የአፍሪካና የተቀረው ዓለም መሪዎች ለባይደን የደስታ መልዕክት እያላኩ ነው

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጆ ባይደን ተቀማጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን በማሸነፍ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠዋል።

ይህን ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።

በትላልቅ የአሜሪካ ከተሞች ያሉ የጆ ባይደን ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ደስታቸውን እየገለፁ ነው። የትራምፕ ደጋፊዎች ደግሞ በተቃራኒው ተቃውሞ ላይ ናቸው።

የጆ ባይደን መመረጥ ይፋ ከሆነ በኋላ በርካታ የዓለም መሪዎች ተመራጩን ፕሬዝደንት እንኳን ደስ አለዎ እያሉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያው ጠ/ሚ አቢይ አሕመድ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጆ ባይደንን 'እንኳን ደስ አለዎ' በለዋለቸዋል።

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂም ለተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት እንደላኩ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምም ለጆ ባይደን መልካም ምኞት ልከዋል። 'ከአዲሱ አስረተዳደር ጋር አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን' የሚል ሐሳብም አክለዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከዶ/ር ቴድሮስ ጋር እሰጥ አገባ እንደገቡና ሃገራቸውን ከዓለም ጤና ድርጅት ለማስወጣት መዛታቸው አይዘነጋም።

የካናዳው ጠ/ሚ ጀስቲን ትሩዶ ቀደም ብለው የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት ካስተላለፉ መሪዎች መካከል ናቸው።

የዚምባብዌው ፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣ የዩጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒ፣ የኬንያው ኬንያታ፣ የጋናው አኩፎ አዶ የደስታ መልዕክታቸውን ለጆ ባይደን ከላኩ የአፍሪካ መሪዎች መካከል ናቸው።

አብዛኛዎቹ መሪዎች ለአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የደስታ መልዕክት ከላኩ በኋላ ከአሜሪካ ጋር አብሮ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸው አሳውቀዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው ትችት ይደርስባቸዋል።

ጆ ባይደን ማናቸው?

ጆ ባይን የቀድሞ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።

ባይደን የፖለቲካ ሕይወታቸው የጀመረው ከ47 ዓመታት በፊት ነበር። የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆኑን ጥረት ማድረግ የጀመሩት ደግሞ ከ33 ዓመታት በፊት እአአ 1987 ላይ።

ጆ ባይደን ትራምፕ ያበላሹትን የውጭ ግንኙነት አስተካክላለሁ፤ አሜሪካ ያስቀየመቻቸውን ወዳጆቿን ልብ እጠግናለሁ ብለዋል። ከኢራንና ከቻይና ጋር የሚከተሉት ፖሊሲም ትራምፕ ጋር የሚቃረን ነው።

ባይደን የአሜሪካን 2020 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው የተረጋገጠው ከ270 ኤሌክቶራል ድምጽ በላይ ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው።