ሱዳን፡ "ድንበሩ ወደ ቀደመ ቦታው ተመልሶ ችግሩ በሰላም መፈታት አለበት" የኢትዮጵያ መንግሥት

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የፎቶው ባለመብት, MFA

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተከሰተው የድንበር አለመግባባት በሰላማዊ መንግድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ ገለፁ።

በፌደራል መንግሥትና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ግጭት ተከትሎ የሱዳን ጦር የኢትያጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት መሬት መያዙን ኢትዮጵያና ሱዳን ከዚህ ቀደም የነበራቸውን መልካም ግንኙነት እንዲሻክር ያደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽን አባላት ሰሞኑን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ቃል አቀባዩ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያን መሬት መያዛቸውና በገበሬዎች ላይ ችግር ማድረሳቸው "የሱዳን መንግሥት ፍላጎት አይደለም" ይላሉ።

በዚህ አለመግባባት ውስጥ ጥቂት የሱዳን ከፍተኛ አመራሮች ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል ተናግረው፤ በአብዛኛው ግን ከድርጊቱ "ከጀርባ ሌላ አካል አለ" ብለዋል።

"ከሕግ ውጪ ይህንን ጉዳይ የሚገፉ አሉ ብለን እናምናለን፤ ከኋላ በመሆን በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮቿ መካከል አለመግባበት እንዲፈጠር የሚሰሩ አሉ" የሚሉት አምባሳደር ዲና እነዚ ከጀርባ አሉ የሚሏቸው አካላት እነማን እንደሆኑ ግን ሳይገልጹ አልፈዋል።

ኢትዮጵያና ሱዳን እስካሁን ድረስ ተግባብተውበት የቆዩት ድንበር እኤአ 1902 በተካሄደው ስምምነት መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደር ዲና፤ በፈረንጆቹ 1972 ሁለቱ መንግሥታት ይህንን ድንበር በሕጋዊ መንገድ ለማስመር ቢግባቡም እስከዛሬ ድረስ ሳይፈፀም ቆይቷል ብለዋል።

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚሽንም በመግለጫው ሁለቱ አገራት በፈረንጆቹ 1972 ለድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን አመልክቷል።

በስምምነቱ መሰረት አገራቱ በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ እስከሚያስቀምጡ ድረስ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ያስገድዳል እንደሚያስገድድ የድንበር ኮሚሽኑ አባል አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ አብራርተዋል።

ሆኖም ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በመግባት የያዘችው መሬት ይህንን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በትግራይ ክልል ባለፈው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የወሰደውን እርምጃ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን መሬት በመያዝ ገበሬዎች ላይ ጥቃት በማድረስ የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

"ይህ ድርጊት ሕገወጥ ነው፤ ሁለቱ አገራት ለረዥም ዓመታት ከነበራቸው መልካም ግንኙነት ተቃራኒ ነው በማለት ከሱዳን መንግሥት ጋር በመወያየት ላይ እንገኛለን" ብለዋል አምባሳደር ዲና።

በመንግሥታቸው ውስጥ ይህንን ችግር በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ የኢትዮጵያን መሬት ለመያዝ የሚደረገው ድርጊት ትክክል አይደለም በማለት ነግረናቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ወታደሮች ከሕግ ውጪ የያዙትን መሬት ለቅቀው የተፈጠረውን የድንበር አለመግባባት በሰላማዊ መንግድ ለመፍታት ያቀረበችውን ሀሳብ ሱዳን አለመቀበሏን አንዳንድ የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ይህ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የውይይት ሃሳብ ተቀባይነት አላገኘም መባሉን አስመልክቶ ሲናገሩም "እምቢ እያሉ ያሉት የሱዳንን ሕዝብ ፍላጎት የሚያገለግሉ አይደሉም። ሱዳንን የሚጎዳ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

ሱዳን በተቆጣጠረቻቸው የኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች፣ በአሁኑ ሰዓት ግጭት ስለመኖር አለመኖሩ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና ሲመልሱ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ሙሌትና ቀጣይ ሥራ ላይ ሰኞ በተካሄደው የሦስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ቅሬታ እንዳላት የሱዳን ዜና አገልግሎት ሱና የአገሪቱን መስኖና ውሃ ሀብት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።

ሱዳን ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ለአንድ ወር ያህል ተቋርጦ የነበረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ባለፈው እሁድ ተጀምሮ በተካሄደበት ጊዜ የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያና ሱዳን ሲቀበሉት ግብጽ ሳትቀበለው እንደቀረች ተገልጾ ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ እንደገለጹት ውይይቱን በመጪው ቅዳሜ ለመቀጠል ቀጠሮ ተይዟል።