የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት በድንበሩ ጉዳይ ሱዳንን እንዲመክሩ ጥሪ አቀረበች

የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የድንበር አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ የአፍሪካ አገራት ሱዳንን በመምከር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ሐሙስ ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ በድንበር ጉዳይ ሰበብ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት እንዲገቡ የሱዳን የመከላከያ ኃይል ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ነው ሲል ወንጅሏል።
በተጨማሪም የሱዳን ሕዝብ መንግሥቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያበላሽ በሚችል መልኩ ሦስተኛ ወገን ፍላጎት መጠቀሚያ እየሆነ እንዳለ እንዲያጣራም ጥሪ አቅርቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የድንበር አለመግባባት አንጻር ሱዳን እየተከተለችው ያለውን ችግሩን አባባሽ ጸብ አጫሪ እርምጃን በጽኑ አውግዞታል።
ኢትዮጵያ የትኛውም ግጭት የሁለቱን አገራት ደኅንነት የሚጎዳና ከባድ ጉዳትን የሚያስከትል መሆኑን እንደምትገነዘብ የጠቆመው መግለጫ፤ በሱዳን መንግሥት ወታደራዊ ክንፍ እየተበረታታ ያለው ግጭት "በሱዳን ሕዝብ ኪሳራ የሦስተኛ ወገንን ፍላጎት የሚያስፈጽም ነው" ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው በዚህ ጠንካራ መግለጫው ላይ የድንበር ጥያቄው ሊስተናገድባቸው የሚችሉ በቂ መንገዶች ቢኖሩም "የሱዳን ሠራዊት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል" ብሏል።
መግለጫው ጨምሮም በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የትብብርና የወዳጅነት መንፈስ በተቃራኒ "የሱዳን ሠራዊት ንብረቶችን ዘርፏል፣ ካምፖችን አቃጥሏል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በማጥቃት እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን ባዷቸውን የነበሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ካምፖችን ተቆጣጥሯል" ሲል ከሷል።
ባለፈው ሳምንት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሠራዊት በአንዳንድ የድንበር አካባቢዎች ላይ ጥቃት ፈጽሞ ወረራ አካሂዷል ሲል መክሱ ይታወሳል።
ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ ሱዳን በመሬት ላይ እየተከሰተ ያለውን ሐቅ በመካድ የተሳሳተ መረጃ እያሰራጨች ነው በማለት፤ እራሷን ከፈጸመችው ወረራ በተቃራኒው ወረራ እንደተፈጸመባት እየገለጸች ነው ብሏል። "ይህም የጸብ አጫሪነት ድርጊቷንና ተጨማሪ ግዛቶችን ለመያዝ የምታደርገውን ሙከራ ለመሸፋፈን" እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ባሉ አማራጮች ሁሉ ለችግሩ ሠላማዊ መፍትሔ እንዲገኝለት እንደመትፈልግ የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ "በሱዳን ሠራዊት በኩል ወዳጅ የሆነውን የኢትዮጵያንና የሱዳንን ሕዝብ ወዳልተፈለገ ጦርነት ለመግፋት የሚደረገው ሙከራ የአገራቱንና የአካባቢውን ሠላም፣ መረጋጋትና ልማት ያስተጓጉለዋል" ብሏል።
ሱዳን ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ለረጅም ጊዜ ይገባኛል ስትላቸው የነበሩትን በርካታ የድንበር አካባቢዎችን ሠራዊቷን በማሰማራት የተቆጣጠረች ሲሆን፤ ባለስልጣናቷም በቁጥጥራቸው ስር ያስገቡት ሕጋዊ ግዛታቸው መሆኑን በመግለጽ ይዞታቸውን ሲያጠናክሩ ቆይተዋል።
የሱዳንን እርምጃ ተከትሎ ኢትዮጵያ የድንበር አካባቢው ይዞታ ወደነበረበት እንዲመለስና ሁለቱ አገራት ችግሩን ቀደም ሲል ጀምረውት በነበረው የድንበር ኮሚሽን በኩል በውይይት እንዲፈቱት በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል።
ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሁለት አገሮችን እያወዛገበ የሚገኘው ድንበር፤ አልፋሽቃ፣ ከፍ ያለ የእርሻ ልማትና ተያያዥ ኢንቨስትመንቶች ይካሄዱበታል።
ባለፈው ሳምንት እሁድ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሠራዊት ድንበር አቋርጦ ወረራ ፈጽሞብኛል ማለቱን የአገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።
አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት በድንበሩ አካባቢ ያለው የሁለቱም ወገን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እየጨመረ በመሄዱ አገራቱ ውዝግቡን ከዚህ በፊት በጀመሩት የውይይት መንገድ መፍታት ካልቻሉ ውጥረቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመራ ተሰግቷል።
በዚህ ሳምንትም ሱዳን በአዲስ አበባ የሚገኙትን ዲፕሎማቷን "ለምክክር" በሚል መጥራቷን የተለያዩ የዜና ምንጮች የዘገቡ ሲሆን ጥሪው ከድንበሩ ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑ ግን አልተረጋገጠም።
የሱዳን መንግሥት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳባቸውን የአል ፋሽቃ አካባቢን የተቆጣጠረው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በትግራይ ወደ ተቀሰቀሰው ግጭት መሰማራቱን ተከትሎ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው በዚህ መግለጫ የኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በውይይት ይፈታ ዘንድ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጿል።
ሁለቱም አገራት ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ቢሆንም ኢትዮጵያ የድንበሩን ጉዳይ በንግግር ለመፍታት የሱዳን ጦር ቀድሞ ወደ ነበረበት ስፍራ መመለስ አለበት ስትል፣ ሱዳን ደግሞ ሠራዊቷ ከያዛቸው ቦታዎች እንደማይወጣ በተደጋጋሚ ገልጻለች።
የኢትዮጰያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ወዳጅ የሆኑትን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ሕዝቦች ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ለማስገባት በሱዳን ጦር እየተደረገ ያለው ሙከራ የሁለቱን አገራት እንዲሁም በአጠቃላይ የቀጠናውን ሰላም፣ መረጋጋት እና እድገት የሚሸረሽር ከባድ ስህተት ነው ሲልም አስቀምጧል።
የአፍሪካ አገራት የሱዳን መንግሥት የድንበሩን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ጥልቅ ግንዛቤ ላለው እንዲሁም ከፍተኛ ትዕግስት ላሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢፌዴሪ መንግሥት ምስጋና አቅርቧል።
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጋሩት ድንበር ርዝመት 750 ኪሎ ሜትር ያካልላል። ነገር ግን ይህ ድንበር አብዛኛው ርቀት ግልጽ በሆነ መንገድ መሬት ላይ አልተመላከተም።
ይህን ለማሳካት ተደጋጋሚ ንግግሮች ተጀምረው በተደጋጋሚ ተቋርጠዋል።
የአልፋሽቃ ማዕዘን
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የምትወዛገብብት አካባቢ ረዥም የግዛት ድንበር ነው ያላት። ሁለቱም አገሮች ለም ነው የሚባለውን ፋሽቃ አካባቢን እጅጉኑ ይፈልጉታል።
ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።
በዚህ ድንበር ሁለቱም አቅጣጫ የሚገኙ ገበሬዎች ባሻገራቸው ያሉ ለም መሬቶች ላይ ያማትራሉ። አልፋሽቃ ማዕዘን በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን ምሥራቃዊ ገዳሪፍ የሚገኝ ለም መሬት ነው።
አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞችም በቅርብ ይገኛሉ።
የሱዳን ባለሥልጣናት አልፋሽቃ የሱዳን ግዛት ነው ይላሉ። አሁን በኢትዮጵያን እጅ ለምን ሆነ ሲባሉ፣ "የሱዳን መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ባለው የትብብርና የመግባባት ስምምነት መንፈስ ነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ቦታውን አሁን እያለሙት ያሉት" ይላሉ።
ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር በድጋሚ ለማስመር፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
ቀደም ካለው አስተዳደር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሬው ሕዝብ ሉአላዊ መሬቱን ቆርሶ እየሰጠ ነው በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ነው የቆየው።
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ቀን እንዲያሳውቁ መመርያ አስተላልፈውላቸው ነበር።
ሆኖም አወዛጋቢውን ድንበር መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ እስከዛሬም አልተሳካም፡፡















