አዲሱ የቪድዮ መደዋወያ ሕፃናትን ለወሲብ ጥቃት አሳልፎ እንደሚሰጥ ቢቢሲ አጋለጠ

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ፅሑፍ ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶች አሉበት።
ቢቢሲ የሠራው የምርመራ ዘገባ አንድ ኦሚግል የተሰኘ የቪድዮ መደዋወያ ድረ-ገፅ ሕፃናትን ለወሲባዊ ጥቃት እንደሚያጋልጥ ተደረሰበት።
ኦሚግል የተሰኘው የቀጥታ ቪድዮ መደዋወያ መተግበሪያ [አፕሊኬሽን] የማይተዋወቁ ሰዎች እየተያዩ እንዲደዋወሉ የሚያስችል ነው።
ድረ-ገፁ ይዘቶቼን እቆጣጠራለሁ ቢልም ተጠቃሚዎች ያልተጠበቀ ድርጊት ሲፈፅሙበት ታይቷል።
ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ተቋርቋሪዎች ወሲባዊ ጥቃት አድራሾች ገፁን ተጠቅመው ሕፃናትን እየበዘበዙ ነው ሲል ይከስሳሉ።
የገፁ መሥራች ሊፍ ኬ ብሪክስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይዘት የምንቆጣጥርባቸውን መላዎች እያሰፋን ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሴምራሽ የተሰኘው መረጃ ሰብሳቢ ቡድን በቅርቡ ያጠናው ጥናት እንደሚያመልክተው የገፁ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርክቷል።
በፈረንጆቹ ጥር 2020 34 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች የነበሩት ኦሚግል አሁን 65 ሚሊዮን ሰዎችን ያስተናግዳል።
በተለይ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሜክሲኮ የተጠቃሚዎች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል።
በዩኬ ብቻ ባለፈው ታኅሣሥ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች ገፁን ጎብኝተውታል።
ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ከ34 ዓመት በታች ሲሆኑ በርካታ ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ጥናቱ ይጠቁማል።
ቲክቶክ በተሰኘው የቻይና ማሕበራዊ ድር-አምባ ላይ ብቻ 9.4 ቢሊዮን 'ሃሽታግ' ኦሚግል የሚሉ ቪዲዮዎች ታይተዋል።
የቻይናው ቲክቶክ ቢቢሲ በሠራው የምርመራ ዘገባ ምክንያት የኦሚግልን ቪድዮዎች ገፁ ላይ እንዳይጫን አግዷል።
የቲክቶክ ሰዎች እንዳሉት ምንም እንኳ እስካሁን ጎጂ የሚባል ይዘት የኦሚግል ቪድዮዎች ላይ ባያገኙም ቁጥጥራቸውን ግን ይቀጥላሉ።
የወንዶች አፀያፊ ድርጊት
"ሁሉም ሰው ቲክቶክ ላይ ሲያደርገው ዓይተን እኔና ጓደኞቼም እንሞክረው ተባባልን" ትላለች የ15 ዓመቷ አሜሪካዊት ኬይራ።
"ነገር ግን በብዛት የሚታየው ወንዶች አስፀያፊ ድርጊት ሲፈፀሙ ነው። ቁጥጥር ቢደረግበት መልካም ነው። ድብቅ ድረ-ገፅ ነው የሚመስለው። ግን ለሁሉም ክፍት ነው።"
ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ የፖሊስ ተቋማትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችነድረ-ገፁን በተመለከተ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል።
ይህን ካደረጉ ሃገራት መካከል ዩኬ፣ ዩኤስ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳና አውስትራሊያ ይጠቀሳሉ።
ቢቢሲ የምርመራ ዘገባውን ለማድረግ ድረ-ገፁ ላይ በተገኘበት ወቅት በርካታ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተጠቃሚዎችን ተመልክቷል።
አልፎም ዕድሜያቸው ከሰባት ወይም ስምንት የማያልፍ ሕፃናት ድሩን ይጠቀሙታል።
ድረ-ገፁ ተጠቃሚዎች ቢያንስ 18 አሊያም ከዚያ በላይ እንዲሆኑ ቢመክርም የተጠቃሚዎችን ዕድሜ መቆጣጠሪያ መንገድ ግን የለም።
የቢቢሲ ምርመራ ቡድን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዓታት ብቻ ግለ-ሩካቤ [ማስተበርቤት] ከሚያደርጉ 12 ወንዶች ጋር ተገናኝቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ስምንት ራቁታቸውን ያሉ ወንዶችና ሰባት የወሲብ ድረ-ገፅ ማስታወቂያዎች ተመልክቷል።
የወሲብ ድርጊት የሚፈፅሙ ሕፃናት
የምርመራ ቡድኑ ሁለት ጊዜ ግለ-ሩካቤ እያደረጉ ካሉ ታዳጊዎች ጋር መገናኘት ችሏል። ከእነዚህ መካከል አንደኛው የ14 ዓመት ታዳጊ እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
የምርመራ ቡድኑ እኒህን ይዘቶች አልቀዳም። ሕፃናቱ ይህን ድርጊት በሚያደርጉበት ወቅትም የቪድዮ ግንኙነቱ ወዲያውኑ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የድርጅቱ መሥራች የሆነው ግለሰብ ገፁ አሁን መሰል ይዘቶች እንዳይሰራጩ አድርጓል ቢልም ቢቢሲ ይህን ማጣራት አልቻለም።
ሕፃናት ጥቃት ሲደርስባቸው የሚያሳዩ ምስሎችን ከበይነ መረብ በማስወገድ የሚታወቅ ኢንተርኔ ዎች ፋውንዴሽን የቢቢሲ ዘገባ አስደንጋጭ ቢሆንም እውነታን ያሳየ ነው ብሏል።
ድርጅቱ ሕፃናት ወሲባዊ ድርጊቶች ሲፈፅሙ የሚያሳዩ ቪድዮዎች ከኦሚግል ተገኝተው በትላልቅ ሰዎች አማካይነት በይነ መረብ ላይ እንደተበተኑ ደርሼበታለሁ ብሏል።
ቢቢሲ ያናገራት ዩኬ ውስጥ ያለች እናት የስምንት ዓመት ሴት ልጇን አንድ ትልቅ ሰው ወሲባዊ ድርጊት እየፈፀመች ገፁ ላይ እንድትታይ እያሳመናት ሳለ እንደደረሰች ተናግራለች።
"ልጄ ቲክ ቶክ ላይ ሰዎች ስለዚህ ገፅ ሲያወሩ ሰምታ ነው ወደ ድሩ ያመራችው። ይህን ገፅ መመዝገብ [ሎግ ኢን] እንዲሁም የዕድሜ ገደብ አያሻም" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ገፁ ላይ ያሉ ሰዎች ልጄን ቆንጆ ነሽ፣ ታሳሻለች እያሏት ነበር። እሷ ገና ስምንት ዓመቴ ነው ብትልም ችግር የለውም ብለዋታል። ይባስ ብሎ አንድ ትልቅ ሰው ግለ-ሩካቤ ሲፈፅም ተመልክታለች።"
ቢቢሲ ለሶስት ወራት ያክል ኦሚግል የተሰኘውን ገፅ እንዲሁም መሥራቹ ሊፍ ኬ ብሩክስን ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል።
የድረ-ገፁን አስተዳዳሪዎች ለማግኘት የሚያስችል ምንም ዓይነት መንገድ ድሩ ላይ አልተቀመጠም።
መሥራቹን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ
ብሩክስ የተሰኘው የድረ-ገፁ መሥራች ለዓመታት በይፋ ስለ ኦሚግል ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም።
ቢቢሲ መሥራቹ ከሌሎች ጋር ላቋቋመው ኦክቴን ኤአይ የተሰኘ መሥሪያ ስድስት ጊዜ ኢሜይል ልኮ በስተመጨረሻ ምላሽ አግኝቷል።
በሰጠው ምላሽ ድረ-ገፁ የይዘት ቁጥጥር እንደሚደርግለትና ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ተጠቃሚዎች 'እንደሚታገዱ' ተናግሯል።
አልፎም በፈረንጆቹ 2020 የይዘት ቁጥጥር ሥራዎች እንደተጠናከሩ ተናግሯል።
"ምንም እንኳ ፍፁም መሆን ባይቻልም የኦሚግል የይዘት ቁጥጥር ገፁ ንፁህ እንዲሆን አስችሏል። አላስፈላጊ ድርጊቶች የፈፀሙ ሰዎች ተይዘው ለሕግ ተላልፈው እንዲሰጡም አድርገናል" ይላል በኢሜይል የሰጠው ምላሽ።
ሰውዬው በምላሹ ገፁ ላይ የሚታዩት የወሲብ ገፅ ማስታወቂያዎች የሚለቀቁት ዕድሜን ተገን አድርገን ነው ቢልም ተጠቃሚዎች ዕድሜያቸው ካልተመዘገበ ይህ ሊሆን እንደሚችል ግን ማብራሪያ አልሰጠም።
ብሩክስ ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።












