ትራምፕ ምርጫውን አስመልክቶ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካዋ ፔኒሲልቫኒያ ግዛት ዳኛ የፕሬዝደንት ትራምፕ ጠበቆች በፖስታ የተላኩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድምፆች ውድቅ ይደረጉ ብለው ያቀረቡትን ክስ ውድቅ አደረጉ።
ዳኛ ማቲው ብራን የምርጫ ድምፅ ቆጠራው የተዛባ ነበር ተብሎ የቀረበው ክስ 'ጭብጥ አልባ' በማለት ውድቅ አድርገውታል።
ይህ ማለት በሚቀጥለው ሳምንት የፔኒሲልቫኒያ ግዛት የጆ ባይደንን አሸናፊነት ውድቅ ያደርጋል ማለት ነው።
ባይደን በግዛቲቱ ዶናልድ ትራምፕን በ80 ሺህ ድምፆች እየመሩ ይገኛሉ።
ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 3 የተደረገውን ምርጫ ውጤት አልቀበልም በማለት ክስ ቢመሠርቱም በበርካታ ግዛቶች ድል እየቀናቸው አይደለም።
ፕሬዝደንቱ በፖስታ የተላኩ ድምፆች መቆጠር የበላቸውም፤ የተጨብረበሩ ናቸው ሲሉ ማስረጃ አልባ ክስ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
ለወትሮው የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ከምርጫው ጥቂት ቀናት በኋላ ውጤት አምነው የሚቀበሉ ቢሆንም ትራምፕ ግን እስካሁን አሻፈረኝ ብለዋል።
ጆ ባይደን ትራምፕን 306 ለ232 በሆነ ኢሌክቶራል ኮሌጅ ድምፅ እየመሩ ይገኛሉ።
በአሜሪካ ምርጫ ሕግ መሠረት የማሸነፊያው ድምፅ 270 ነው።
የትራምፕ ጠበቆች በተለይ ግዙፍ የሚባሉ ግዛቶች የጆ ባይደንን አሸናፊነት እንዳያውጁ በመጎትጎት ላይ ናቸው።
ግዛቶች የጆ ባይደንን አሸናፊነት አወጁ ማለት ዶናልድ ትራምፕ ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ አበቃላቸው ማለት ነው።
ከወሳኝ ግዛቶች አንዷ የሆነችው ፔኒሲልቫኒያ ዳኛ የሆኑት ብራን የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ድምፆችን ሕጋዊ ያልሆኑ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።
'ፍርድ ቤት የቀረበለት ክስ ጭብጥ አልባ እና ማስረጃ የሌለው ወቀሳ ነው' ሲሉ ነው ዳኛው ጉዳዩን ውድቅ ያደረጉት።
የትራምፕ ጠበቆች ነጋ ጠባ ሳንል ይግባኝ እንጠይቃለን ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ጥቂት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ናቸው ፕሬዝደንቱ የምርጫውን ውጤት እንዲቀበሉ በይፋ የወተወቱት።
ጆርጂያ በተባለችው ግዛት ድምፅ ድጋሚ ይቆጠር ብለው ያመለከቱት ትራምፕ ቅሬታቸው ተሰምቶ ድምፅ ድጋሚ ቢቆጠርላቸውም ተሸናፊ ከመሆን አላዳናቸውም።
ፕሬዝደንቱ ለሶስተኛ ጊዜ ድምፅ ድጋሚ ይቆጠር ሲሉ በጠበቆቻቸው አማካይነት አመልክተዋል።
በሌላኛዋ ወሳኝ ግዛት ሚሺጋን የጆ ባይደን ማሸነፍ በይፋ ከመታወጁ በፊት ሁለት ሳምንት ያስፈልጋል ቢባልም የግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች ይህ ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።
በዊስኮንሲን ደግሞ የትራምፕ ምርጫ ቡድን ታዛቢዎች ድጋሚ ቆጠራው እንዲዘገይ ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ የምርጫ አስተባባሪዎች ከሰዋል።
ግዛቶች የአሸናፊዎችን ውጤት ይፋ የሚያደርጉበት ቀነ ገደብ እየቀረበ ነው።
በአሜሪካ ምርጫ አሸናፊዎችን ይፋ የሚያደርጉት ግዛቶች ሲሆኑ ይህ ተደምሮ በሃገር ደረጃ ውጤቱ ይፋ የሚሆነው።












