ከትራምፕ በኋላ ባይደን በኢራን ጉዳይ ላይ ምን ያደርጉ ይሆን?

የኢራን ጋዜጦች

የፎቶው ባለመብት, EPA

አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የዓለም አቀፉ ሥርዓት "እየተሳሰረ፤ እየተጋመደ ነው" ይላሉ።

አሜሪካ ያላትን ስምና ተቀባይነትም ለመመለስ ጠንክረው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል። "የምናባክነው ጊዜ የለም" በማለትም የውጭ ጉዳይ መፅሄት ላይ ሃሳባቸውን አስፍረዋል።

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በስልጣናቸው ዘመን አከናውናቸዋለሁ ብለው ከዘረዘሯቸው ጉዳዮችም መካከል የ2015ቱን የኢራን የኒውክሊየር ስምምነትን መመለስ አንዱ ነው።

ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው ወቅት አሳክተዋቸዋል ከሚባሉት ጉዳዮች ውስጥ (JCPOA) ተብሎ የሚጠራው የኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ሲሆን ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ2018 ስምምነቱን አፍርሰዋል።

ኃያላኑ አገራት የደረሱበትን ስምምነትና የፀጥታው ምክር ቤት ያፀደቀውን ውሳኔ ዕውቅናም አልሰጡም በሚልም ትራምፕ ተተችተው ነበር።

ትራምፕ አገራቸውን ከስምምነቱ በማውጣት በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራሟን እንዳትቀጥል ከፍተኛ ጫና ለማድረግ ቢሞክሩም ፍሬ አላፈራም።

በጥር ወር ላይ ስልጣን የሚረከቡት ጆ ባይደንስ ኢራንን ይገቷት ይሆን? በተለይም የአሜሪካ ፖለቲካ እንዲህ በተከፋፈለበት ወቅትና የዓለም ሥርዓትም በተወሰነ መልኩ በተቀየረበት ወቅት፤ ማሳካት ይችሉ ይሆን?

"ስትራቴጂያቸው ግልፅና ግልፅ ቢሆንም ቀላል አይሆንም" በማለት በሮያን ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም የኢራን ባለሙያ አኒሼህ ባሳሪ ታብሪዚ ይናገራሉ።

ወደኋላ መመለስ የለም

የተወሰኑ ፈተናዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ግልፅ ነው።

አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የተወሳሰበ ማዕቀብ መጠቀም ከፈለጉ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንደ ማስገደጃ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ፕሬዚዳንቱ እስካሁን ድረስ የተናገሩት ኢራን የተደረሰውን የስምምነት ግዴታዋን እንድትወጣ ብቻ ነው።

"ቴህራን ስምምነቱን በጥብቅ ልታከብር ይገባል" በማለት ጆ ባይደን ቢፅፉም ይህ ሁኔታ ግን አስቸጋሪ ሆኗል።

ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ማፍረሳቸውን ተከትሎ ኢራንም የገባችውን ቃል አልጠበቀችም ተብሏል።

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የሩብ ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው ኢራን ስምምነቱ ከሚፈቅዳላት በዝቅተኛ ሁኔታ የበለፀገ ዩራኒየም አስራ ሁለት እጥፍ አከማችታለች ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ዩራኒየሟን በከፍተኛ የጥራት ደረጃም ማበልፀግ ጀምራለች የተባለ ሲሆን ስምምነቱ ይፈቅድላት የነበረው 3.67 በመቶ ነው።

በኢራን የሚገኝ የዩራኒየም ማበልፀጊያ

የፎቶው ባለመብት, WANA via Reuters

በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ የበለፀገ ዩራኒየም ለተለያዩ አገልግሎቶች ቢውልም በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ጥርት ብሎ ከበለፀገ ግን በጦር መሳሪያነት፣ ለኒውክሊየር ቦምብነት ይውላል። ይህም ከፍተኛ ስጋት ነው።

ምንም እንኳን እንዲህ አይነት ጉዳዮች ቀላል ቢመስሉም የኢራን ባለስልጣናት በበኩላቸው "አገሪቷ በምርምር ያባከነችውን ጊዜ ዝም ብላ አታቃጥልም፤ ሙሉ በሙሉም አታጠፋም" ይላሉ።

"ወደ ኋላ አንመለስም። በአሁኑ ወቅት የደረስንበት ደረጃ አለ፤ እሱ ነው መታየት ያለበት" በማለት በዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኢራን የቀድሞ አምባሳደር አሊ አስጋር ሶልታኒየህ ይናገራሉ።

ፖለቲካዊ ጫና

ከትራምፕ ይደረግባት የነበረውን ጫና መቋቋም የቻለችው ኢራን በአሁኑ ወቅት መመለስ ይገባቸዋል የምትላቸው ጥያቄዎች አሉ ትላለች።

ባለስልጣናቱ ማዕቀቡ መነሳቱ በቂ አይደለም ይላሉ። በባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ውስጥ አገሪቷ በማዕቀቡ ምክንያት ላጋጠማት የምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆል ካሳ ሊከፈለኝ ይገባልም በማለት ትሞግታለች።

ኢራን በመጪው ሰኔ ወር በምታደርገው ምርጫ ለውጥ ፈላጊዎችና የቀድሞው ሥርዓት በሚልም እየተፎካከሩ ይገኛሉ።

የኢራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአገሪቱ የምጣኔ ሃብት መሽመድመዱን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ ተቀባይነት ዝቅ ብሏል። ጆ ባይደን የኢኮኖሚ እቀባውን በማላላት የፕሬዚዳንቱን ማሸነፍ እድል ከፍ የማድረግ ፍላጎት ይኖራቸው ይሆን?

በቴህራን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ናስር ሃዲን ጄዚ፤ ጆ ባይደን የስልጣን ዘመናቸውን ከመጀመራቸው በፊት በኢራን ላይ ያላቸውን ጉዳይ ግልፅ ሊያደርጉት ይገባል ይላሉ።

"ወደ ስምምነቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት እንመለሳለን ብለው ለሕዝቡ ቢነግሩ በቂ ይመስለኛል" ይላሉ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ሁኔታዎች በበለጠ እንደሚበላሹ ያስረዳሉ።

የጆ ባይደን ወደ ኒውክሊየር ስምምነቱ መመለስ ጉዳይ በእሳቸው ብቻ አይወሰንም። የኒውክሊየር ስምምነቱ በአሜሪካ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛ ልዩነትን ያመጣ ሲሆን ሪፐብሊካኑ በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወሙታል።

በጆርጂያ ያለው የምክር ቤቱ ምርጫ ውጤት በጥር ወር ሲጠናቀቅ በዋሽንግተን ያለውን የኃይል ሚዛን የሚወስን ይሆናል። ይህም ሁኔታ አስተዳደሩ በምን አይነት ነፃነትም ተግባሩን ያከናውናልም የሚለውንም ያሳያል።

አዲስ ጥምረቶች

የኒውክሊየር ስምምነቱ የሁለትዮሽ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ኃያላኑ አገራት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ጀርመን እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት በስምምነቱ ላይ ድርሻ አላቸው፤ ዓለም አቀፍም ደጋፊም ተብለው ተካተዋል።

በተለይም የአውሮፓውያኑ አሜሪካ ወደ ስምምነቱ ተመልሳ እንዲሳካ ታደርገዋለች የሚለውን በጉጉት የሚጠብቁት ይሆናል።

ትራምፕ ስምምነቱን ካፈረሱት በኋላም ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይና ጀርመንም ስምምነቱ እንዲቀጥል የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ነበር።

ሆኖም ሦስቱም የአውሮፓ አገራት ዓለም እንደተቀየረችና ወደቀድሞው ስምምነት መመለስም የማይቻል መሆኑንም ይረዱታል።

ፕሮፌሰር አኒሴህ ባሲሪ ታብሪዚ እንደሚሉት ኢራን በቀጣናው የምታደርገው እንቅስቃሴ፣ የባሊስቲክ ሚሳይል ልማትና እንዲሁም የኒውክሊየር ስምምነቱ ጊዜ ማለፉም ጋር ተያይዞ የአውሮፓውያን አገራቱ ስምምነቱ በአዲስ መልክ እነዚህን ጉዳዮች ሊያካትት ይገባልም እያሉ ነው።

የኢራን ባሊስቲክ ሚሳይል

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

የኒውክሊየር ስምምነቱን (JCPOA) በመጀመሪያ ሲቃወሙ የነበሩት እስራኤል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ባህሬንን የመሳሰሉ የቀጣናው አገራት በትራምፕ አማካኝነት ግንኙነታቸውን ለማደስ መወሰናቸው አዲስ ለሚመጣው ስምምነት በራቸው ክፍት ላይሆን ይችላል።

"በአካባቢያችን ያለውን የደኅንነት ጉዳይ በተመለከተ ስምምነት መፈረም ካለበት እኛም መኖር አለብን" በማለት በዋሽንግተን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር ዩሴፍ አል ኦታቢያ በቴልአቪቭ ዩኒቨርስቲ በነበረ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

የእስራኤልም አቻቸው አሞስ ያድሊን ይህንኑ አስተያየት የተጋሩት ሲሆን "እስራኤል ከመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮቿ ጎን በመሆን ስምምነቶቹ ላይ መገኘት ትፈልጋለች" ብለዋል።

የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ሳልማን በበኩላቸው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢራንን ተቃውሞ እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል።

በዚህ ሁሉ ፍራቻ፣ መጠራጠርና የተለያየ ፍላጎት መካከል ወደ ኒውክሊየር ስምምነት መመለስ ለጆ ባይደን ቀላል አይሆንም። መረሳት የሌለበት ጉዳይ ደግሞ ትራምፕ ስልጣናቸውን አላስረከቡም።

ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት ትራምፕ የኢራን የኒውክሊየር ማበልፀጊያ ጥቃት እንዲደርስበት ከፍተኛ አማካሪዎቻቸውን ጠይቀዋል የሚልም ዜና የአሜሪካ ሚዲያዎች ይዘው ወጥተዋል።

በምርጫ የተሸነፉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራንን አልለቀቋትም አዲስ ማዕቀብም እያስተዋወቁ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ እቀባዎችም ይኖራሉ በማለትም እያስፈራሩ ነው።

ትራምፕ እስከ ጥር ድረስ የሚያደርጉት ተግባር ግልፅ ይመስላል፤ ከእሳቸው ስልጣናቸውን ለሚረከቡት ጆ ባይደን ሥራቸውን ማክበድና፤ የደረሰውንም ጉዳት እንዳይቀለበስ ማድረግ ነው።