እስራኤል እና ሶሪያ የእስረኞች ልውውጥ አካሄዱ

እስራኤላዊቷ ድንበር አቋርጣ ሶሪያ ክልል በመግባቷ መያዟ ተነግሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አንዲት እስራኤላዊት ድንበር ስታቋርጥ በቁጥጥር ስር መዋሏንና መታሰሯን ተከትሎ እስራኤል እና ሶሪያ በሩሲያ አሸማጋይነት የእስረኞች ልውውጥ አካሄዱ።

የእስራኤል ጦር ሐሙስ ዕለት በአገሪቱ ቁጥጥር ስር የቆዩ የነበሩ ሁለት ሶሪያውያን እስረኞች እንደተመለሱ አስታውቋል።

ግለሰቧ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነበር በኩኔይትራ አቅራቢያ ወደ ሶሪያ መግባቷ የተገለጸው።

ሴትየዋ ወደ እስራኤል ለመመለስ ዝግጅቷን አጠናቃለች። የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ግለሰቧ ከሶሪያ ወደ ሩሲያ ማቅናቷን ተከትሎ እሷን የሚያመጣ አውሮፕላን ተልኳል፡፡

ሩሲያ ከሶሪያ መንግስት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሲሆን በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 አንድ የእስራኤል ወታደር አስክሬን እንዲመለስ ሸምግላለች፡፡

እስራኤል በጎርጎሮሳዊያኑ 1967 በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የጎላን ኮረብታዎችን ከሶሪያ ነጥቃ በ1981 ደግሞ የሃገሯ አካል በማድረግ አዋህዳለች። ይህ እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አልተሰጠውም፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ማክሰኞ ምሽት የካቢኔውን ሙሉ ስብሰባ ጠርተው የነበረ ሲሆን፣ ይህም ልውውጡ ላይ ለመወያየት ነበር ተብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በቀጠናው፣ በፀጥታና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተነጋግረዋል፡፡