ሶሪያ፡ ሩሲያ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ አሜሪካና ሌሎችም የተሳተፉበት የሶሪያ ጦርነት 10 ዓመታት ሆነው

በከባድ መሳሪያ ሁለት ልጆቹ የተገደሉበት አባት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በከባድ መሳሪያ ሁለት ልጆቹ የተገደሉበት አባት

በሶሪያ ፕሬዝዳንት ላይ ከ10 ዓመት በፊት የተጀመረው ሕዝባዊ አመጽ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ መጠነ ሰፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ተቀይሮ ከ380 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጓል። ከተሞችን ሲያወድም ቀውሱ ሌሎች አገራትን ስቧል።

የሶሪያ ጦርነት እንዴት ተጀመረ?

የሶሪያው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ አባታቸውን ሃፌዝ አል አሳድን ተክተው ወደ መንበረ ስልጣን የመጡት በአውሮፓውያኑ 2000 ነበር። ግጭቱ ከመጀመሩ በፊትም ብዙ ሶሪያውያን የነበረውን ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣ ሙስናና የፖለቲካ ነፃነት እጦት እያማረሩ ነበር።

በጎረቤት አገራት ጨቋኝ ገዥዎችን የሚቃወሙ አመጾች ተቀጣጥለው ነበር። ከዚህ በመነሳሳትም የዛሬ አስር ዓመት በደቡባዊዋ የዴራ ከተማ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይስፈን የሚሉ ሰልፎች አደባባይ ወጡ።

የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ለመጨፍለቅ ኃይል ተጠቅሞ ተቃዋሚዎችን መግደል ሲጀምር ፕሬዚዳንቱ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች በመላው አገሪቱ ተቀጣጠሉ።

አመጹም እርምጃውም ጎን ለጎን ተጠናከረ። የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ነፍጥ አነሱ፤ መጀመሪያ ራሳቸውን ለመከላከልና በኋላም አካባቢዎቻቸውን ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ነጻ ለማድረግ። ፕሬዝዳንት አል አሳድ "በውጭ የሚደገፉ ሽብርተኞች" ያሏቸውን እንደሚጨፈልቁ ቃል ገቡ።

አመፁ በፍጥነት ተባብሶ አገሪቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ገባች። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማፅያን ቡድኖች በየቦታው አበቡ። ግጭቱም በአሳድ ደጋፊዎችና ተቃዋሚ ሶርያውያን መካከል ባሻገር ሲሆን ጊዜ አልወሰደበትም። የውጭ ኃይሎች እጃቸውን አስገቡ። ገንዘብ፣ የጦር መሣሪያዎችን እና ተዋጊዎችን በመላክ የሚፈልጉትን ይደግፉ ጀመር።

እንደ እስላማዊ መንግሥት (አይ ኤስ) እና አልቃይዳ ያሉትም ጽንፈኛ ቡድኖች የራሳቸውን ዓላማ በመያዝ ተሳታፊ ሆኑ። ይህም እንደ ትልቅ ስጋት ለሚያዩዋቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ዘንድ ትልቅ ሥጋት ፈጠረ።

ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚፈልጉት የሶሪያ ኩርዶች ከአሳድ ኃይሎች ጋር ባይዋጉም ለግጭቱ ሌላ ገጽታን ሰጡት።

ጸረ መንግሥት ተቃውሞው በተጀመረበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጸረ መንግሥት ተቃውሞው በተጀመረበት ጊዜ

ምን ያህል ሰዎች ሞቱ?

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶርያ ኦብዘርቫቶሪ ፎር ሂዩማን ራይትስ (ኤስኦኤችአር) ሶሪያ ውስጥ የመረጃ ምንጮች አሉት። ድርጅቱ እስካለፈው ዓመት ድረስ 387,118 ሰዎች መሞታቸውን መዝግቧል። ከእነዚህም መካከል 116,911 ሰላማዊ ሰዎች ናቸው።

ይህ ቁጥር ጠፍተዋል ወይም መረጃቸው ያለተገኙትን 205,300 ሰዎችን አላካተተም። እንዲሁም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ በስቃይ ሞተዋል የተባሉ 88,000 ሰዎችንም አልተደመሩም።

ከተለያዩ አክቲቪስቶች መረጃ የሚያገኘው ቫዮሌሽን ዶክመንቴሽን ሴንተር ደግሞ በሠላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰቶች እና በሰብዓዊ መብቶች ሕግ ጥሰቶችን መዝግቧል።

እስካለፈው ዓመት ታኅሣስ ድረስ 135,634 ሠላማዊ ሰዎችን ጨምሮ 226,374 ከጦርነቱ ጋር የተዛመዱ ሰዎችን ሞት መዝግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ድርጅት- ዩኒሴፍ ደግሞ ወደ 12,000 የሚጠጉ ሕፃናት ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ሲል አስታውቋል።

የቆሰለ ህጻን ህክምና ሲደረግለት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቆሰለ ህጻን ህክምና ሲደረግለት

የጦርነቱ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?

የመንግሥት ቁልፍ ደጋፊዎች ሩሲያ እና ኢራን ናቸው። ቱርክ፣ ምዕራባዊያን ኃይሎች እና በርካታ የባሕረ ሰላጤ አረብ አገራት ላለፉት አስርት ዓመታት ተቃዋሚዎችን በተለያየ ደረጃ ደግፈዋል።

ሩሲያ ከጦርነቱ በፊትም በሶሪያ ውስጥ ወታደራዊ ካምፕ ነበራት። በ2015 (እአአ) አሳድን በመደገፍ የአየር ጥቃት ዘመቻ ጀምራለች። ይህም የጦርነቱን የበላይነት ወደ መንግሥት ወገን እንዲያጋድል ወሳኝ ነበር።

የሩሲያ ጦር ጥቃት የሚያተኩረው "አሸባሪዎች" ላይ ብቻ እንደሆነ ቢገልጽም አክቲቪስቶች ግን በመደበኛነት ዋና ዋና አማፅያን እና ሠላማዊ ሰዎች ይገድላሉ ብለዋል።

ኢራንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አሰማርታለች። አሳድን ለመርዳት በሚልም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዳወጣች ይታመናል።

አብዛኞቹ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ንቅናቄ አባላት የሆኑበትና በሺህዎች የሚቆጠሩ የሺአ ሙስሊም ታጣቂዎች በኢራን የትጥቅ፣ የስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን እና የመንንም እንዲሁ ከሶሪያ ጦር ጎን ሆነው ተዋግተዋል።

አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በመጀመሪያ "አክራሪ ያልሆኑ" ብለው ለሚያስቧቸው አማጺ ቡድኖች ድጋፍ ይሰጡ ነበር። ጂሃዲስቶች በታጠቁ ተቃዋሚዎች ላይ የበላይ ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ ለጦርነት የማይውል እርዳታ ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥተዋል።

በአሜሪካ የሚመራው ዓለም አቀፍ ጥምረትም እንዲሁ ከ2014 (እአአ) ጀምሮ በሶሪያ ውስጥ የአየር ጥቃት እያደረሰ ነው። ይህም የኩርድ እና የአረብ ሚሊሻዎች ጥምረት የሆነው የሶሪያ ዴሞክራቲክ ፎርስን (ኤስ ዲ ኤፍ) በማገዝ በሰሜን ምሥራቅ በአይ ኤስ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ለማገዝ ነው።

ቱርክ ለተቃዋሚዎች ከፍተኛ ድጋፍ ታደርጋለች። ትኩረቷ ግን የአማጺ ቡድኖችን በመጠቀም በአብዛኛው በኤስ ዲ ኤፍ ስር ያሉትን የኩርድ ዋይ ፒ ጂ ሚሊሺያን በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው። ቡድኑንም ቱርክ ውስጥ የታገደው የኩርድ አማጺያን ቡድን ተቀጥላ ነው በሚል ክስ ታቀርባለች።

የቱርክ ወታደሮች እና አጋር አማፅያን በሶሪያ ሰሜናዊ ድንበር ዙሪያ ሰፋፊ ቦታዎችን በመያዝ የመንግሥት ኃይሎች የመጨረሻዋን የተቃዋሚዎች ይዞታ ኢድሊብን እንዳያጠቁ ጣልቃ ገብተዋል።

የኢራን ተጽዕኖን ለመከላከል ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባት ሳዑዲ አረቢያ ጦርነቱ ሲጀመር አማጺያኑን አስታጥቃ በገንዘብ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች። ይህም የባሕረ ሰላጤው ተቀናቃኟ ኳታርም እንዳደረገችው መሆኑ ነው።

እስራኤል በበኩሏ ኢራን በሶሪያ ውስጥ ያላት "ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት" በጣም እንደሚያሳስባት ትገልጻለች። ኢራን የጦር መሣሪያዎችን ወደ ሄዝቦላህ እና ወደ ሌሎች የሺአ ሚሊሺያዎች መላክ በጣም ስላስጨነቃት እነሱን ለማደናቀፍ በማሰብ በተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን ሰንዝራለች።

በቱርክ የሚደገፉ የሶሪያ አማጺያን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በቱርክ የሚደገፉ የሶሪያ አማጺያን

ሕዝቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው?

እንደ ኤስ ኦ ኤች አር ከሆነ ግጭቱ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ከመሆን አልፎ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ሠላማዊ ዜጎች አደጋ ወይም ቋሚ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከጦርነቱ በፊት 22 ሚሊዮን እንደሆነ ከሚገመተው የሶሪያ ሕዝብ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ቤታቸውን ለቀው ተሰደዋል። ወደ 6.7 ሚልዮን የሚሆኑት በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ናቸው።

ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በመጠለያ ጣብያዎች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በውጭ አገር በስደት ላይ ይገኛሉ። 93 በመቶ የሚሆኑትን የሚያስተናግዱት ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ እና ቱርክ በቅርብ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ትልቁን የስደተኞች ቁጥር ለመቋቋም ተቸግረዋል። አንድ ሚሊዮን የሶሪያ ስደተኛ ልጆች በስደት እያሉ ተወልደዋል።

እስከዚህ ዓመት ጥር ወር ድረስ በሶርያ ውስጥ 13.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የሰብአዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች እንደነበሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት በከፍተኛ ደረጃ እርዳታ የሚሹ ናቸው።

ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በየቀኑ በቂ ምግብ ለማግኘት እየተቸገሩ ነው። ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናትም በተመጣጣኝ የምግብ እጥረት ተጎድተዋል።

ባለፈው ዓመት የሰብዓዊ ቀውሱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተባብሷል። የሶሪያ ምንዛሬ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን የምግብ ዋጋ ታሪካዊ በሚባል ደረጃ እንዲያሻቅብ አስገድዷል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ማጋጠሙ ደግሞ የአገሪቱ የምርመራ አቅም ውስን መሆን እና በተደቆሰው የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ሲጨመር እግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።

ከአስር ዓመቱ ጦርነት በኋላ በመላ አገሪቱ ያሉ ሁሉም መሠረተ ልማቶችም ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ቀጥለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሳተላይት መረጃ እንደሚያሳየው የአሌፖ ከተማ በ2016 መገባደጃ በድጋሚ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከመዋሏ በፊት ብቻ ከ35 ሺህ በላይ መሠረተ ልማቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም እንደወደሙ ጠቁሟል።

የህክምና ማዕከላት ጥበቃ ቢያስፈልጋቸውም እስካለፈው ዓመት መጋቢት ድረስ በ350 የተለያዩ የህክምና ተቋማት ላይ 595 ጥቃቶች ተሰንዝረው 923 የሕክምና ባለሙያዎች መሞታቸውን ፊዚሽያን ፎር ሂዩማን ራይትስ የተሰኘው ድርጅት መዝግቧል። እንዲህ ያሉት ጥቃቶች የአገሪቱን ግማሽ ሆስፒታሎች ብቻ ሙሉ በሙሉ እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል።

አብዛኞቹ የሶርያ ባህላዊ ቅርሶችም ወድመዋል። የአይ ኤስ ታጣቂዎች የጥንታዊቷ የፓልሚራ ከተማ ክፍሎችን ሆን ብለው ማፈንዳታቸውን ጨምሮ በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘጉ ስድስቱ የአገሪቱ ቅርሶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀል መርማሪዎች ሁሉንም ወገኖች "እጅግ በጣም አስከፊ ጥሰቶች" በመፈፀም ይከሳሉ።

የተፈናቀሉ የሶሪያ ህጻናት ከመተለያ ካምፓቸው ለቀው ለመውጣት ተዘጋጅተው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የተፈናቀሉ የሶሪያ ህጻናት ከመተለያ ካምፓቸው ለቀው ለመውጣት ተዘጋጅተው

አሁን አገሪቱን የሚቆጣጠረው ማነው?

መንግሥት የሶሪያን ታላላቅ ከተሞችን እንደገና ቢቆጣጠርም ሰፊው የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም በአማፅያን፣ በጂሃዲስቶች እና በኩርድ በሚመራው ኤስ ዲ ኤፍ ቁጥጥር ስር ናቸው።

ዋነኛው የተቃዋሚዎች ምሽግ የሚገኘው በሰሜናዊ ምዕራብ ኢድሊብ እና በአጎራባች የሰሜን ሀማ እና የምዕራብ አሌፖ ክፍሎች ነው።

አካባቢው ሀያት ታህሪር አል-ሻም (ኤች ቲ ኤስ) በሚባለው እና ከአልቃኢይዳ ጋር ግንኙነት ባለው የጂሃዳዊ ኅብረት የበላይነት የተያዘ ሲሆን ለዋነኞቹ አማፅያንም መኖሪያም ነው። አንድ ሚሊዮን ህፃናትን ጨምሮ በግምት ወደ 2.7 ሚሊዮን የተፈናቀሉ ሰዎች የሚኖሩት አካባቢ ነው። ብዙዎቹ በመጠለያዎች ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ይገኛሉ።

መንግሥት ኢድሊብን እንደገና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ለማስቆም ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ ሩሲያ እና ቱርክ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመዋል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ አንፃራዊ መረጋጋት ቢኖርም ስምምነቱ በማንኛውም ጊዜ ሊፈርስ እንደሚችል ይሰጋል።

ጦርነቱ መቼ ያከትማል?

በቅርብ ጊዜ የሚሆን አይመስልም። ሁሉም ግን ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ይስማማሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የጄኔቫ ስምምነት እንዲተገበር ጥሪ አቅርቧል። ስምምነቱ "በጋራ ስምምነት የተቋቋመ የሽግግር አስተዳዳር" እንዲመሠረት ይደግፋል።

በጄኔቫ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት የሚመሩ የሠላም ድርድሮች ለዘጠኝ ዙር ያህል ቢሞከርም ፍሬ አልባ ሆነዋል። ፕሬዝዳንት አሳድ ከስልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው ከሚሉት ከየትኞቹም የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ አልሆኑም።

ሩሲያ፣ ኢራን እና ቱርክም ከሦስት ዓመታት በፊት 'አስታና' በመባል የሚታወቅ ትይዩ የፖለቲካ ውይይቶችን ጀመረዋል።

በቀጣዩ ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ቁጥጥር ስር ለሚካሄድ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ የሚያግዝ አዲስ ሕገ-መንግሥት ለመፃፍ 150 አባላት ያሉት ኮሚቴ ለማቋቋም ከስምምነት ተደርሷል። ነገር ግን ይህ ሂደት ምንም አይነት እርምጃ አለማሳየቱን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ጂር ፔደርሰን በምሬት ተናግረዋል።