አውሮፓን ክፉኛ ነቅፎ፣ ቻይናን እና ሩሲያን በዝምታ ያለፈው የትራምፕ አዲሱ የደኅንነት ስትራቴጂ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
የትራምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ በአሜሪካ የቅርብ አጋሮች መካከል ስጋት ፈጥሯል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ለዓመታት የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ ከመሠረቱት መርሆዎችም በእጅጉ ያፈነገጠ ነው።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ አስተዳደር ይፋ ያደረገው ባለ 33 ገጽ ሰነድ ዓለምን በዋናነት እንደ ኢኮኖሚያዊ ማዕከል አድርጎ ያቀርባል። በዚህም የተነሳ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እና የኢኮኖሚ ብሔርተኝነትን ከዴሞክራሲ መስፋፋት በላይ ከፍ አድርጎ አቅርቧል።
ስትራቴጂው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ከዘረዘራቸው ነጥቦች መካከል የውጭ ተጽዕኖን መዋጋት፣ በስፋት የሚደረግ ስደትን ማስቆም እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ አለ የተባለው "ሳንሱር" መቃወም የሚሉት ይገኙበታል።
በርካታ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት እና ተንታኞች ሰነዱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገበት ምክንያት ላይ ጥያቄ በማንሳት ትችታቸውን አሰምተዋል።
የቢቢሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘጋቢ ቶም ባተማን ለዘ ግሎባል ስቶሪ ፖድካስት የትራምፕ አስተዳደር የሚከተለውን "ርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከቶችን" በሚገባ ያሳያል ብሏል።
ሰነዱ እንደ ሩሲያ ወይም ቻይና ያሉ ተገዳዳሪዎችን የሚተች ሃሳብ አልሰፈረበትም፤ ይህም ብዙ ታዛቢዎችን ያስገረመ ሆኗል።
በምትኩ፣ ለአውሮፓ ጠንካራ ቃላትን በመጠቀም ትችቶችን ሰንዝሯል። ይህም በዚህ ሳምንት በአውሮፓ ዋና ከተሞች ላይ ስጋት ፈጥሯል።
'የሥልጣኔ መጥፋት'
ቀደም ሲል የነበሩት የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ስልቶች ከአውሮፓ አገሮች ጋር በሚኖሩ የጋራ እሴቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ይህ ሰነድ ግን የተለየ መንገድ መጓዝን መርጧል።
በአውሮፓ አሁን ያለው አዝማሚያ ከቀጠለ አህጉሪቱ "በ20 ዓመታት ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ የማትታወቅ" እንደምትሆን ሰነዱ ይጠቅሳል።
የአውሮፓ "ሥልጣኔ" ላይ የተጋረጠው "የመጥፋት" አደጋ የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ካስከተሉት ችግር ይልቅ "እውነተኛ እና ይበልጥ ግልጽ" ሆኖ እንደሚታይም ያብራራል።
በተጨማሪም የአውሮፓ አገራት ባለ ብዙ ወገን ተቋማት እና የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን በመቀበላቸው የተነሳ በ"ምዕራባዊ ማንነት" ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው ሲል ሰነዱ ይተቻል።
በአንድ የሰነዱ ክፍል፣ ስትራቴጂው አውሮፓ "የሥልጣኔ መጥፋት" እያጋጠማት መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል።
የአውሮፓ መሪዎች፣ ቢያንስ በግል፣ በሰነዱ "ደንግጠዋል" ሲል ቶም ባተማን ለፖድካስቱ ተናግሯል።
"ይህ የአስተዳደሩ ርዕዮተ ዓለማዊ አቋም መሆኑ አያስደንቃቸውም፤ ነገር ግን በመደበኛ የፖሊሲ ሰነድ ውስጥ ሲገለጽ ማየት በጣም አሳሳቢ ነው" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ እና የአውሮፓ ግንኙነት መካከል ንፋስ መግባቱ ለወራት በግልጽ ታይቷል።
የትራምፕ አስተዳደር ለአውሮፓ ያለውን አመለካከት የሚያሳዩት የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች የታዩት ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በሙኒክ የጸጥታ ጉባዔ ላይ በአውሮፓ ዲሞክራሲዎች ላይ ከባድ ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት ነው።
በዚህ ጉባዔ ላይ መሪዎች መራጮች ስለ ፍልሰት እና የመናገር ነፃነት ያላቸውን ስጋትን ችላ በማለታቸው ተችተዋል።
ግን ደግሞ በተግባር በሌላ መድረክ ላይ በግልጽ ተስተውሏል፤ በዩክሬን ጦርነት።
ሰነዱ አውሮፓ ያለውን የኃይል ተለዋዋጭነት በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳች እና ዩናይትድ ስቴትስ ቀጠናውን ለማረጋጋት የዲፕሎማሲ ኃይል መጠቀም እንዳለባት የሚጠቁም ይመስላል።
ይህ የስትራቴጂ ሰነድ የአውሮፓ ኅብረትን አሜሪካ የዩክሬን ጦርነት ለማስቆም የምታደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ተጠያቂ ያደርጋል።
ሰነዱ አሜሪካ "ለሩሲያ ስትራቴጂካዊ መረጋጋትን እንደገና መፍጠር" አለባት የሚል ሲሆን ይህም "የአውሮፓን ኢኮኖሚ ያረጋጋል" ይላል።
ዋናው መልዕክት ዩክሬን አዋጭ አገር ሆና መቀጠል አለባት የሚለው ነው፤ ነገር ግን ይህ የሩሲያን የበላይነት መቀበልን ይጠይቃል።
የቢቢሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘጋቢ ዶናልድ ትራምፕ አውሮፓ እና ዩክሬን ላይ "ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ ነው" ሲል ተናግሯል።
"ግልጽ ነው... ዩክሬናውያን በመሠረቱ እንደ እጅ መስጠት አድርገው የሚቆጥሩትን አቋም ለመቀበል አውሮፓውያን ጫና ውስጥ ናቸው" ሲል ቶም ባተማን በፖድካስቱ ላይ ያለውንሁኔታ ያብራራል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዩክሬን ዙሪያ የተፈጠረው ውጥረት ቀደም ሲልም ጎልቶ ታይቷል።
ከእነዚህም መካከል ትራምፕ እና ምክትላቸው ቫንስ በዋይት ሐውስ ኦቫል ኦፊስ በየካቲት ወር ከፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ወቅት ፕሬዚዳንቱን "አክብሮት እና ምስጋና የጎደለው" በሚል ተችተዋል።
የአውሮፓ መሪዎች አሜሪካ ከኪየቭ ይልቅ ከሞስኮ ምርጫ ጋር በጣም የቀረበ ውጤት እንዲመጣ ልትገፋ ትችላለች የሚለውን እውነታ እየተጋፈጡ ነው።
ሩሲያ የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂውን ከራዕያቸው ጋር "በአብዛኛው የሚጣጣም" በማለት በደስታ እንደምትቀበለው ገልጻለች።
'የትራምፕ ምክረ ሃሳብ'
አዲሱ ስትራቴጂ አውሮፓን ከመተቸት ጎን ለጎን "ምዕራባዊው ንፍቀ ክበብ" በመባል የሚታወቀውን ቀጠና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ትኩረት አድርጎ ገልጾታል።
አስተዳደሩ "ቀጠናው ወደ አሜሪካ የሚደረገውን የጅምላ ፍልሰት ለመከላከል እና ለማስቆም የተረጋጋ እና መልካም አስተዳደር እንዲኖረው ማረጋገጥ ይፈልጋል" ይላል ሰነዱ።
ይህ ስትራቴጂ ከሞንሮ አስተምህሮ ጋር የ"ትራምፕን ምክረ ሃሳብ" ያስተዋውቃል።
የአስተዳደሩ አካሄድ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ፕሬዚዳንት ጄምስ ሞንሮ የአሜሪካን የበላይነት በሚመለከት የያዙት ፖሊሲ ተከታይ ተደርጎ ታይቷል።
ምንም እንኳን ቻይና በቀጥታ በሰነዱ ውስጥ ባትጠቀስም አስተዳደሩ ቻይና በላቲን አሜሪካ ያላትን ተጽዕኖ ለመግታት ይህንን አዲስ ትኩረት አስፈላጊ አድርጎ ይወስደዋል ሲል ቶም ባተማን ለፖድካስቱ አስረድቷል።
እንደ ትራምፕ ገለጻ፣ ምንም እንኳን የፓናማ ቦይን "እየተጠቀመች ነው" የሚለው ሀሳብ እውነት ባይሆንም ቻይና በአካባቢው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም አግኝታለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ወደ ላቲን አሜሪካ አገሮች ያደረጉትን ጉብኝት ጨምሮ የቅርብ ጊዜ የዲፕሎማሲ ጥረቶች፣ ዋሽንግተን በክልሉ ውስጥ በኢኮኖሚያም ሆነ በስትራቴጂ የበላይነትን እንደገና ለማግኘት ያላትን ፍላጎት ያመለክታሉ።
ስትራቴጂው በዚህ ፖሊሲ ወታደራዊ ገጽታ ላይ ባያተኩርም፣ በካሪቢያን በሚገኙ የዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚሰነዘረው የአየር ጥቃት ዘመቻ እና በርካታ የአሜሪካ የጦር መርከቦች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር ኃይሎች በቬንዙዌላ የባሕር ዳርቻ መኖራቸው የወታደራዊ ኃይል ስጋትን ያጎላል።
አዲሱ የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ በዋሽንግተን እና በመላው አውሮፓ የተነሱ ክርክሮችን እንደገና ቀይሯል።
ይህ በዩክሬን፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ግንኙነት እንዲሁም በሰፊው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ላይ ያለው አንድምታ አሁንም እየተገለጠ ነው።
ነገር ግን ሰነዱ አንድ ነገር በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ያደርጋል፤ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንደገና ለመበየን ያቀደ ሲሆን አጋሮቹም ከዚያ አዲስ እውነታ ጋር እንዲላመዱ ይጠብቃል።















