የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ እንዴት ሰነበተ?

ለዘመናት መቋጫ ሳያገኝ የቆየው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከኅዳር ወር መጀመሪያ ወዲህ ሱዳን ይዞታዬ ነው ወዳለቻቸው የድንበር አካቢዎች ወታደሮቿን ካሰማራችና ኢትዮጵያ የሱዳን ሠራዊት ድንበሬን ጥሶ ገብቷል ካለች በኋላ ውጥረቱ አይሏል።
ሁለቱም አገራት ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ የድንበሩን ጉዳይ በንግግር ለመፍታት እንደምትሻ ነገር ግን በአካባቢው ያለው ሁኔታ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ስትጠይቅ፤ ሱዳን ደግሞ ሠራዊቷ ከያዛቸው ቦታዎች እንደማይወጣ በተደጋጋሚ ገልጻለች።
የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ይዞታ ስር የነበሩ በርካታ ስፍራዎችን ሠራዊታቸው በቁጥጥር ስር ማስገባቱን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህ ሳቢያ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን በኢትዮጵያ በኩል መገለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣንት የሱዳን ኃይሎች ድንበር አልፈው ወረራ መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ እየገለጹ ባሉበት ሁኔታ ባለፈው እሁድ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሠራዊት ድንበር አቋርጦ ወረራ ፈጽሞብኛል ማለቱን የአገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።
አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት በድንበሩ አካባቢ ያለው የሁለቱም ወገን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት፣ እየጨመረ በመሄዱ አገራቱ ውዝግቡን ከዚህ በፊት በጀመሩት የውይይት መንገድ መፍታት ካልቻሉ ውጥረቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመራ ተሰግቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአወዛጋቢው የድንበር አካባቢ በአሁኑ ወቅት ስላለው እንቅስቃሴና አጠቃላይ ሁኔታ ለማወቅ ቢቢሲ በድንበሩ አቅራቢያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን አነጋግሯል።
በምዕራብ አርማጭሆ ምድረ ገነት ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌቱ ሙላት እንደሚሉት "የሱዳን ጦር አቦአጥርን ጨምሮ በኢትዮጵያ ድንበር ስር የነበሩ አካባቢዎችን በተለያዩ ጊዜያት በመውረር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ" ኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው መሰማራቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሱዳን ሠራዊት በድንበር አካባቢ መስፈሩን የሚጠቅሱት አቶ ጌቱ የኢትዮጵያ ሠራዊትም በአካባቢው እንዳለ ቢናገሩም በሁለቱ ወገኖች በኩል ጦርነት እንደሌለ ይናገራሉ።
"ውጊያ የለም እንጂ የወታደሮች እንቅስቃሴ አለ። ምንም ተኩስ የለም። ስጋትም የለም። ልዩ ኃይሉም ሆነ መከላከያው ሁሉም አንድ ላይ ነው በትብብር በአካባቢው ነው ያሉት" ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
አቶ ጌቱ እንደሚሉት የሱዳን ሠራዊት ወደ አካባቢው ዘልቆ መግባቱን ተከትሎ ከነበረው አንጻር ያለው ሁኔታ ሠላማዊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጨምረውም "[የሱዳን ኃይሎች] የወሰዱትን ወስደዋል። አሁን ግን ሠላም ነው። ጓንግ ወንዙን ሳይሻገሩ እንዳሉ አሉ። አቦጥር የሚባል ሰፊ በረሃ አለ። በረሃው እርሻ ነበር። እርሻው ላይ ነው የሚገኙት" ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳንን ከሚለየው ድንበር ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በመተማ ወረዳ የሽንፋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ በለጠ ዳምጤ ደግሞ፤ በአካባቢያቸው የጎላ ግጭት ባይኖርም የሱዳን ሠራዊት በሰፊው ወደ ድንበሩ ተጠግቶ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
"የሱዳንና የእኛ አካባቢ በፊትም የድንበሩ ዙሪያ ያልተለየ ስለነበረ ያንን መሠረት አድርጎ ሱዳን አጠቃላይ ከላይ ጀምሮ ኢትዮጵያን በሚያዋስነው አካባቢዎች ወታደሮችን አሰማርታ ነው ያለችው ሲሉ" ተናግረዋል።
ሠራዊቱ አልፎ አልፎ ወደ አካባቢው እንደሚገባ የተናገሩት አቶ በለጠ፤ በዚህም በስፍራው በግብርና ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶችን የማጉላላትና በአካባቢው አሰሳ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ ግጭት መከሰቱን የሚናገሩት አቶ በለጠ "መተማ ቁጥር 4 ደለሎ አካባቢ እንዲሁም ምዕራብ አርማጭሆ አካባቢዎች ነው ሰፋ ያለ ችግር ያለበት። ከታች ደግሞ ወደ ቋራ አካባቢ ነፍስ ገበያ በሚባለው አካባቢም አንድ ሁለት ጊዜ ከአርሶ አደሩ ጋር ግጭት ተፈጥሯል" ሲሉ አስረድተዋል።
በአካባቢያቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ አለመኖሩንም ጠቅሰው ነገር ግን "የአካባቢው አርሶ አደር ነው በሩን እየጠበቀ ያለው፤ ቁልፍ ቦታዎች ላይ እየተቀያየረ አርሶ አደሩ ግዛቱን እየጠበቀ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም አልፎ አልፎም ግጭት መኖሩን ጠቁመው፤ "በቋራ በነፍስ ገበያ ቁጥር 4 እና ቁጥር 2 በሚባሉ አካባቢዎች የሱዳን ጦር በተደጋጋሚ ሰርጎ በመግባት የእርሻ ባለሃብቶችን ንብረት መውሰድና ማቃጠል እንዳጋጠመ ገልጸዋል።
በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ይበልጣል አዕምሮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት "የሱዳን ኃይሎች ድንበር ጥሰው ፈጽመውታል ባሉት ወረራ" በንብረት እና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።
በድንበር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ለቢቢሲ እንደገለጹት ከፍተኛ መጠን ያለው የእርሻ ምርትና የግብርና መገልገያዎች ወድመዋል። አምባሳደሩም "ሱዳን በፈጸመችው ወረራ በግምት እስከ አንድ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ጉዳት አጋጥሟል" ብለዋል።
የሱዳን ጦር በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ምሽግ ከመቆፈር ባለፈ ሰዎችን ለማስፈር የመንገድ ጠረጋ እና መሠረተ ልማት ዝርጋት እየተከናወነ መሆኑን እንደሰሙ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም በድንበር አካባቢ ባሉ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ መኖሩን እንደሰሙም አመልክተዋል።
በሁለቱም አገራት በኩል የድንበሩን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ፍላጎት እንዳለ በተደጋጋሚ ቢገለጽም እስካሁን ይህንን የሚያመለክት እንቅስቃሴ በይፋ አልታየም።
አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ሱዳን በአውሮፓውያኑ 1972 በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን "የድንበር መርህ በጣሰ መልኩ ወረራ ፈጽማ ጉዳት አድርሳለች" ሲሉ ከስሰዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ፍላጎት እንዳላት አመልክተው "ይህ የማይሆን ከሆነ ራስን የመከላከል ሕጋዊ መብቷን ትጠቀማለች" ሲሉ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሱዳን ባለስልጣናት ሠራዊታቸው የወሰደው እርምጃ የአገሪቱን ይዞታ ማስመለስ መሆኑን በመግለጽ በቁጥጥራቸው ስር የገቡት አካባቢዎች ጉዳይን ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች አመልክተዋል።
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ሌፍተናንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቻቸው ከሳምንታት በፊት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ወስጥ መግባት እንደማትፈልግ ነገር ግን ስንዝር መሬት እንደማትሰጥ ተናግረዋል።
ሌፍተናንት ጀነራል አል ቡርሐን ጨምረውም አገራቸው ሕጋዊ መብቷን በሚያስከብር መንገድ አሁን በሱዳን ሠራዊት የተያዙት ቦታዎች በይዞታዋ ውስጥ ከሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን 750 ኪሎ ሜትሮች ያህል የጋራ ድንበር ሲኖራቸው፣ ለዓመታት በድንበር አካባቢ ግጭት ሲያጋጥም ነበር።
በተለይ አል ፋሽቃ በሚባለው ለም የእርሻ መሬት ባለበት አካባቢ ግጭቶች በተለያዩ ጊዜያት መከሰታቸው ይነገራል።
በድንበር አካካቢ ተከስቶ ወራትን ያስቆጠረው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሆን፣ በሠላማዊ ሰዎችና በወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።
ውጥረቱን ለማርገብ በሁለቱ አገራት ጠቅላይ ሚኒስትርና በሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካይነት ንግግር ቢደረግም እስካሁን ለቀውሱ መፍትሄ አላስገኘም።














