"ሱዳን በድንበር አካባቢ በተጠናከረ ሁኔታ ጦሯን እያንቀሳቀሰች ነው" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የፎቶው ባለመብት, MFA
በአወዛጋቢው የድንበር አካባቢ ሱዳን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ መቀጠሏን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ [ማክሰኞ] አዲስ አበባ ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ሱዳን በድንበር አካባቢ በተጠናከረ ሁኔታ ጦሯን እያንቀሳቀሰች ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
አምባሳደር ዲና ጨምረውም ኢትዮጵያ ለሠላምና ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ቅድሚያ እንደምትሰጥ አመልክተው የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ መግባቱንና እየፈጸማቸው ያሉ "ሕገወጥ እንቅሰቃሴዎችን መታገሷ ከፍርሃትና ከመወላወል ጋር የተገናኘ አይደለም" ብለዋል።
በፌደራል መንግሥትና በህወሓት ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የሱዳን ጦር የኢትያጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት መሬት መያዙን ኢትዮጵያና ሱዳን ከዚህ ቀደም የነበራቸውን መልካም ግንኙነት እንዲሻክር የሚያደርግ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ አመልክቶ ነበር።
ይህንን እርምጃ የሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር ወታደሮቻቸው በሁለቱ አገራት አዋሳኝ የድንበር አካባቢ በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ተይዞ የቆየ ካሉት መሬት ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠራቸውን ለሮይተርስ ዜና ወኪል መግለጻቸው ይታወሳል።
የማስታወቂያ ሚንስትሩ ፋይሳል ሳሊህ "ሠራዊታችን መሬታችንን ለማስመለስ ኃላፊነቱን ይወጣል። በዚህም በአሁኑ ጊዜ ከ60 አስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሱዳን መሬትን መልሶ ይዟል" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።
በሱዳን ሠራዊት በድንበር አካባቢ የሚካሄደው እንቅስቃሴ መቀጠሉን አምባሳደር ዲና ያረጋገጡ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት ቢቢሲ ያናገራቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደተናገሩት በድንበሩ አካባቢ የሡዳን ሠራዊት በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና የከባድ መሣሪያ ተኩስም በተደጋጋሚ እንደሚሰማ ተናግረው ነበር።
ሱዳን በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ ሱዳን ሠራዊቷን አሰማርታ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደር ኢትዮጵያውያንን ከአካባቢው ማስወጣት የጀመረችው ከሳምንታት በፊት ነበር።
ወታደራዊ ግጭት ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ እንደማይሆንና አገሪቱ "ጦርነት ትርፍ እንደሌለው ትረዳለች" ያሉት ቃል አቀባዩ ሁለቱ አገራት በድንበር ሰበብ ወደ ግጭት እንዲገቡ በማድረግ "የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ የሦስተኛ ወገኖች ፍላጎት አለ" በማለት የዲፕሎማሲ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተከሰተው የድንበር አለመግባባት በሰላማዊ መንግድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት መሆኑንና ለዚህም ድንበሩ ወደ ቀደመ ቦታው ተመልሶ ችግሩ በሰላም መፈታት አስፈላጊነት ላይ የመንግሥታቸው አቋም ጽኑ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ቀደም ሲል የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባላት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ ማመላከታቸው ይታወሳል።
ሱዳን በበኩሏ አሁን በሠራዊቷ ቁጥጥር ስር የገቡት የድንበር አካባቢዎች ሕጋዊ ይዞታዋ እንደሆኑ ባለስልጣናቷ ለመገናና ብዙሃን መግለጻቸው አይዘነጋም።
የሱዳን ወታደሮች በድንበር አካባቢ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ወደሚኖሩበት አካባቢ ከተንቀሳቀሱ በኋላ በእርሻ ልማቶች ላይ በወሰዱት እርምጃ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጣ ምርትና ንብረት የወደመባቸውና አካባቢውን ለቀው ለመውጣት እንደተገደዱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ቢያንስ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ሁለቱ መሞታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከሳምንት በፊት ለቢበሲ ከመናገራቸው በተጨማሪ ከ1700 በላይ ሰዎች ከድንበሩ አካባቢ ሲፈናቀሉ ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት መውደሙንም አመልክተዋል።
የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት የድንበር አካባቢው ችግር መከሰቱን ተከትሎ በአዲስ አበባና በካርቱም ውስጥ ውይይት ቢያደርጉም ምንም አይነት መፍትሄ የሚሰጥ ነገር አልታየም።
ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት አካባቢ ያልተቋጨ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ያለ ሲሆን፤ በተለያዩ ጊዜም በድንበር አካባቢ ግጭቶች እንደሚከሰቱ ሲዘገብ ቆይቷል።
የሁለቱ አገራት መንግሥታትም ለረዥም ጊዜ ለቆየው ለዚህ የድንበር ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት በሚል የጋራ የድንበር ኮሚሽን አዋቅረው ተከታታይ ውይይቶችን ቢያደርጉም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ሳይደርስ እስካሁን ዘልቋል።















