እየተካረረ የመጣው የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ፍጥጫ

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN PM OFFICE
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተቀሰቀሰው የድንበር ይገባኛል ውጥረት፣ወታደራዊ እንቅስቃሴን አስከትሎ ይፋዊ መወነጃጀል መሰማት ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
የሱዳን ወታደሮች ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባቸውን የእርሻ መሬቶችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጉዳዩን አለዝባ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን ፍላጎት በመግለጫዎች ብታሳውቅም ነገሮች እየተጠናከሩና እየተባባሱ በመምጣት ላይ ናቸው።
እርምጃው የሱዳን መንግሥት ፍላጎት ሳይሆን በድንበር አካባቢ ያሉ የሱዳኑ ግዛት አስተዳዳሪዎችና ወታደራዊ መኮንኖች የተናጠል ድርጊት በመሆኑ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በመነጋገር ሠላማዊ መፍትሔ ይገኝለታል በማለት ገልጻ ነበር።
ነገር ግን የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት የአገራቸው ሠራዊት ግዛቴ ነው ከሚላቸው ቦታዎች ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠሩንና ይህም የማይቀለበስ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የሱዳን ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ጥሶ በመግባት የእርሻ ቦታዎችን ወርሮ እንደያዘና ንብረት እንደዘረፈ ገልጿል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ወረራው የድንበር ላይ ውጥረቱን እንዳባባሰው በማመልከት ችግሩን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ሱዳን በበኩሏ ባወጣችው መግለጫ የኢትዮጵያ ታጣቂዎች በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል አል ቁራይሻ ውስጥ 'የኢትዮጵያ ታጣቂዎች ወረራ' ያለችውን ፈጽመዋል ስትል አውግዛለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አማራ ክልል በኩል የገቡ የታጠቁ ቡድኖች ፈጸሙት ያለውን ጥቃት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ በመግባት እንዲያወግዘው ጠይቋል።
የሌሎች አገራት ጥረት
ጉዳዩ ያሳሰባት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የድንበር ላይ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድና በንግግር እንዲፈቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ ጠይቃለች።
ከሁለቱም አገራት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት አረብ ኤምሬቶች ችግሩን ሊያባብስ ከሚችሉ ነገሮች በመቆጠብ ለሕዝቦቻቸውና ለአካባቢው ሠላምና ብልጽግና በሚያግዝ መልኩ መፍትሄ እንዲፈልጉ ለአገራቱ ጥሪ አቅርባለች።
ከዚህ ባሻገር የሁለቱ አገራት ወዳጅ የሆነችው ኤርትራ ባለፈው ሳምንት ባለሥልጣናቷን ወደ ካርቱም በላከችበትና የሱዳን ባለሥልጣናት ወደ አስመራ በመጡበት ጊዜ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር አለመግባባት ጉዳይ ተነስቶ መወያየታቸው ተዘግቧል።

ወቅታዊ ሁኔታ
የሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪና ነዋሪዎች የሱዳን ሠራዊት ወረራ ፈጽሞበታል ወደ ሚባሉት ስፍራዎች ዘልቆ መግባት የጀመረው በአካባቢው የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ በጥቅምት 29/2013 ዓ.ም እንደሆነ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአካባቢው በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩትና በሱዳን ሠራዊት ወረራ ማሳቸውን ትተው ወደ መተማ የሸሹት አቶ ከሰተ ውበቱ እንደገለጹት "ወታደሮቹ ድንበር አልፈው ከገቡ በኋላ ወደ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች በመግባት ማንኛውንም የሰው እንቅስቃሴ በተመለከቱ ቁጥር ተኩስ ይከፍታሉ።"
በድንበር አካባቢ ወታደራዊ ግጭት እንዳጋጠመ ቢነገርም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ፍጥጫ ባለበት የድንበር አካባቢ አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች፣ አልፎ አልፎ ከባድ ተኩስ እንደሚሰማ፤ በሁለቱ ሠራዊት መካከል ግጭት ተከስቷል ለማለት የሚያስችል ሁኔታ እንዳልተመለከቱና እንዳልሰሙ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ ያን ያክል የተጋነነ ባይሆንም ወደ ድንበር አካባቢ የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት አልፎ አልፎ ሲንቀሳቀስ እንደሚታይ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አንድ የአካባቢው የጸጥታ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቀናት በፊት በተለይ ከመተማ ወደ ምዕራብ አርማጭሆና ሁመራ የሚወስደውን መንገድ ለመዝጋት የሱዳን ሠራዊት ሙከራ አድርጎ እንደነበር፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በቦታው በመድረሱ ገፍተው ለመሄድ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በድንበር አካባቢ ስላለው ወታደራዊ እንቅስቃሴን በተመለከተ በአካባቢ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሠራዊት አመራሮች መካከል አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ "በሥፍራው የተለየ የሠራዊት እንቅስቃሴ የለም ብለዋል። በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ኃይል ግን ከስፍራ ስፍራ ስለሚዘዋወር ምናልባት ያንን እንቅስቃሴ የተመለከቱ ሰዎች ተጨማሪ ኃይል እየተንቀሳቀሰ ነው ብለው አስበው ይሆናል" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎች በድንበር አካካቢ ይሰማል ስላሉት ተኩስ የተጠየቁት የሠራዊቱ አመራር፤ በተደጋጋሚ የሱዳን ወታደሮች ተኩስ እንደሚከፍቱ አረጋግጠው "ተኩሱ ግን በአብዛኛው እንዲሁ ተራራ ላይ የሚቀርና የእርሻ ሠራተኞች ወደ እነሱ እንዳይቀርቡ ለማስፈራራት ነው" ሲሉ በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት ኖሮ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ጨምረውም አስካሁን በድንበር አካባቢ በተከሰተው ፍጥጫ ምክንያት በሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያመለክት ዝርዝርና ሙሉ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት ከሚያጋጥመው "በተለየ መልኩ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ከሌሎች ሰዎች መስማታቸውን" ገልጸዋል።
"ትዕግስትም ልክ አለው"
በድንበር አካባቢ ያለውን አለመግባባት በተመለከተ ጉዳዩ በሁለቱ አገራት መንግሥታት አማካይነት በሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታና ለዚህም ጥረት እያደረገች እንደሆነ ስትገልጽ የነበረችው ኢትዮጵያ ከሱዳን ሠራዊት በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዳሳሰባት ገልጻለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት በድንበር አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየበረታ መጥቷል።
ከሁለት ወር በፊት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት በመጠቀም የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ መግባቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ አሁን ደግሞ "የሱዳን ወታደራዊ ኃይል በድንበር አካባቢ ወደ ተጨማሪ ቦታዎች ዘልቆ ለመግባት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" ሲሉ ከስሰዋል።
ችግሩን በትዕግስትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር "ፍርሃት ወይም መወላወል አይደለም" ያሉት አምባሳደር ዲና፣ አካባቢውን ከግጭት ለመጠበቅ ሲባል ኢትዮጵያ ጉዳዮች እንዳይካረሩ ለማድረግ እየጣረች ቢሆንም ይህ ታጋሽነት ገደብ እንዳለው አመልክተዋል።
የቆየ የድንበር ውዝግብ
ሁለቱ አገራት 750 ኪሊ ሜትሮች ያህል የጋራ ድንበር ሲኖራቸው፣ ለዓመታት በድንበር አካባቢ ግጭት ሲያጋጥም ነበር። በተለይ አል ፋሽቃ በሚባለው ለም የእርሻ መሬት ባለበት አካባቢ ግጭቶች በተለያዩ ጊዜያት መከሰታቸው ይነገራል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሱዳን ባለስልጣናት እንደከሰሱት በአካባቢው የኢትዮጵያ ኃይሎች ባካሄዱት ጥቃት አንዲት ሴትና ህጻንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
በድንበር አካካቢ ተከስቶ ሳምንታት ያስቆጠረው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሆን፣ በሠላማዊ ሰዎችና በወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
ውጥረቱን ለማርገብ በሁለቱ አራት ጠቅላይ ሚኒስትርና በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካይነት ንግግር ቢደረግም እስካሁን ለቀውሱ መፍትሄ አላስገኘም።
የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታት ከድንበር ውዝግቡ ባሻገር ኢትዮጵያ ወደ ማጠናቀቁ እያደረሰችው ባለው ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብጽን ጨምሮ እያደረጉት የነበረው ድርድር በሱዳን ቅሬታ ምክንያት ወደፊት መራመድ ሳይችል መቋረጡ ተገልጿል።















