ትራምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚሉት ምኑን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዲሞክራቱ ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ማሸነፋቸው እሙን ነው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን በአንዳንድ ቁልፍ ግዛቶች ላይ በምርጫ ውጤት ላይ ሕጋዊ ጥያቄዎችን አነሳለሁ እያሉ ነው።
የትራምፕ ጠበቃ ሩዲ ጁሊያኒ ለፎክስ ኒውስ ሲናገሩ ትራምፕ ሽንፈቱን ቢቀበሉ ስህተት ነው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ፤ "ይህ ምርጫ ቢያንስ ሦስት ወይም አራት እንደውም 10 በሚሆኑ ግዛቶች ስለመሰረቁ ማስረጃ አለ። "
ጠበቃው ጨምረውም የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ምርጫው ስለመጭበርበሩ የሚያረጋግጡ "ጠንካራ ማስረጃዎችን" ይዞ ይቀርባል።
የትራምፕ ጠበቆች በቁልፍ ግዛቶች የሚያነሷቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።
ፔንሲልቬኒያ
ጠበቃው ሩዲ ጁሊያኒ በፔንሲልቬኒያ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መሄድ አለመቻላቸውን በማስመልከት ክስ ይመሰረታል ብለዋል።
የምርጫ ታዛቢዎች ከምርጫ ቀን ጀምሮ ፍቃድ እስካገኙ ድረስ የምርጫ ቆጠራውን የመታዘብ መብት አላቸው።
በዘንድሮ ምርጫ ከምርጫ ቀን በፊት የተጣሉ ገደቦች ነበሩ። ለዚህም ከምክንያቶቹ መካከል አንዱ ኮሮናቫይረስ ነው።
በፊላዴልፊያ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ላይ እስከ 6 ሜትር ርቀት እንዲኖር ተወስኖ ነበር።
የትራምፕ ጠበቃ ምንም እንኳ ፍርድ ቤት የሪፓብሊካን ታዛቢዎች ቆጠራውን ተጠግተው እንዲታዘቡ ቢፈቅድም ይህ ሳይሆን ቀርቷል ይላሉ።
የግዛቲቱ ምርጫ አስፈጻሚዎች ግን ስራችንን ያከናወነው ሕግን ተከትለን ነው ይላሉ።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የሚያነሳው ሌላ ጉዳይ ዘግይተው በፖስታ የተላኩ ድምጾች ለምን ተቆጠሩ የሚለው ይገኝበታል።
በምርጫው ቀን ተልከው ምርጫው ከተከናወን ከሶስት ቀናት በኋላ በቆጠራ ጣቢያ የደረሱ ድምጾች መቆጠር የለባቸውም ይላሉ የትራምፕ ጠበቆች።
ሚሺጋን
ከአራት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ ትራምፕ በሚሺጋን ግዛት ማሸነፍ ችለው ነበር። ባይደን በዚህ ግዛት እንደሚያሸንፉ ተገምቷል።
የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን በምርጫው ዕለት የሪፓብሊካን ምርጫ ታዛቢዎች ወደ ድምጽ መቁጠሪያ ጣቢያዎችን ገብተው መታዘብ አልቻሉም በሚል ምክንያት በሚሺጋን የድምጽ ቆጠራው እንዲቆም ያቀረቡት ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ የትራምፕ ጠበቃቆች ጥያቄን ውድቅ ያደረጉት በቂ ማስረጃ መቅረብ አልቻለም በሚል ነው።
ዊስኮንሰን
የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን በዊስኮንሰን ግዛት ዳግም ቆጠራ እንዲካሄድ እጠይቃለሁ ብሏል።
በዊስኮንሰን ግዛት ድምጽ ተቆጥሮ አልተጠናቀቀም በዚህም የጠበቆቹ ጥያቄ መቼ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሪቻርድ ብሪፎልት እአአ 2016 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ በዊስኮንሰን ግዛት ምርጫው ዳግም ተካሂዶ "በመቶዎች የሚቆጠር የድምጽ ለውጥ ታይቷል" ይላሉ።
ነቫዳ
የነቫዳ ሪፓብሊካን ፓርቲ "ከዚህ ቀደም የኔቫዳ ነዋሪ የነበሩ እና አሁን በሌላ ስፍራ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የምርጫ ሕጉን ተላለፈው ድምጽ እንዲሰጡ ተደርጓል" ብሏል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ ጠበቆች ነዋሪነታቸው ኔቫዳ ግዛት ሳይሆን በነቫዳ ድምጽ የሰጡ የሰዎች ስም ዝርዝርን ይፋ አድርገዋል።
ምርጫ አስፈጻሚዎች ግን የተጣሰ የምርጫ ሕግ የለም እያሉ ነው።
ጆርጂያ
በጆርጂያዋ ቻታም ካውንቲ የድምጽ ቆጠራው እንዲቆም ፍርድ ቤት እንዲያዝ የትራምፕ ጠበቆች ጠይቀው ነበር።
ሪፓብሊካኖች ታዛቢዎቻችን ድምጽ ሳይቆጠር ገሸሽ እንዲደረግ ሲያደርጉ ተመልከተዋል ይላሉ። ፍርድ ቤት ግን ለዚህ ማስረጃ አልቀረበም በሚል ቆጠራው እንዲቀጥል ወስኗል።
አሪዞና
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላት ቅዳሜ ዕለት በሕጋዊ መንግድ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ድምጽ ሰጪዎች ድምጻቸው እንዳይቆጠር ተደርጓል በማለት በአሪዞና ይግባኝ ብለዋል።
ይህ ይግባኝ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየተመረመረ ይገኛል።
ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያመራ ይሆን?
ፕሬዝደንት ትራምፕ በምርጫ ዕለት ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ ምርጫው ተጭበርብሯል ካሉ በኋላ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ተናግረው ነበር።
ትራምፕ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከመውሰዳቸው በፊት ይግባኝ ያሉባቸው ጉዳዮች በየግዛቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች መታየት ይኖርባቸዋል።
የግዛት ፍርድ ቤቶች ምርጫው ዳግም እንዲቆጠር የሚያዙ ከሆነ ብቻ ነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ እንዲገባ ሊጠየቅ የሚችለው።
የሕግ መምህሩ ብሪፎልት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የምርጫውን ጉዳይ የመመልከቱ ዕድል በጣም አነስተኛ ነው ይላሉ።














