ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው በማለት ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የግብጽ ፓርላማ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የፓርላማ አባል ታሪክ ሬድዋን በካይ በበኩላቸው በካይሮ በተደረገ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ምክር ቤቱ ግብጽ ያደረገችውን ጥሪ ውድቅ አድርገዋል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባል እንደሚሉት የሕዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮ ያለባቸውን ፍራቻና ተማፅኖ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት መስማት አይፈልጉም ይላሉ።
"የግብጽ አርሶ አደሮች የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት ልማት አይቃወሙትም። ልማታችን የሚሉት ውሃ ነው አርሶ አደሮቻችንና ሕዝባችንን የሚመግበው። የአባይ ውሃ ሊያስማማን በተገባ ነበር። የጦርነት መነሾ ሊሆን አይገባም" ብለዋል።
በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስካሁን ሲጓተት ቆይቶ በግንባታ ላይ አስር ዓመትን አስቆጥሯል።
ተገንብቶ ሲያበቃ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረው ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግንባታ ሥራው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተነገረለት ይህ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ፣ ለኢንዱስትሪዎችና ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።












