በኬንያ ታዳጊ ሴቶችን በኢንተርኔት ኢላማ ያደረገ ቡድን "አላስፈላጊ ተግባራት" እያስፈፀማቸው ነው ተባለ

ፖሊስ በኬንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ ፖሊስ ታዳጊ ሴቶችን በማማለል አላስፈላጊ ተግባራት ውስጥ የሚያስገባ አንድ ቡድንን እየመረመርኩ ነው ብሏል።

ቡድኑ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቤታቸው ውስጥ የተቀመጡ ታዳጊዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት በማጭበርበር ፓርቲ እንጋብዛችሁ በሚል ሽፋን እየወሰዷቸው ነው ብሏል።

ሶስት ታዳጊዎች ከቤታቸው ጠፍተው ከሰሞኑ በፖሊስ ተገኝተዋል። ታዳጊዎቹ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ ፓርቲ እንደተጋበዙ ተናግረዋል።

ፖሊስ ታዳጊዎቹ ከመጠን በላይ ለሆነ መጠጥና የቡድን ወሲብ ተጋልጠዋል ብሏል።

ቤተሰቦች ልጆቻቸው የሚያደርጓቸውንም ተግባራት እንዲከታተሉና እንዲጠብቁም ፖሊስ አስጠንቅቋል።

የወንጀል መርማሪ ዳይሬክቶሬት ዲሲአይ የቡድኑን አባላት ፍለጋ ላይ እንዳሉና ለሰሯቸውም ወንጀሎች ተጠያቂ ይሆናሉ በማለት በትዊተር ገፁ አጋርቷል።

ስራ እንሰጣችኋለን በሚል የሃሰት ማጭበርበሪያ የሚጠፉ ታዳጊዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑም ከሰሞኑ በሚዲያዎች ላይ ተዘግቧል።

ከሰሞኑ በትዊተር ላይ የጠፋች ታዳጊ ዘመድ ተጠልፋ ወይም በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ወድቃ ሊሆን ይችላልም በሚል እንባ እየተናነቀቃት ስትማፀን ነበር።

የሞዴልነት ስራ አለ በሚልም አጭበርብረው እንደወሰዷት የምትናገረው ዘመዷ ከዚያ በኋላ አልታየችም ብላለች።

"የአጎቴ ልጅና ሌሎች አብረዋት የነበሩ ስድስት ታዳጊዎችም ደብዛቸው እንደጠፋ ነው" በማለት መልእክቷን አስተላልፋለች።

ፖሊስ ጠፍተዋል ከተባሉት ሰባት ታዳጊዎች መካከል ሶስቱን መታደግ እንደቻለ ያስታወቀ ሲሆን ሌሎቹንም ለማግኘት የህፃናት ጥበቃ መርማሪዎች እንደተሳተፉም ተገልጿል።

ታዳጊዎቹ የት እንደተገኙም ሆነ የወሰዷቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

ዲሲአይ እንዳስታወቀው የተባለው ቡድን መቀመጫውን ናይሮቢ እንዳደረገና አለም አቀፍ የስልክ ቁጥሮችንም እንደሚጠቀሙ ባደረግኩት ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።

"ምርመራዎቹ እየተጠናከሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎችን ኢላማ ያደረጉ ግለሰቦችን እናስጠነቅቃለን፤ ቀናችሁ ደርሷል" ብሏል ዲሲአይ በትዊተር ገፁ

በኬንያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንደገና ማሻቀቡን ተከትሎ መመሪያዎች ጠብቀዋል።

ህዝባዊ ስብሰባም ታግዷል፤ የሰዓት እላፊ አዋጅም ተጥሏል። በመጋቢት ተዘግተው የነበሩት ትምህርት ቤቶች በከፊል ጥቅምት ወር ላይ ተከፍተዋል። መንግሥት እንደሚለው እስከ ጥር ድረስ ሙሉ በሙሉ አይከፈቱም ብሏል።

53 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ባላት ኬንያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 75 ሺህ የደረሰ ሲሆን 1 ሺህ 349 ሰዎችም እንደሞቱ ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።