ደቡብ አፍሪካ፡ ተማሪውን መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ የገባ ስልኩን እንዲያወጣ ያደረገው መምህር ተቀጣ

መጸዳጃ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ11 ዓመትን ልጅ የሞላ መፀዳጃ ቤት ውስጥ ገብቶ የጠፋ ስልክ እንዲፈልግ አስገድዷል በሚል ክስ የቀረበበት አንድ የደቡብ አፍሪካ ርዕሰ መምህር ከሥራው ታገደ፡፡

ግለሰቡ ልጁን ለመጸዳጃ ቤት በሚያገለግለው ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አስሮ እንዲገባ ያደረገው ሲሆን፣ ለዚህ ተግባሩም 200 ራንድ (14 ዶላር ) እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለት ነበር ተብሏል፡፡

በዚህ ምክንያት ተማሪዎች ያፌዙበት ስለነበር ልጁ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ መፍራቱን አያቱ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን ሲሰማ "በሃፍረት" እንደተሰማው የአካባቢው የትምህርት ቢሮ ለታይምስ ላይቭ ገልጿል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የጉድጓድ መጸዳጃ ቤቶች በጥቅም ላይ ይውላሉ። ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ካሉ ትምህርት ቤቶች አንድ ስድስተኛ የሚሆኑት መጸዳጃ ቤቶቻቸው የአደጋ ስጋት እንዳለባቸው የተገለፀ ቢሆንም አሁንም ግን እንደሚጠቀሙባቸው ይገመታል፡፡

ፉንዲሌ ጋዴ የተባሉ የምስራቃዊ ኬፕ የትምህርት ቢሮ ባለሥልጣን ድርጊቱን "ከነውርም በላይ ነው" ያሉ ሲሆን፣ ራሳቸው ይቅርታ ለመጠየቅ የተማሪውን ቤት እንደሚጎበኙ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በሉቱቱ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት ግለሰብ ላይ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመጋቢት ወር መጀመሪያ በድንገት ወደ ሠራተኞቹ መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ የገባውን ስልክ ለማውጣት እንዲረዱ ሌሎች ልጆችንም ማበረታታቸው ተነግሯል፡፡

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት ጉዳዩ ይፋ ተደረገው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚሠራ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መረጃውን በማግኘቱ ነው፡፡

ለኩላ ማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክት የሚሠሩት ፒተር ማጆላ ስልኩን ለመፈለግ ለአንድ ሰዓት መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ ይህን በሚመለከት የለቀቁት ቪዲዮውም በብዙዎች ተጋርቷል።

እንደ ማጁላ ከሆነ ተማሪዎች የተወሰነውን ቆሻሻ ለማስወገድ ባልዲዎችን ተጠቅመዋል። በኋላም ልጁ "አይነ ምድር ውስጥ እስከ ጉልበቱ ድረስ እንዲገባ" ተደርጓል ብለዋል፡፡

"ስልኩን ለመፈለግ እጆቹን የተጠቀመ ሲሆን አይነ ምድሩን ከእጆቹ በላይ እስከ ክርኑ ድረስ ነክቶታል" ብለዋል፡፡

ኒውስ 24 እንደዘገበው ስልኩ ባይገኝም ርዕሰ መምህሩ ተማሪው ላደረገው ጥረት 50 ራንድ ሰጥቶታል፡፡

ስማቸው ያልተጠቀሰው የልጁ አያት ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት የልጅ ልጃቸው ከደረሰበት ችግር በኋላ ሃፍረት ተሰምቶታል፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ 2018 የአምስት ዓመት ተማሪ በአንድ መጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የጉድጓድ መፀዳጃዎች ለማስወገድ መንግስት ቃል ገብቷል፡፡