"ሱዳን ድንበራችንን አልፋ እንድትገባ የተደረሰ ስምምነት የለም" የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የፎቶው ባለመብት, MFA

ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ እንድትጠብቅም ሆነ መሬት እንድትይዝ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጥር 12/ 2013 ዓ. ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

መንግሥት ህግ ማስከበር በሚለው ወታደራዊ ዘመቻ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባቀናበት ወቅት ድንበር አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን በተመለከተ ከሱዳን ጋር መግባባት ተደርሶ ነበር ብለዋል።

"ድንበር አካባቢ የሁለቱን አገሮች ደህንነት የሚጎዳ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በኛ አመራር ለሱዳን መንግሥት አደራ ተሰጥቷል" ያሉት ቃለ አቀባዩ አክለውም ሆኖም "ድንበሩን አልፈው አገራችን ግቡ መሬት ይዛችሁ ጠብቁልን የሚል አይነት ሊኖር የሚችል አይደለም፤ አልነበረም" ብለዋል።

ከሰሞኑ የሱዳን ምክር ቤት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ሱዳን ሰራዊቷን ወደ ድንበር ያስጠጋችው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ አህመድ ጥያቄና ፈቃድ ነው መባሉ ተዘግቧል።

ለዚህም ምላሽ የሰጡት ቃለ አቀባዩ "ቅዠት ነው" ካሉ በኋላም "አጥፊ ኃይሎች የናንተን ድንበር ተጠቅመው ወደኛ ድንበር እንዳይገቡ ማለት ኑና ገብታችሁ ጭራሽ ያልተከለለና መቶ አመት በዚሁ ሁኔታ ይሁን ተብሎ የቆየውን መሬት ድንበር የኛ ነው በሉ ማለትም አይደለም" ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በአመራር ደረጃ የተደረሰ ስምምነት እንዳለ መነገሩ ስህተት ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ይገባናል ውጥረት እየተጋጋለ ነው በተባለበት ወቅትም የመንግሥታቸውን አቋም ያስረዱት አምባሳደር ዲና፤ ሱዳን በትግራይ ክልል ግጭት ከተነሳበት ከሶስት ቀናት በኋላ፣ ከጥቅምት 27፣ 2013 ዓ.ም ያላግባብ የያዘችውን መሬት ትልቀቅና ወደ ንግግር እንግባ የሚል ነው።

የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት የአገራቸው ሠራዊት ግዛቴ ነው ከሚላቸው ቦታዎች ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠሩንና ይህም የማይቀለበስ እርምጃ መሆኑን መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

ሁለቱን አገራትን በተመለከተም የድንበር፣ የቴክኒክና ከፍተኛ ኮሚሽኖች ያሉ ሲሆን በየጊዜው ውይይቶችም ሲደረጉ እንደነበር አንስተዋል።

ሁለቱን አገራት ለማስታረቅና ለማሸማገል የተለያዩ አካላትም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የጠቀሱት አምባሳደር ዲና "አገሮቹን እናደንቃቸዋለን፤ ይኸንን ያሰቡትን ጥሩ ነው እንላለን። ነገር ግን እኛ እኮ እምቢ አላልንም። እንነጋገር ነው እያልን ነው ያለነው። ያስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ ግን ወደነበራችሁበት ተመለሱና እንነጋገር የሚል ነው" ብለዋል።

ጉዳዩ ያሳሰባት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የድንበር ላይ ውዝግብ በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ ጠይቃለች።

ቃለ አቀባዩ በመግለጫቸው ወቅት አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሱዳን የያዘችውን መሬት እንድትለቅ ኢትዮጵያ በቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧንና ይህ ከተሳካ ሁለቱ አገራት በዋናነትም ችግራቸውን ተነጋግረው መፍታት እንደሚችሉም አስረድተዋል።

የሱዳንና የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ምጣኔ ኃብት፣ ባህላዊና የህዝቦች ትስስርና ቁርኝት በመጥቀስም አገራቱ ወደ ግጭት ቢገቡም የሁለቱም ህዝቦች እንደሚጎዱ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በታሪካቸውም እንዲሁ ከመደጋገፍና ከመረዳዳት በስተቀር ይህ ነው የሚባል ግጭት ተከስቶ እንደማያውቅ የተናገሩት አምባሳደር ዲና በተለይም በሰላም ጥበቃ፣ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላቸውን ግጭት ለመፍታትና በአጠቃላይ የሱዳንና ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ተጫውታለች ብለዋል።

የህዝቦቹን ቁርኝትና የአገራቱንም እጣ ፈንታ አንድ መሆኑን አፅንኦት በመስጠትም አሁን ሱዳን እያደረገችው ያለችው ከህዝቡ የመነጨ አይደለም ይላሉ።

"የሁለቱ አገራት ጥቅም ይተሳሰራል ስንል ግጭቱ ሁለቱንም አገራት እንደሚጎዳ እናውቃለን። ነገር ግን ሁለቱን አገሮች አባልቶ የራሳቸውን ጥቅም በመሃል መፍጠር የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ እናቃለን።" ብለዋል።

ቃለ አቀባዩ ሶስተኛ ወገን የሚሉትን አካል ባይጠቅሱም ሁለቱን አገራት በማበጣበጥ የሚጠቀሙ ኃይሎች አሉ በማለት የተናገሩ ሲሆን ግጭቱ የሱዳን ፍላጎት አይደለም ብለዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግሥት "አጥፊ ኃይሎች" ያላቸው አካላት በሱዳን ድንበር በኩል እንዳይገቡ ሲል አገራቱ ካላቸው ትስስር አንፃር እምነት በመጣል እንደሆነም ጠቆም አድርገዋል።

"የፌደራሉ መንግሥት እምነት በሱዳን አለው እንጂ ከኋላ ይወጉናል የሚል እሳቤ በኢትዮጵያ በኩል እንዳልነበረ ነው። እንዲህ አይነት ተግባር ከጀርባ ይፈፅማሉ ብለንም ከኢትዮጵያ በጭራሽ ግምት አልነበረም። ያየነው ግን ተቃራኒውን ነው" ብለዋል።

ስለ ኤርትራሶማሊያ ሰራዊት

በዚሁ መግለጫ ላይ ትግራይ ላይ በተደረገው ወታደራዊ ግጭት የኤርትራ ሰራዊት ተሳትፏል ስለመባሉም ምላሽ ሰጥተዋል። ሁኔታውንም "ፕሮፓንዳና መሰረተ ቢስ ነው" ብለውታል።

ከኤርትራም በተጨማሪ የሶማሊያ ሰራዊት ተሳትፏል መባሉን ሃሰት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገሩን ዳር ድንበር ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሶማሊያ፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲና፣ ኮንጎ "ትልቅ ገድል የሰራ ኃይል ነው" በማለትም የሰራዊቱን ጥንካሬ አስረድተዋል።

"የውስጥ የህግ በላይነትን ለማስከበር ማንንም አገር የሚጠራ አይደለም፤ የሚጠራም አገር የለም፤ ሊጠራም አይችልም፤ አይገባም፤ አይፈልግምም፤ አስፈላጊም አልነበረም" በማለት አፅንኦት በመስጠትም ነው የተናገሩት።

ቢቢሲ ያናገራቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች፣ አዲስ የተሾሙት የመቀሌ ከንቲባም ሆኑ፣ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች አካላት የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸውን ቢናገሩም አምባሳደሩ በበኩላቸው ግጭቱን ቀጠናዊ ለማድረግና ጣልቃ ገብነትን ለመጋበዝ የተቃጣ ነው ብለውታል።

ወደ አስመራ የተወነጨፉት ሮኬቶችም ይህንኑ ለማገዝና የኤርትራ ሰራዊት እንዲገባ በሚል ታቅዶም ነው ብለዋል።

ነገር ግን ወደ ኤርትራ ሚሳይል ሲወነጨፍ አገራቱ ካላቸው ርቀት አንፃር የኤርትራ ሰራዊት ድንበር አካባቢ ድንበሩን ለማስከበር ሊታይ እንደሚችል ጠቁመዋል።

"ይህንን ወስዶ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እየተዋጉ ነው ማለት ስህተት ነው። የኤርትራም የሶማሊያም ሌላ ኃይል አልነበረም። ብቃት አለው በራሱ ነው የጨረሰው" ብለዋል።

ነገር ግን የአውሮፓ ሕብረት በከፍተኛ ዲፕሎማቱ ጆሴፕ ቦሬል በሰጠው መግለጫ " ግጭቱ ወደ ቀጠናዊ ወደ መሆን የመሸጋገር እድል አለው፣ ለምሳሌ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ግጭት ውስጥ መሳተፋቸው፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸው" በማለት መጥቀሳቸው የሚታወስ ነው።

አምባሳደር ዲና በበኩላቸው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሚዲያውም ሆነ የምዕራቡ አለም ግጭቱን ቀጠናዊ ለማድረግ ሲሰሩ የነበሩ ኃይሎች ነበሩ ብለዋል።

በርካታ የጦር መሳሪያ አምራችና ሻጮች ጠመንጃ ከመሸጥ ጀምሮ እንዲሁም ግጭቶችን ሰበብ በማድረግ እርዳታ እስከማሰባሰብ ድረስ በአፍሪካ ከሚከሰቱ ጦርነቶች የሚጠቀሙ ኃይሎችም እንዲሁ ግጭቱ የቀጠናዊ መልክ እንዲኖረው ጥረዋል ብለዋል።

"ንግድ ስለሆነ በየሚዲያውም ቀጠናዊ ለማድረግ እያራገበ ይገኛል፤ የምዕራቡ አለም ከግጭቱ መጠቀም ለሚፈልጉ በርካታ አገራት እንዲበጣበጡ ይፈልጋሉ ያሉት ቃለ አቀባዩ "ግጭቱ ቀጠናዊ ሳይሆን ከሽፏል" በማለትም ያለውን ፖለቲካ አስረድተዋል።

ስለ ህዳሴ ግድቡ

ሌላኛው ከሶስትዮሽ ህዳሴ ግድቡ ጋር ተገናኝቶ የተናገሩት አምባሳደር ዲና በህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ተጠቃሚዋ ሱዳን ናት ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ መሰረት በተጣለበት ወቅት ከሶስቱ አገራት የተውጣጣ ነፃ አለም አቀፍ የባለሙያዎች ጉባኤ ቡድን ግድቡ በከባቢ፣ ምጣኔ ኃብትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚለውን አጥንቶ በግምገማው መሰረትም አይጎዳም የሚል ማጠቃለያ ላይ መድረሱንን አስታውሰዋል።

ሱዳን የህዳሴ ግድብ በደለልና በጎርፍ መጥለቅለቅን ከማስቀረት በተጨማሪ፣ ርካሽ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት፣ የዳበረ እርሻ እንዲሁም ደለል ለመጥረግ ከምታወጣው ወጪም እንደምታተርፍ ሱዳን ታውቃለች የሚሉት አምባሳደር ዲና፤ "የሚያነሷቸው ነገሮች የነሱ አይደሉም፤ ሌላ አካል ወክለው ነው እየሰሩ ያሉት" ይላሉ።

በኢትዮጵያ በኩል አሁንም የተቀየረ ነገር እንደሌለና ድርድሩም ሆነ ግንባታና ሙሌቱ ተያይⶋ ይቀጥላልም በማለት የመንግስታቸውን አቋም አስረድተዋል።