1 ቢሊዮን ዶላር ተከፍሎ አባል የሚሆንበት የትራምፕ የጋዛ 'የሰላም ቦርድ' ምንድን ነው?

ከግራ ቶኒ ብሌር፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ማርኮ ሩቢዮ
የምስሉ መግለጫ, ከግራ ቶኒ ብሌር፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ማርኮ ሩቢዮ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ የሰላም ዕቅድ በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ያገኘ ነበር። የዚህ የሰላም ዕቅድ አካል የሆነው 'አዲስ ዓለም አቀፍ የሽግግር አካል' አወዛጋቢ ሆኗል።

'የሰላም ቦርድ' ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሆነው ከተካተቱ መካከል የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይገኙበታል።

ቶኒ ብሌር በአውሮፓውያኑ 2003 ኢራቅ ላይ የተፈጸመውን ወረራ በመደገፍ ይከሰሳሉ።

በቦርዱ ውስጥ አንድም ፍልስጤማዊ የለም። ቋሚ የቦርዱ አባል ለመሆን 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል ያስፈልጋል መባሉ ጥያቄ አጭሯል።

በቦርዱ ውስጥ የመንግሥታቱ ድርጅት ያለው ሚናም አነጋጋሪ ሆኗል።

የሰላም ቦርዱ ለማን ጥሪ አቀረበ?

በርካታ የዓለም መሪዎች የቦርዱ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መሪዎች ጥሪ ከደረሳቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

  • የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ
  • የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ
  • የቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ ክሪስቶዱሊደስ
  • የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታሕ አል-ሲሲ
  • የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮን ደር ላይን
  • የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ
  • የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ
  • የዩርዳኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃፋን ሐሰን
  • የፓኪስታን ፕሬዝዳንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ
  • የፖላንድ ፕሬዝዳንት ካሮል ናውሮኪ
  • የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
  • የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን
  • የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር

የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ሉክሰንም ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን "ነገሩን እንደሚያጤኑት" ገልጸዋል።

የታይላንድ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም የጥሪውን ዝርዝር ይዘት እየቃኘ መሆኑን አስታውቋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ የቦርዱ አባል ናቸው

በሰላም ቦርዱ ለመካተት እነማን ፈቀዱ?

በቦርዱ እንዲካተቱ የቀረበላቸውን ጥሪ መቀበላቸውን በይፋ የገለጹት የሚከተሉት ናቸው፦

  • የአልባንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢዲ ራማ
  • የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ሀቬር ሚሌ
  • የሃንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን
  • የካዛኪስታን ፕሬዝዳንት ካሲም-ጆማርት ቶካዬቭ
  • የፓራጉዋይ ፕሬዝዳንት ሳንቲያጎ ፔና
  • የኡዝቤኪስታን ፕሬዝዳንት ሻቭካት ሚርዝዮዬቭ

የቬትናም ኮምኒስትፓርቲ ዋና ፀሐፊ ቶ ላም ጥሪውን መቀበላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮም "ለመሳተፍ ዝግጁ" መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ጥሪውን ቢቀበሉም የቦርዱ አባል ለመሆን ገንዘብ አይከፍሉም።

የሰላም ቦርዱን ለመቀላቀል ቅድመ ሁኔታዎች አሉ?

የአሜሪካ ባለሥልጣን ለቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት፤ ቦርዱን ለመቀላቀል የተቀመጠ ምንም ቅድመ ሁኔታ የለም።

ሆኖም ከሦስት ዓመት በላይ ለሚዘልቅ ጊዜ የጋዛ ሰላም ቦርድ ቋሚ አባል መሆን የሚፈልጉ አካላት 1 ቢሊዮን ዶላር መክፈል አለባቸው።

ገንዘቡ ጋዛን መልሶ ለመገንባት እንደሚውል ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

የቦርዱ የዕድሜ ዘመን መሪ ትራምፕ ይሆናሉ። ከፕሬዝዳንትነት ቢለቁም ቦርዱን መምራት ይቀጥላሉ።

ቦርዱ ከጋዛ ባሻገር በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት እንደሚሠራ ሮይተርስ የዜና ወኪል የተመለከተው የቦርዱ ረቂቅ ሰነድ ይጠቁማል።

ትራምፕ በተመድ ጉባዔ ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ በተመድ ጉባዔ ንግግር ሲያደርጉ

የሰላም ቦርዱ የተመድን ሥልጣን ይገዳደራል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስለ ቦርዱ በሚገልጽ ደብዳቤ ላይ ትራምፕ "ቦርዱ ዓለም አቀፍ ግጭትን ለመፍታት አዲስ ስልት ይቀይሳል" ብለዋል።

ይህም የተባበሩት መንግሥታትን ሥልጣን እንደሚገዳደር ተሰግቷል። የተቋሙ የፀጥታዊ ምክር ቤት በዓለም አቀፍ መድረክ ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የእስራኤሉ ሀሬትዝ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ቦርዱ "ፈጣን እና ውጤታማ ዓለም አቀፍ የሰላም ተቋም" የመሆን አቋም እንዳለው ያትታል።

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት "በተደጋጋሚ ከወደቁ ተቋማት ጋር ለመለያየት ቁርጠኛ መሆን" ያስፈልጋል የሚለውም የቦርዱ እምነት ነው።

ዋይት ሐውስ እንዳለው ቦርዱ "ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አንቀጽ 2803 ጋር የሚጣጣም" ነው።

ለፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቅርብ የሆኑ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ምንጭ እንዳሉት የቦርዱ ቻርተር "ከጋዛ የሚሻገር" ነው።

"ከተባበሩት መንግሥታት ሥልጣን ጋር የሚጣረስ መሆኑ ጥያቄ ያጭራል። የተመድ ሥልጣን ደግሞ መጣስ የለበትም" በማለትም ተናግረዋል።

የክዊንሲ ኢንስቲትዮት ፎር ሪስፖንሲብል ስቴትክራፍት ባልደረባ ካሊድ ኤልጊንዲ "ጋዛ መነሻው ቢሆንም የቦርዱ ሥልጣን ማብቂያ እንዳልሆነ የትራምፕ አስተዳደር ያምናል" ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ቦርዱ አሁን ያለውን የተባበሩት መንግሥታት እንዲተካ ፍላጎት እንዳለው አስተዳደሩ ጠቁሟል" ብለውም አክለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ለተመድ የምትሰጠውን ድጋፍ ቀንሷል። የፀጥታው ምክር ቤት የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ አሜሪካ መቃወሟ አይዘነጋም።

ትራምፕ የአየር ንብረት ለውጥ እና ዴሞክራሲ ላይ የሚሠሩ ተቋማትን ጨምሮ ከ31 የመንግሥታቱ ድርጅት አካል ከሆኑ ተቋማት አሜሪካ እንድትወጣ አድርገዋል።

ለዚህም ምክንያታቸው ተቋማቱ "ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒው መቆማቸው ነው" ብለዋል።

'የሰላም ቦርድ' ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሆነው ከተካተቱ መካከል የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, 'የሰላም ቦርድ' ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሆነው ከተካተቱ መካከል የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ይገኙበታል።

የሰላም ቦርዱ እንዴት ይሠራል?

ከሰላም ቦርዱ በተጨማሪ ሁለት ከፍተኛ ቦርዶችም ይፋ ተደርገዋል። አንደኛው 'ፋውንዲንግ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' የሚባል ሲሆን፤ ኢንቨስትመንት እና ዲፕሎማሲ ላይ ያተኩራል።

ሁለተኛው ደግሞ 'ጋዛ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' ይባላል። ጋዛን የማስተዳደር ሁኔታን የሚተካተል ሲሆን በሽግግር አስተዳደር ሥር በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ የሚሳተፍ ነው።

ዋይት ሐውስ እንዳለው፤ በዚህ ቦርድ ውስጥ እንዲሠሩ የተመረጡ አባላት "ለጋዛ ሕዝብ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልፅግና ለማስፈን ውጤታማ አስተዳደር እና አገልግሎት የማቅረብ" ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

'ፋውንዲንግ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' በትራምፕ ይመራል። በጋዛ መልሶ ግንባታ ዋነኛ ተሳትፎ የሚኖረው ሲሆን፤ ዋይት ሐውስ እንዳለው አባላቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ፣ የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ ልጅ ባል ጄራርድ ኩሽነር ናቸው።

የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር፤ ኢራቅ ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ አላት በሚል ሐሰተኛ ክስ እንድትወረር በማድረግ ይከሰሳሉ።

ዋይት ሐውስ በበኩሉ እያንዳንዱ የቦርዱ አባል "ለጋዛ መረጋጋት ሚና አለው" ብሏል።

በጋዛ የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጋዛ የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ

ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን ተወክለዋል?

በቦርዱ ውስጥ ፍልስጤማውያን አልተካተቱም። 'ጋዛ ኤክስኪውቲቭ ቦርድ' ውስጥ አንድ እስራኤላዊ ይገኛሉ። የሪል ስቴት ቢልየነሩ ያኪር ጋቢ እስራኤል የተወለዱ ሲሆን፣ አሁን በቆጵሮስ ይኖራሉ።

ከኳታር እና ከቱርክ ከፍተኛ ፖለቲከኞች በቦርዱ ተካተዋል። ሁለቱ አገራት የእስራኤልን የጋዛ ወረራ በጽኑ በማውገዝ ይታወቃሉ።

ፖለቲከኛው ሙስጠፋ ቤርጋቲ እንደሚሉት ፍልስጤማውያን በቦርዱ "ሰፊ ተሳትፎ" እንደሚኖራቸው ጠብቀው ነበር።

"ሆኖም ግን የተወሰነ ዓለም አቀፍ ገጽታ ቢኖርም በአመዛኙ የአሜሪካ ቦርድ የሆነ ይመስላል" ብለዋል።

በግብፅ፣ ካይሮ የሰላም ውይይት ሲደረግ ስለ ፍልስጤማውያን ሚና ቢነሳም ግልጽ እንዳልነበር ያስረዳሉ። እስራኤል የራፋህ ድንበርን ከፍታ ለጋዛ መልሶ ግንባታ መንገድ ትዘረጋለች ብለውም አያምኑም።

እስራኤል በቦርዱ ውስጥ እንዳትሳተፍ መገለሏን ከዚህ ቀደም ተናግራለች። ቦርዱ "ከእስራኤል ጋር ያልተናበበ እና ከፖሊሲዋ ጋር የሚጻረር" መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ ገልጿል።

የእስራኤል ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ያፒር ላፒድ "ለእስራኤል የዲፕሎማሲ ውድቀት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

ቀኝ ዘመሙ የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጋቪር "የጋዛ ሰርጥ 'መልሶ የማገገሚያ ኮሚቴ' አይደለም የሚያስፈልገው። ከአሸባሪው ሐማስ መጽዳት አለበት" ብለዋል።

የትራምፕ የሰላም ቦርድ በጋዛ ሰላም ያሰፍናል?

ለሁለት ዓመት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የጋዛ 80 በመቶ የሚሆነው ሕንጻ ወድሟል አልያም ተጎድቷል። የመንግሥታቱ ድርጅት እንዳለው ፍርስራሹ 60 ሚሊዮን ቶን ይመዝናል።

ተፈናቃዮች በምግብ እና መጠለያ እጥረት እየተንገላቱ ይገኛሉ። እርዳታ ሰጪዎች መሻሻል እንዳለ ቢናገሩም፤ እስራኤል ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ክልከላ መጣሏን ይገልጻሉ።

እስራኤል እርዳታ እንዲደርስ እያመቻቸች እንደሆነ እና ክልከላ የተጣለው ሐማስ የተራድዖ አገልግሎትን ለራሱ ጥቅም እንዳያውል በሚል መሆኑን አስታውቃለች።

በጋዛ እርዳታ ላለመድረሱ እስራኤል ተመድን ተጠያቂም አድርጋለች። ዋነኛው መሰናክል ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ማስጠበቅ ይመስላል።

ሐማስ ትጥቅ የሚፈታው ፍልስጤም እንደ አገር ስትቋቋም መሆኑን ገልጿል። አብዛኛውን የጋዛ ሰርጥ የሚቆጣጠረው የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከአካባቢው ለቅቆ የሚወጣው ሐማስ ትጥቅ ሲፈታ መሆኑን አሳውቋል።

የትራምፕ የሰላም ቦርድ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? ዘላቂ ሰላም ማስፈንስ ይችላል? የሚለው በሒደት የሚታይ ይሆናል።