አሜሪካ፡ በአትላንታ በተፈፀመ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገደሉ

በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት ባሉ ስፓዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት ባሉ ስፓዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ሰዎች ተገደሉ። አብዛኛዎቹ ሟቾች የእስያ ተወላጅ ሴቶች ናቸው ተብሏል።

ጥቃቱ የደረሰው ከአትላንታ በስተሰሜን በምትገኘው አክዎርዝ ማሳጅ ቤት እና በከተማዋ ውስጥ ባሉ ሁለት ስፓዎች መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

ደቡብ ኮሪያ ከተጎጂዎች መካከል አራቱ የኮሪያ ዝርያ ያላቸው መሆናቸውን አረጋግጣለች፡፡

ባለስልጣናት የ 21 አመት ወጣት በቁጥጥር ስር መዋሉን እና ከሁሉም ጥቃቶች ጀርባ እንዳለበት ይታመናል ብለዋል፡፡

የግድያው መነሻ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም፡፡

በእስያ-አሜሪካውያን ላይ የጥላቻ ወንጀሎች ከቅርብ ወራት ወዲህ እየጨመሩ ናቸው። ለኮቪድ -19 መስፋፋት ተጠያቂ መደረጋቸው ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር በእስያ-አሜሪካውያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት፣ እንግልት፣ ክስ እና ውንጀላ ኮንነዋል፡፡

ስለ ተኩስ ምን እናውቃለን?

የመጀመሪያው የተኩስ ልውውጥ የተከናወነው በቼሮኪ አውራጃ በአክዎርዝ በሚገኘው በያንግ ኤሲያን ማሳጅ ፓርለር ነበር፡፡

የፖሊስ ቃል አቀባዩ ካፕቴይን ጄይ ቤከር ሁለት ሰዎች በቦታው መሞታቸውንና ሶስት ሰዎች ደግሞ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልፀዋል። ሆስፒታል ውስጥ ሌሎች ሁለት ሰዎች እንደሞቱ ተናግረዋል፡፡ ከተጎጂዎቹ ሁለቱ የእስያ ዝርያ ያለባቸው ወንድ እና ሴት መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ሌላ የሂስፓኒክ ዝርያ ያለበት ግለሰብ መቁሰሉን ተናግረዋል።

ከአንድ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በሰሜን ምስራቅ አትላንታ በሚገኘው ጎልድ ስፓ "ዝርፊያ እየተካሄደ ነው" በሚል ፖሊስ መጠራቱን ገልጿል።

ፖሊስ በሪፖርቱ እንደገለጸው "ፖሊሶች በቦታው በደረሱበት ወቅት የሞቱ ሶስት ሴቶች ተገኝተዋል፡፡

ከመንገዱ ባሸገር በሚገኘው የአሮማቴራፒ ስፓ የተጠሩት ፖሊሶች የተገደለች ሌላ ሴት አግኝተዋል፡፡

የአትላንታ ጆርናል-ኮንስቲትዩሽን፣ ፖሊስን ጠቅሶ እንዳስታወቀው አራቱ የአትላንታ ተጠቂዎች የእስያ ዝርያ ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡

መርማሪዎች በአንዱ ስፓ አቅራቢያ የተቀረጸን የተጠርጣሪ ምስል ለቅቀዋል፡፡

በጆርጂያ ጆርጅ ዉድስቶክ ነዋሪ የሆነው ሮበርት አሮን ሎንግ ከአትላንታ በስተደቡብ 240 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ክሪስፕ ካውንቲ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ካፕቴን ቤከር እንዳሉት በሦስቱም ግድያዎች ተጠርጣሪው ተመሳሳይ ግለሰብ እንደሆነ መርማሪዎች በጣም እርግጠኞች ናቸው፡፡

ምላሹ ምን ነበር?

ተጎጂዎቹ በዘር ወይም በጎሳ ምክንያት የተለዩ ስለመሆናቸው ለማወቅ ምርመራው ገና መሆኑን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል፡፡

ኤሺያን አሜሪካንስ ኤንድ ፓስፊክ አይስላንደርስ የተባለው ተሟጋች ቡድን በበኩሉ "ሊገለጽ የማይችል አሳዛኝ አደጋ" ብሎታል፡፡

"በአሁኑ ወቅት በእስያ አሜሪካዊያን ማህበረሰብ ውስጥ መፍትሄ ሊበጅለት የሚገባው ከፍተኛ ፍርሃትና ህመም አለ" ሲል በትዊተር ገፁ አስፍሯል፡፡

የአትላንታ ፖሊስ ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ጋር ተመሳሳይ በሆኑ የንግድ ተቋማት ዙሪያ የጥበቃ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የጆርጂያው ገዥ ብራያን ኬምፕ ለጉዳዩ ምላሽ የሰጡትን የህግ አስከባሪዎች አመስግነው "ለዚህ ዘግናኝ ድርጊት ሰለባዎች እየጸለይን ነው" ብለዋል፡፡

የኒው ዮርክ ፖሊስ መምሪያ የፀረ-ሽብርተኝነት ክፍል በበኩሉ "በከተማው ባሉ ታላላቅ የእስያ ማህበረሰቦቻችን ዙሪያ ለጥንቃቄ ሲባል ኃይል ያሰማራል" ብሏል፡፡