ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ ገለጸች

ሌፍተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሌፍተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን

የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሌፍተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን ሱዳን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌላ ጎረቤት አገር ጋር ጦርነት ወስጥ መግባት እንደማትፈልግ ነገር ግን ስንዝር መሬት እንደማትሰጥ ገለጹ።

የሱዳን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ሌፍተናንት ጀነራል አል ቡርሐን ይህንን የተናገሩት ከአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ሲሆን፤ ጨምረውም አገራቸው ሕጋዊ መብቷን በሚያስከብር መንገድ አሁን በሱዳን ሠራዊት የተያዙት ቦታዎች በይዞታዋ ውስጥ ከሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሱዳን ሠራዊት የተሰማራበት አካባቢ የአገሪቱ ግዛት መሆኑን ያመለከቱት ጀነራሉ ጦር ሠራዊታቸው ይህንን እርምጃ የወሰደው በሱዳን መንግሥት ውስጥ ካለው ፖለቲካዊ አካል ጋር በተደረገ ሙሉ ቅንጅት መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት መንግሥታቸው ከሱዳን ጋር ያጋጠመውን የድንበር ችግር በሰላም መፍታት እንጂ ወደ ጦርነት መግባት ፍላጎት እንደሌለው አመላክተዋል።

ጨምረውም በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል በቅርቡ የተከሰተውን የድንበር ላይ ወታደራዊ ፍጥጫን በተመለከተ በቅርቡ በሁለቱ አገራት ወታደራዊ ተቋማት ደረጃ ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን ገልጸዋል።

ጀነራል ብርሃኑ ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደም በድንበር አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላም ሲፈቱ መቆየታቸውን ገልጸው የአሁኑ ግን በክስተቱ ውስጥ "የሦስተኛ ወገን እጅ ስላለበት ችግሩ ጎላ ብሎ ወጥቷል" ሲሉ በስም ያልጠቀሱት ወገን በጉዳዩ ውስጥ አለ ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ "የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ ገብቷል" ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ይህ ድርጊት ሁለቱ አገራት ካለቸው ወዳጅነት አንጻር "ከሱዳን የማይጠበቅ አሳዛኝ ተግባር ነው" በማለት ገልፀውታል።

አክለውም የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ ከመግባቱ ጀርባ የግድቡን ድርድርና ግንባታ ማስተጓጎልን ያለመ በስም ያልጠቀሱት ሶስተኛ አካል መኖሩን ለኢዜአ ተናግረዋል።

"ሱዳን በሦስተኛ ወገን የተደገሰላትን የጦርነት ወጥመድ ወደ ጎን በመተው" የድንበሩን ጉዳይ በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ብርሃኑ ጁላ አፅንኦት በመስጠት መልዕክታቸውን አስተልፈዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን 750 ኪሊ ሜትሮች ያህል የጋራ ድንበር ሲኖራቸው፣ ለዓመታት በድንበር አካባቢ ግጭት ሲያጋጥም ነበር።

በተለይ አል ፋሽቃ በሚባለው ለም የእርሻ መሬት ባለበት አካባቢ ግጭቶች በተለያዩ ጊዜያት መከሰታቸው ይነገራል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሱዳን ባለስልጣናት እንደከሰሱት በአካባቢው የኢትዮጵያ ኃይሎች ባካሄዱት ጥቃት አንዲት ሴትና ህጻንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

በድንበር አካካቢ ተከስቶ ሳምንታት ያስቆጠረው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሆን፣ በሠላማዊ ሰዎችና በወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

ውጥረቱን ለማርገብ በሁለቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትርና በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካይነት ንግግር ቢደረግም እስካሁን ለቀውሱ መፍትሄ አላስገኘም።

የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታት ከድንበር ውዝግቡ ባሻገር ኢትዮጵያ ወደ ማጠናቀቁ እያደረሰችው ባለው ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብጽን ጨምሮ እያደረጉት የነበረው ድርድር በሱዳን ቅሬታ ምክንያት ወደፊት መራመድ ሳይችል መቋረጡ ተገልጿል።