አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ 'በጥንካሬ እና በጉልበት' ዓለምን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ፉክክር

ዚፒንግ፣ ትራምፕ እና ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC

የቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ ኃይል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ያላት የበላይነት ከዚህ በኋላ ጥያቄ ውስጥ አይገባም" ብለዋል።

አሜሪካ ኃያልነቷን አጉልታ ለማሳየት እየሞከረች ነው። ቻይና እና ሩሲያም ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት መሆናቸው እንዲታወቅ ለማድረግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

ሦስቱም አገራት አዲስ የዓለም ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚፈልጉ ተንታኞች ይናገራሉ። ተጽዕኗቸው ከአውሮፓ አልፎ በሌሎችም ቀጣናዎች የሚታይ ይሆናል።

አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ በወታደራዊ ኃይል፣ በምጣኔ ሀብት እና በፖለቲካ አማካኝነት በጎረቤት አገራት እንዲሁም በተቀረው ዓለም የሚያሳድሩትን ጫና በዚህ ዘገባ እንዳስሳለን።

'በኃይል የሚመራ' ዓለም

የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የደኅንነት ስትራቴጂ እየለወጠ ነው። ትኩረቱን ያደረገው ደግሞ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ነው።

ከትራምፕ በፊት የነበሩ ፕሬዝዳንቶች ዴሞክራትም ይሁኑ ሪፐብሊካን ትኩረታቸው የአሜሪካን ኃያልነት ዓለም አቀፍ ማድረግ ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር 'ቅድሚያ ለአሜሪካ' የሚል መፈክር አለው። በስደት፣ በወንጀል እና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች በዚህ ይመራሉ።

ከትራምፕ ከፍተኛ አማካሪዎች አንዱ ስቲቨን ሚለር ዓለም የምትመራው "በጥንካሬ፣ በጉልበት እና በኃይል" እንደሆነ በቅርቡ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ንግግራቸውን ከሄንሪ ኪሲንጀር እና ሪቻርድ ኒክሰን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ያነጻጸሩት አሉ። በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ የነበረው ፖሊስ የማያወላዳ የሚባል ነው።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ዊልያም መኬንሊ እና ቴዲ ሩዝቬልት አሜሪካ እንደ ኃያል ግዛት ገንብተዋል።

በ1823 'ሞንሮ ዶክትሪን' በሚል የወጣው መመሪያ ምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ከአውሮፓ አገራት ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን አለበት ይላል።

አሜሪካ ሁሉንም የአሜሪካ አገራት በመጠበቅ ቀዳሚ ቦታ እንዲኖራት ሩዝቬልት ይፈልጉ ነበር።

በወቅቱ አሜሪካ እንደ ቬንዙዌላ እና ዶምኒካን ሪፐብሊክ ላሉ አገራት የገንዘብ ድጋፍ ታደርግ ነበር። በሔይቲ እና ኒካራጉዋም ወታደሮቿን አሰማርታለች።

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ግዛቶችን በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር ስለማዋል ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ትራምፕ የቬንዙዌላ መሪን ለመያዝ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ከማካሄዳቸው በፊት በተከታታይ የአየር ጥቃት ሰንዝረዋል።

አሜሪካ የአየር ጥቃት የፈጸመችው አደንዛዥ ዕፅ በያዙ ጀልባዎች ላይ እንደሆነ ገልጻለች። የላቲን አሜሪካ አገራት ላይ ጫና ለማሳደር ታሪፍ ጥላለች።

በብሔራዊ ምርጫዎች ላይ አንዳንድ ዕጩዎችን ወይም ፓርቲዎችን በመደገፍም አሜሪካ ጣልቃ ትገባለች።

ትራምፕ ፓናማ ካናል፣ ግሪንላንድ እና ካናዳን ለመጠቅለል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስ ይፋ ያደረገው የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ "አሜሪካ ለደኅንነቷ እና ለዕድገቷ ስትል በምዕራብ ንፍቀ ክበብ ቀዳሚ ሆና መገኘት አለባት። ይህም በቀጣናው በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንድትገኝ ያስችላታል" ይላል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ አገሪቱ ያላትን ተጽዕኖ ከሚገዳደሩ አገራት ጋር የሚደረግ ፉክክርን ይጨምራል። ይህም በዋነኛነት ቻይናን ይመለከታል።

አሜሪካ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ገናና ለመሆን ከቻይና ጋር ትፎካከራለች።

ትራምፕ በተለያዩ አገራት ሰላም ለማስፈንም ጥረት ያደርጋሉ። ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ከአረብ አገራት ጋር የንግድ እና የደኅንነት ትስስር የማጠናከር ፍላጎት አሳይተዋል።

እሳቸው እና አማካሪዎቻቸው እንደሚሉት አሜሪካ የምዕራባውያን 'ሥልጣኔ ጠባቂ' ናት።

ለአሜሪካ ቅድሚያ የመስጠት የትራምፕ ፖሊሲ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ነው። የትራምፕ የግል አቋም አሜሪካ በዓለም አቀፍ ፖሊሲዋ ላይ የምታሳየው አቋም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ይመስላል።

በ250 ዓመታት የአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ ታይቷል። አሜሪካ ተገልላ ከመቆየት በሌሎች አገራት ጣልቃ እስከመግባት ድረስ የተለያየ አቋም አንጸባርቃለች።

የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ካለው አቅም እና ቁመና ጋር በሚመጣጠን ሁኔታ በሌሎች አገራት ጣልቃ ስትገባ ተስተውሏል።

በትራምፕ አስተዳደር ሥር የአሜሪካ የውጭ አገር ፖሊሲ ለውጥ ቢያሳይም በቀጣይ ዓመታት በጉልህ መንገድ ይቀየራል ማለት ላይሆን ይችላል።

ዚፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC

የቻይና 'ሕዳሴ'

የቻይና በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ጫና ከቀጣናዊነት ባለፈ የተለያዩ አገራትንም ያማከለ ነው። በተለያዩ አገራት ውስጥ ቻይና ያላትን ሚና መመልከት አያዳግትም።

በደቡብ ፓስፊክ፣ በማዕከላዊ እስያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በላቲን አሜሪካ እና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች የቻይና እጅ ረዥም ነው።

ቻይና በተለይም አምራች አገር መሆኗ ዓለም አቀፍ ጫና እንድታሳድር አድርጓል። በዓለም ላይ ካሉ ሸቀጦች አንድ ሦስተኛው የሚመረተው በቻይና ነው።

ከሶኬት አንስቶ አልባሳት፣ ቴሌቪዥን እና የቤት ቁሳቁሶችን ቻይና ታመርታለች።

ቻይና የዓለም ልዩ እና በብዛት የማይገኙ የተፈጥሮ ማዕድናት ያሏት አገርም ናት።

እነዚህ ማዕድናት ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የኤሌክትሪክ መኪና፣ ከነፋስ ኃይል የሚያመነጭ መሣሪያ እና የጦር መሣሪያ ለማምረት ይውሳሉ።

ከዓለም ልዩ ማዕድናት ውስጥ 90 በመቶ የሚደርሱት የሚቀናበሩት ቻይና ውስጥ ነው።

ከትራምፕ ጋር ለመደራደር የምትጠቀመውም ይሄን እምቅ ሀብት ነው። ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልከውን ማዕድን መጠን በመገደብ ለአሜሪካ ታሪፍ ምላሽ ሰጥታለች።

አሜሪካ ወደ ግሪንላንድ ማዕድናት ፊቷን ያዞረችውም ለዚህ ነው። ሁለቱ ልዕለ ኃያል አገራት የንግድ ፉክክራቸውን ቀጥለዋል።

በ2000 አካባቢ ቻይና ከአሜሪካ በመቀጠል ነበር የዓለም ንግድን የምትመራው። በ2026 ላይ ግን ነገሮች እየተለወጡ ነው።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሪ ሆነዋል።

ቻይና ከዓለም ድሃ አገራት አንዷ ከመሆን በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ወደመሆነ ተሻግራለች።

እያደጉ ያሉ አገራት ራሳቸውን ቻይና ውስጥ የሚመለከቱትም ለዚህ ነው።

ቻይና ያለ ምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የመበልጸግ ተምሳሌት ናት። የምዕራባውያንን የፖለቲካ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይከተሉ ማደግ እንደሚቻል ታሳያለች።

በ2001 (በአውሮፓውያኑ) 80 በመቶ የሚሆኑ የዓለም አገራት ከአሜሪካ ጋር የንግድ አጋር ነበሩ። አሁን ግን 70 በመቶው ከቻይና ጋር የንግድ ትስስር አላቸው።

ቻይና እያደጉ ባሉ አገራት ላይ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግም ትታወቃለች። 'ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ' እስያ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ በየብስ እና በባሕር የሚተሳሰሩበት ፕሮጀክት ነው።

ቻይና በወደብ፣ በመንገድ እና በኃይል አቅርቦት ግንባታ ዋነኛ ተሳታፊ ሆናለች። በዚህም ብዙ አገራት የቻይና የገንዘብ ዕዳ አለባቸው።

ዚፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC

ትራምፕ በቬንዙዌላ ዘመቻ ካካሄዱ በኋላ ቻይናም ታይዋንን ልትወር ትችል ይሆን? የሚለው ጥያቄ ተስተጋብቷል።

ቻይና ታይዋንን እንደ ራስ ገዝ ደሴት ብትወስዳትም፤ አንድ ቀን ከግዛቷ ጋር እንደምተጠቃለል ታምናለች።

ቻይና ታይዋንን የመውረር ሳይሆን ቀስ በቀስ የማዳከም ስትራቴጂዋን እንደምትቀጥል ተንታኞች ይናገራሉ።

ታይዋን በሚያድርባት ጫና ምክንያት ወደ ድርድር ታመራለች ብለውም ይገምታሉ።

ዢ ጂንፒንግ ቻይና 'ታላቅ ሕዳሴ' ውስጥ ያለች አገር መሆኗን ይናገራሉ። ወታደራዊ ትዕይንት ሲመለከቱ የቻይናን ማንሰራራት "የሚያስቆም ኃይል የለም" ብለዋል።

በዶናልድ ትራምፕ ሥር ያለው የዓለም ነውጥ "የሕዳሴው መንገድ" እንደሆነ በመግለጽ፤ ዓለም ወደ ቻይና የሚያማትርበት ዘመን ሩቅ እንዳልሆነ ያምናሉ።

ዓለም መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደሆነች እና የተሻለው አማራጭ የቻይናን መንገድ መከተል እንደሆነ ጂንፒንግ ይናገራሉ።

'የቅርብ ሩቅ' ሩሲያ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሶቪየት ኅብረት መንኮታኮት "የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቁ ጂኦፖለቲካል ውድቀት ነው" ሲሉ በአንድ ወቅት ተናግረዋል።

ፑቲን ቀድሞ የሶቪየት ኅብረት ግዛት ስለነበሩ እና ነጻነታቸውን ስላወጁ ግዛቶች ሲናገሩ 'ዘ ኒር አብሮድ' የተባለ አገላለጽ ይጠቀማሉ።

እነዚህ አገራት ራሳቸውን ችለው የመቆም መብታቸው የተወሰነ ገደብ እንዳለው ለመጠቆም የሚውል አገላለጽ ነው። 'የቅርብ ሩቅ' በሚል ሊተረጎም ይችላል።

ሩሲያ በእነዚህ አገራት ውስጥ ያላትን ፍላጎት ሕጋዊ ቁመና ትሰጠዋለች። ክሬምሊን በሩሲያ እና በአገራቱ መካከል ስላለው ድንበር እና ስለ ድንበሩ ምን እንደሚያስብ በግልጽ የማያስታውቀው ሆነ ብሎ እንደሆነ ይታመናል።

ክሬምሊን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ግልጽ ስላልሆነ ጥልቀቱን በግልጽ ለማወቅ ያዳግታል።

ፑቲን በአንድ ወቅት የሩሲያ ድንበር "ወሰን የለውም" ብለው ተናግረዋል። አንዳንዶች ንግግሩን የመስፋፋት ፖሊሲ አድርገው ይወስዱታል።

በታሪክ የሩሲያ አካል የነበሩ ግዛቶች እና ሌሎችም አካባቢዎችን ወደ ሩሲያ የመጠቅለል አካሄድ እንደሆነ ይነገራል።

ሩሲያ ከዩክሬን የወሰደቻቸውን ግዛቶች "ታሪካዊ" የምትላቸውም ለዚህ ነው።

ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC

ክሬምሊን በይፋ የሚገልጸው የቀድሞ የሶቪየት ግዛቶችን ሉዓላዊነት እንደሚያከብር ነው።

ግን ደግሞ በአገራቱ ውስጥ "ፍላጎቶች" እንዳሉትም ይጠቅሳል።

እነዚህ አገራት ከሩሲያ ቁጥጥር ውጭ ለመውጣት ሲሞክሩ በምጣኔ ሀብት እና በወታደራዊ ኃይል ጫና ታሳድራለች።

ዩክሬን ከሶቪየት ኅብረት ከወጣች በኋላ ለዓመታት ከክሬምሊን እምብዛም የማይቃረን ፖሊሲ ስታራምድ ቆይታለች። በክሬሚያ ጥቁር ባሕር ላይ የሩሲያ የባሕር ኃይል መቀመጫ መገንባቱ ለዚህ ማሳያ ነበር።

ከዚህ አካሄድ ማፈንገጥ ዋጋ እንደሚያስከፍልም በጦርነቱ ታይቷል።

ለምዕራባውያን ቅርብ የሆኑት እና ለውጥ የሚፈልጉት ፕሬዝዳንት ቪክቶር ዩሺቼንኮ ሲመሩ ነገሮች ተለወጡ።

በአመራር ዘመናቸው ሁለት ጊዜ ሩሲያ የጋዝ አቅርቦት አቋርጣለች።

የምጣኔ ሀብት እና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ውጤት አላሳይ ሲል ሩሲያ ክሬሚያን ወረረች እና በ2014 ግዛቱን ጠቀለለች።

በ2022 ደግሞ ሩሲያ ዩክሬንን ወርራለች።

ሩሲያ ከጆርጂያ ጋር በ2008 ጦርነት ውስጥ ገብታለች። በጦርነቱ ሩሲያ 20 በመቶ የጆርጂያ ግዛትን ጠቅልላለች።

ከዚያ ጊዜ አንስቶ የሩሲያ ወታደሮች ግዛታቸውን የበለጠ ወደ ጆርጂያ ለማስፋፋት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ይሄንንም "አዝጋሚው መስፋፋት" ብለው የሚገልጹት አሉ።

ሩሲያ ጆርጂያን እና ዩክሬንን ስትወር የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት አለመኖሩ ፑቲን "የቅርብ ሩቅ ግዛቶችን" መጠቅለል መብታቸው እንደሆነ እንዲሰማቸው አድርጓል።

ከቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባል አገራት መካከል ቤላሩስ፣ ታጃኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ካዛክስታን እና አርሜንያ ከሩሲያ ጋር ቅርብ ግንኙነት አላቸው። የሩሲያ ወታደሮችም በግዛቶቻቸው እንዲሰፍሩ ፈቅደዋል።

ጆርጂያ እና ዩክሬን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት በመሞከራቸው እና ከምዕራቡ ዓለም ጋር በመቀራረባቸው ከሩሲያ ጋር ተጋጭተዋል።

በታሪክ የሚታወቁ ጦርነቶች የአንድን አገር ፍላጎት ከማስጠበቅ እና በቁጥር ውስን የሆኑ ማኅበረሰቦችን ከመከላከል ጋር የተያያዙ አመክንዮዎች ተሰጥተዋቸዋል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የዓለም ሕዝቦች በእኩል እንዲታዩ የማድረግ ንቅናቄዎች ተስተውለዋል።

አገራት ያላቸው የጦር መሣሪያ እና ግዝፈታቸው ወይም ትንሽነታቸው ከግምት ሳይገባ እኩልነት እንዲሰፍን ቢፈለግም ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን የሚደረገው ፉክክር ወደቀደመው የጨለማ ዘመን የሚወስድ ይመስላል።