ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ አንጻር የያዙትን አቋም ተቸች

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Water, Irrigation and Energy

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ ላሳየችው በቅን ልቦና የመደራደር ፈቃደኝነት በጎ ምላሽ አልሰጡም ሲል የኢትጵያ መንግሥት ተቸ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ላይ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሱዳንና ግብጽ የሚያነሱት ተቃውሞ ላይ ጥያቄ አንስቷል።

ሚኒስቴሩ ቀደም ሲል ሱዳን ስለግድቡ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች ምላሽ ካገኙ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ አሁን ለምን በድጋሚ እንደተነሳ ጠይቋል።

"ኢትዮጵያ ሱዳን በግድቡ ላይ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች ቴክኒካዊ ስለሆኑ ምላሽ ሰጥታበታለች" ያለው ሚኒስቴሩ፤ ኢትዮጵያ መረጃ ለመለዋወጥ ፈቃደኝነቷን የገለጸች መሆኑንና የግድቡ ደኅንነት ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ በጥንቃቄ የያዘችው ጉዳይ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ይህንን ያለችው ባለፈው ሳምንት ኮንጎ ኪንሻሳ ውስጥ ከሁለቱ አገራት ጋር በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ያቀረበችው መረጃ የመለዋወጥ ጥያቄ በአገራቱ ተቀባይነት ሳያገኝ ከቀረ በኋላ ነው።

ጨምሮም የሱዳን ባለስልጣናት ለዓመታት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለአገራቸው የጎርፍ አደጋን በመቀነስ፣ ለመስኖ የሚውለውን የውሃ ፍሰት በማመጣጠን፣ ከፍተኛ መጠን ያለውን ደለል በመከላከልና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ለማግኘት እንደሚያስችል በመግለጽ ሲያደንቁት መቆየታቸውን አመልክቷል።

ወደ መጠናቀቁ በተቃረበው ግድብ ዙሪያ ቀደም ሲል ከሱዳን በኩል የቀረቡ ጥያቄዎች መመለሳቸውን ያስታወሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ "ሱዳን በግድቡ የውሃ ሙሌት ላይ ካቀረበችው ተቃውሞ የሚጠቀመው ማን ነው?" ሲል ጥያቄ አቅርቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከግዛቷ የሚመነጨውን ውሃ በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ተግባር ስትነሳ የታችኛው አገራትን በመጋበዝ ለድርድር መቅረቧ የትም ቦታ ላይ ያልታየ ልምድ መሆኑን በመጥቀስ የኢትዮጵያን ለመስማማት ያላትን ፍላጎት አመልክቷል።

ከዚህም አንጻር "ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በመረዳት በቅን ልቦና ለመደራደር ያሳየችውን ለጋስነት ግብጽ ተገቢውን እውቅና ሳትሰጠው ቀርታለች" በማለት ሚኒስቴሩ ግብጽን ወቅሷል።

ሱዳንና ግብጽ ሲካሄዱ በቆዩት ድርድሮች ላይ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የሚያገኙትን ውሃ ይቀንስብናል ሲሉ ተመሳሳይ አቋም ይዘው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

በቅርቡ የተካሄደውን ጨምሮ ለዓመታት በሦስቱ አገራት መካከል የግድቡን ውሃ አሞላልና ቀጣይ ሂደት በተመለከተ ሲያደርጓቸው የነበሩት ድርድሮች ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ እስካሁን ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት ለማከናወን እየተዘጋጀች መሆኑን ማሳወቋን ተከትሎ ሱዳንና ግብጽ በተለያየ መልኩ ጫናን ለማሳደር ሙከራ እያደረጉ ነው።

ከዚህ አንጻርም ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት ሳይደረግ ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም ኢትዮጵያ አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ገልጻ አገራቱ ባለሙያ እንዲመድቡ ከቀናት በፊት ጥያቄ አቅርባ ነበር።

ሱዳንና ግብጽ ግን ድርድሩ ተካሂዶ አስገዳጅ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መከናወን እንደሌለበትና ባለሙያም ከዚያ በፊት እንደማይሰይሙ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ግን ከስምምነት ላይ ተደረሰም አልተደረሰ የግድቡ ውሃ ሙሌት በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአጽንኦት ተገልጿል።

በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስካሁን ሲጓተት ቆይቶ በግንባታ ላይ አስር ዓመትን አስቆጥሯል።

ተገንብቶ ሲያበቃ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረው ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግንባታ ሥራው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተነገረለት ይህ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ፣ ለኢንዱስትሪዎችና ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።