የአሜሪካ ምርጫ፡ የትራምፕ መሸነፍ አረብ አገራትን ለምን አስደነገጠ?

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY
የዛሬ ሳምንት አካባቢ ነው፤ አምባሳደሩ ስልካቸውን ይበረብራሉ። ትኩረታቸው ተበታትኗል። ቶሎ ቶሎ ይተነፍሳሉ። “ይቅርታ፣ ትኩረት አጣሁ አይደል?” አሉ፣ ከትህትና ጋር።
እኚህ ሰው በታላቋ ብሪታኒያ የሳኡዲ አምባሳደር ናቸው። ዐይናቸውን ከስልካቸው መንቀል ያልቻሉበት ምክንያት አለ። አሜሪካ ‘ማሊያ’ እየቀየረች ነው። የአሜሪካንን ምርጫ በአንክሮ እየተከታተሉ ነው የተረበሹት። አብረዋቸው ያሉትን ሰዎች ደጋግመው ይቅርታ ሲጠይቁ በነበረበት በዚያ ቅጽበት የአሜሪካ ግዛት ዊስኮንሰን ቆጠራ ውጤት እየተገለጸ ነበር።
ዊስኮንሰን እንደ ሚሺጋን ሁሉ ባይደን አሸንፈዋል። አምባሳደሩ ያለ ምክንያት አልደነገጡም። ያለ ምክንያት ትኩረታቸው አልተበታተነም። አገራቸው ሳኡዲ ትራምፕን አጣች ማለት ነዳጅ ማውጫዋ ደረቀ ከማለት የሚተናነስ መርዶ አይደለም። ምናልባት ይህ ዐረፍተ ነገር ተጋኖ ይሆናል።
በዲፕሎማሲ ዋጋ ግን አልተጋነነም። ለዚህም ይመስላል ሳኡዲዎች ለጆ ባይደን እንኳን ደስ ያለዎት ለማለት እንኳ ጊዜ የወሰደባቸው። ከድንጋጤያቸው የበረዱት ዘግይተው ነው። ትልቅ አጋራቸውን፣ ትልቅ ወዳጃቸውን፣ ቀኝ እጃቸው ነው በሽንፈት ያጡት። ዶናልድ ትራምፕ።
የባይደን ድል ለሳኡዲ አረቢያና ሌሎች የገልፍ አገሮች ብዙ ጦስ ይዞ መምጣቱ ከወዲሁ እየተነገረ ነው። አሜሪካ ከገልፍ አገራት ጋር ያላት አጋርነት ከ1945 ዓ ም የሚጀምር ነው። በነዚያ ሁሉ ዘመናት በአመዛኙ መልካም የሚባል ሆኖ ነው የዘለቀው። ይህ ግሩም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በባይደን ጊዜ መልኩን ይለውጣል ማለትም አይደለም።
ነገር ግን የትራምፕ ዘመን ግንኙነት ላይመለስ ሄዷል። ትራምፕ ለሳኡዲ የልኡላን ቤተሰብ እንደ አጎት ነበሩ። ትራምፕ ገና እንደተመረጡ በ2017 መጀመርያ እግራቸውን ያነሱት ወደ ሪያድ ነበር። አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደተመረጠ ቀድሞ ወደ አረብ አገር ይሄዳል ተብሎ አይጠበቅም። የዶናልድ ትራምፕ አማቻቸው (የሴት ልጃቸው ባል) ጃረድ ኩሽነር ከኃያሉ ልዑል ከመሐመድ ቢን ሳልማን ጋ ጥብቅ ምስጢረኛ ነው።
የትራምፕ ቤተሰብና የሳኡዲ ልዑላን ፍቅራቸው ከዓይን ያውጣችሁ በሚባል ደረጃ መድረሱን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። በ2018 ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ በግፍ ኢስታንቡል የሳኡዲ ቆንጽላ ውስጥ ሲገደል ዓለም በሙሉ በሳኡዲው ልዑል ፊቱን አዞረበት።
ልዑሉ በሕግም በዲፕሎማሲም እንዲጠየቁ ግፊቱ በረታ። ነገሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ደረሰ። ቱርክ ዓለምን አስተባብራ ብዙ ርቀት ሄደች። በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ለልዑሉ አንድ ሰው ነበራቸው። ያን ግፊት ያቆሙላቸው ሰው ዶናልድ ትራምፕ ይባላሉ። ትራምፕ ለልዑላዊያኑ የዋሉት ውለታ በዚህ አላበቃም።
የአሜሪካ የላይኛው ምክር ቤታቸው ለሳኡዲ ውስብስብና ውድ የጦር መሣሪያዎች ከእንግዲህ እንዳይሸጡላት ብሎ ነበር። ይህም የመጣው የጋዜጠኛውን እጅግ አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ ነበር። ይህን ለመወሰን ጫፍ ሲደርስ የነበረው ሴኔት ትራምፕ ነገሩን አከሸፉበት። ይህ የትራምፕ ከሰብአዊ ጨቋኞች ጎን የመቆም ውለታ ለሳኡዲ ብቻ አልነበረም።
ለባሕሬን፣ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስም ተመሳሳይ ውለታን ሰርተዋል። ለዚህም ነው እነዚህ አገሮች የትራምፕ መሸነፍ ክው ብለው እንዲቀሩ ያደረጋቸው። ለመሆኑ የትራምፕ መሄድና የባይደን መምጣት በገልፍ አገሮች በተጨባጭ ምን ይቀይራል? የየመን ጦርነት ባራክ ኦባማ በዋይት ሐውስ ለ8 ዓመት ሲኖሩ ምቾት ከነሷቸው ነገሮች አንዱ ሳኡዲ በየመን ዜጎች ላይ ታደርስ የነበረው የአየር ድብደባ ነበር።
ሳኡዲ በሁቲ አማጺዎች ላይ ቦምብ ስታዘንብ ነው የኖረችው። ሁቲዎች በኢራን ይደገፋሉ። ኢራን የሺአ ኢስላም መሪ አገር ናት። የመን በሳኡዲ ተጽእኖ ሥር ሆና የሱኒ ኢስላም መስመርን እንድትከተል ነው ትግሉ። ነገሩ በሃይማኖታዊ መስመር ውስጥ ፖለቲካዊ ተጽእኖን ለማሳደርና የአካባቢው ዋና አለቃ ሆኖ ለመቀጠል የሚደረግ ፉክክር እንጂ ያን ያህልም መንፈሳዊ ተልእኮ አለበት ለማለት አያስደፍርም።
ነገሩ ያልጣማቸው ኦባማ ዋይት ሐውስን ሲለቁ ታዲያ ሳኡዲ ለ2 ዓመታት የመንን በአውሮፕላን ደብድባ ያገኘችው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። እንዲያውም ንጹሐንን ፈጅታለች። በመጨረሻ በካፒቶል ሂል ጉምጉምታው ሲበረታ ኦባማ በመጨረሻዎቹ የሥልጣን ዓመታት ቶሎ ብለው አሜሪካ ለሳኡዲ የምታደርገውን የወታደራዊና የደህንነት ድጋፍ አቋረጡ።
ትራምፕ ዋይት ሐውስ ሲገቡ ግን ይህንን ቀለበሱት። የየመን ሰቆቃ የበረታው ከዚህ በኋላ ነበር። አሁን ግን ነገሮች ይለወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባይደን ከኦባማ ሥር ሆነው አሜሪካንን በመሩበት ዘመን የየመን ጦርነትና የሳኡዲ ድብደባ ያደረሰውን ሰብአዊ እልቂት ተመልክተዋል። ትርፍና ኪሳራውን መዝነዋል።
ሺዎች የተቀጠፉበት፣ ሕጻናት በረሀብ አለንጋ የተቀጡበት የየመን ጦርነት ከንቱ የከንቱ ከንቱ እንደሆነ አገናዝበዋል። እርግጥ ነው የሁቲ ሚሊሻ የመንን በሙሉ ቁጥጥር ሥሩ ማድረግ ለአሜሪካ የሚጥም አይሆንም። ይህም ኢራን አጋር ታገኛለች ከሚል ፍራቻ ነው። ሆኖም ባይደን ከሰሞኑ ላቋቋሙት የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ካውንስል እንደተናገሩት ከሳኡዲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደገና እንደሚያጠኑት ጠቁመዋል።
የየመን ተዋጊዎችና ሳኡዲዎች ከዚህ በኋላ ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙርያ እንዲፈቱ ባይደን ግፊት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ለነገሩ ሳኡዲም ሆነች ብልጹጓ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ይሄ የየመን ጦርነት ማብቂያ እንደማይኖረው ዘግይተውም ቢሆን የተረዱ ይመስላሉ። በቅርብ ጊዜ የጦር ማቆም ስምምነቶችን ያደረጉትም ለዚህ ይሆናል።
ኳታር የፔንታጎን ሳሎን ናት ይላሉ የአካባቢ ፖለቲካ አዋቂዎች። እጅግ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውና በመካከለኛው ምሥራቅ ወሳኙ የጦር ስፍራ አልኡደይድ የሚገኘው በኳታር ነው። አሜሪካ ከአልኡደይድ ቀጠና ሆና ነው አፍጋኒስታንንም ሆነ ሶሪያን የአየር ኃይል ጥቃት የምትሰነዝረው።
መካከለኛው ምሥራቅንና የአየር ክልሉን የምትቆጣጠረውም ከዚህ ከአልኡይዲ ነው። ይህ የኳታር ውለታ ታዲያ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እንዲመለስ ይፈለጋል። እርግጥ ነው አሜሪካ ለኳታር ልዩ ጥበቃ ታደርጋለች። ሆኖም የኳታር ፍላጎት ሌላ ነው።
ኳታር ሀብታም አገር ብትሆንም ማንም የማይቋቋመው እቀባ ጥለውባታል፣ የገዛ ወዳጅ አገሮቿ። የገዛ ጎረቤቶቿ። ሳኡዲዎች፣ ኢምሬቶች፣ ባህሬኖችና ግብጽ በኳታር ላይ የጨከኑት በየአገሮቻችን አብዮት ታስነሳብናለች፣ የሕዝብ አመጽ በገንዘብ ትደግፍብናለች ብለው ነው። የግዙፉ አልጀዚራ ዜና ጣቢያም ለአረብ አገራቱ የጎን ውጋት ሆኖባቸዋል።
ኳታር አልጀዚራን እንድትዘጋላቸው አገራቱ ይሻሉ። ግብጽም አልጀዚራን እንደ ጦር ነው የምትፈራው። ከኳታር ጋር ያላቸውን ድንበር የመክፈትና ግንኙነቶችን የማሻሻሉ ነገር እውን የሚሆነው ከ11 ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የአልጀዚራ መዘጋትም ሲጨመርበት ነው። ይህ በኳታር ላይ አረብ ወገኖቿ የጣሉት ማዕቀብ የተጀመረው ትራምፕ ሪያድን በጎበኙበት በ2017 አካባቢ ነበር።
ኳታሮች ትራምፕ ይህንን ጉዳይ በዋዛ ያልፉታል ብለው በጭራሽ አላሰቡም ነበር። አገራቱን ተቆጥተው ወደ ድርድር ያመጧቸዋል ብለው የኳታር ኤሚሮች ተስፋ አድርገው ነበር። ያ ግን አልሆነም። በእርግጥ ትራምፕ የኳታር ወዳጅነትን በደንብ አያውቁም ነበር ነው የሚባለው።
ያን ጊዜ የፖለቲካ ግንዛቤያቸው የሳሳ ነበር የሚሉት ተንታኞች ኳታር ለፔንታጎን እጅግ ወሳኙን የአል ኡደይድ የጦር ሰፈር እንደምታቀርብ ሲነገራቸው ግን ኳታርን በይፋ ደግፈው ይህ የገልፍ አገሮች እቀባ እንዲነሳላት መናገር ጀምረው ነበር። ሆኖም ጉዳዩን አልገፉበትም።
ምናልባት ውስብስብ ፖለቲካዊ ኩነቶች ተፈጥረው ይሆናል። ምናልባትም ሁነኛ የጦር መሣሪያ ሸማቿን ሳኡዲን ላለማስቀየም ይሆናል። ብቻ ትራምፕ ነገሩን ዘነጉት። ባይደን መምጣታቸውን ተከትሎ ኳታር ወንድም አገሮች የጣሉባት እቀባ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
አረብ አገራትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ብዙዎቹ የገልፍ አገራት የሰብአዊ መብት አያያዛቸው አሳፋሪ የሚባል ነው። ትራምፕ ግን ለዚህ ግድ ያላቸው ሰው አልነበሩም።
በአረብ አገራቱ ሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻሉ በንጉሣዊያኑ ላይ ጫና አድርገውም አያውቁም። የርሳቸው ትኩረት የነበረው ከአረብ አገራቱ የሚገኝ የነዳጅ ሪያል ነበር። ባይደን ከዚህ ምጣኔ ሀብታዊ ጠባብ እይታ በከፊልም ቢሆን ዞር ብለው የሰብአዊ መብት አያያዞች እንዲሻሻል ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።
ሳኡዲ ለሴቶች ነጻነት የምትመች አልሆነችም። ቢን ሰልማን በዚህ ረገድ ጥቂት ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ ትንሽ ውዳሴን እንዳገኙ ብዙ የመብት ታጋይ ሴቶችን እስር ቤታቸው አጉረዋል።
ኳታር በውጭ አገራት ሰራተኞች አያያዝ ላይ አሳፋሪ ታሪክ አላት። ኢምሬትሶችም በሰብአዊ መብት ረገጣ በደፈናው ይተቻሉ። ከሁሉ ከሁሉ ሳኡዲ በኻሾግጂ ላይ ያደረገችው ይቅር የሚባል አልሆነም።
መቺ ኃይል ልካ የገዛ ዜጋዋን በኢስታንቡል የገዛ ኤምባሲዋ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱን ካጠፋች በኋላ ሬሳው እንኳ የት እንደተጣለ አንዳይታወቅ አድርጋ ዓለምን ያስደነገጠ ኢሰብአዊ ድርጊትን ፈጽማለች።
ጆ ባይደን የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጠኛው ጀማል ኻጆግኒን ጉዳይ ተንተርሰው ሳኡዲን ያስጨንቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።












