የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት "በምንም ዓይነት መልኩ" እንደማይራዘም ተገለፀ

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters

ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደማታራዝም ገለፀች።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር በቀጣዩ ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘምና ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ገልጿል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን የገለፀው የህዳሴ ግድብን 10ኛ ዓመትን በማስመልከት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኝ የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ፣ የሦስትዮሽ ድርድሩ የደረሰበት ደረጃ ለመግለፅ እና ግብዓት ለመሰብሰብ ባለመ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 79 በመቶ እንደደረሰ ገልፀዋል።

ሱዳንና ግብጽ ባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው አማካይነት በተደረጉ ጉብኝቶች ላይ ኢትዮጵያ ቀጣዩን ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት በሦስቱ አገራት መካከል ከስምምነት መደረስ አለበት ማለታቸው ይታወሳል።

ለዚህም በአገራቱ መካከል በግድቡ ውሃ አሞላልና ቀጣይ ሥራ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር ላይ ተጨማሪ አደራዳሪዎች እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ደብዳቤ ሱዳን መጻፏን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሱዳን ዜና ወኪል የሆነው ሱና ዘግቧል።

ሱና እንዳለው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ፣ የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ለሆኑት ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት፣ ለአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮችና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ፣ ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሕዳሴን ግድብ ድርድር በሚመለከት ደብዳቤ ልከዋል።

ይህንን የሱዳንን ጥያቄ በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ማክሰኞ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሰጡት ምላሽ "በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሚያደርጉት የሦስትዮሽ ድርድር የሚቋጨው በሦስቱ አገራት እንጂ በአደራዳሪዎች አይደለም" ብለዋል።

"የአደራዳሪ ሚና ማስተባበር እንጂ ማጉረስ አይደለም" ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ነገር ግን ሱዳንና ግብጽ አራት አደራዳሪ ወገኖች ይግቡ በሚል ያቀረቡት ሃሳብ ለኢትዮጵያ በይፋ እንዳልቀረበ ገልጸዋል።

አክለውም አደራዳሪነት ማስተባበር እንጂ ውይይቱ የሚቋጨው በሦስቱ ተደራዳሪዎች እንደሆነ በስምምነት ሰነዱ መቀመጡን ገልጸዋል።

"ለአፍሪካ ሕብረት ትልቅ ክብር አለን፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ፅኑ አቋም አላት" በማለትም ተናግረዋል።

ሃምዶክ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ሱዳን "ኢትዮጵያ ሦስቱ አገራት [ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ] ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ሁለተኛውን ሙሌት በሰኔ ወር ለማካሄድ መወሰኗ አሳስቦናል" ብለዋል።

አምባሳደር ዲና በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ለድርድር ሁሌም ዝግጁ ናት። ሙሌቱ ይቀጥላል። ድርድሩ ግን ከሙሌቱ በፊትም ቢሆን ቢቋጭ ኢትዮጵያ ችግር የለባትም" ብለዋል።

ሐምዶክ አራተኛ አደራዳሪ መግባቱ "ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድጋፍ ያስገኛል እንዲሁም በድርድሩ ላይ መተማመንን ያረጋግጣል" ብለዋል።

የመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የግድብ ሙሌት ሥምምነት ከመደረሱ በፊት እንዳታካሂድ ጠይቀዋል።

ሱዳን በበኩሏ በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ሦስቱ አገራት ከሥምምነት ላይ ሳይደርሱ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት እንዳይካሄድ መግለጫ አውጥታ ነበር።

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና አስረኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከጥቂት ወራት በኋላ እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያስታወቀች ሲሆን፤ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።

የታላቂ ሕዳሴ ግድብ "የኤሌትሪክ ብርሃን ላላገኙ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተስፋ ነው" ሲሉ የውሃ ሚኒስትሩ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስፍረዋል።