ሩሲያ፤ አዲሱ የአሜሪካ የደኅንነት ስትራቴጂ ከራዕይዋ ጋር እንደሚጣጣም ገለጸች

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ሩሲያ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት አዲስ የደኅንነት ስትራቴጂ ከሞስኮ ከራዕይ ጋር "በብዙ መልኩ የሚጣጣም" እንደሆነ በመግለጽ አደነቀች።

የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ባለ 33 ገጹን የስትራቴጂ ሰነድ፤ አውሮፓ "የስልጣኔ ስረዛ" እያጋጠማት እንደሆነ የሚተነትን ነው። ሰነዱ ሩሲያን ለአሜሪካ ስጋት እንደሆነች አገር አድርጎ አያቀርብም።

ስትራቴጂው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ከዘረዘራቸው ነጥቦች መካከል የውጭ ተጽዕኖን መዋጋት፣ በስፋት የሚደረግ ስደትን ማስቆም እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ አለ የተባለው "ሳንሱር" መቃወም የሚሉት ይገኙበታል።

በርካታ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት እና ተንታኞች ሰነዱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገበት ምክንያት ላይ ጥያቄ በማንሳት ትችታቸውን አሰምተዋል። ስትራቴጂው ላይ የሰፈረውን የቃላት ምርጫ እና አገላለጽን የሩሲያ መንግሥት ከሚጠቀመው ጋር አመሳስለውታል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔሽኮቭ በሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል በሆነው 'ታስ' ላይ በወጣ ቃለ መጠይቅ፤ "እየተመለከትነው ያለነው ማስተካከያ... በብዙ መልኩ ከእኛ ራዕይ ጋር የሚጣጣም ነው" ሲሉ ሰነዱን አድንቀዋል።

"ይህንን በጎ እርምጃ እናጤነዋለን" ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ሞስኮ ጠንካራ ድምዳሜ ላይ ከመድረሷ በፊት ሰነዱን መተንተኗን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

የትራምፕ አስተዳድር አዲስ ስትራቴጂ ሩሲያን በተመለከተ ለስለስ ያሉ ቃላትን ተጠቅሞ ተስተውሏል።

የዩክሬንን ጦርነት ለመቋጨት ጥረት እያደረጉ ያሉት የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት፤ ሰነዱ በሩሲያ ላይ የተለሳለሰ መሆኑ ዋሽንግተን ሞስኮ ላይ የተዳከመ አቋም ልትይዝ ትችላለች የሚል ስጋት ጭሮባቸዋል።

ስትራቴጂው፤ አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት የምታደርገው ጥረት በአውሮፓ ኅብረት እንደተደናቀፈ በመጥቀስ ይወቅሳል። አሜሪካ "ከሩሲያ ጋር ስትራቴጂክ መረጋጋትን በድጋሚ መገንባት" እንዳለባት እና ይህም በምላሹ "የአውሮፓን ኢኮኖሚ እንደሚያረጋጋ" ያትታል።

ሰነዱ፤ በአህጉሩ ላይ በሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እየተደረገ ያለውን ፖሊሲ የሚደግፍ ይመስላል። የአሜሪካ ፖሊሲ "ከአውሮፓ እና አውሮፓውያን አገራት ጋር እየተከተለች ያለውን አሁናዊ አካሄድ መቃወም" ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳል።

"ምዕራባዊ ማንነት" እንዲመለስ ጥሪውን የሚያቀርበው አዲሱ ስትራቴጂ፤ "በ20 ዓመት ወይም ባነሰ ጊዜ ውስጥ" አውሮፓን "መለየት የማይቻልበት" ደረጃ ላይ እንደሚደረስ ያስጠነቅቃል። የአውሮፓ "ሥልጣኔ" ላይ የተጋረጠው "የመጥፋት" አደጋ የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ካስከተሉት ችግር ይልቅ "እውነተኛ እና ይበልጥ ግልጽ" ሆኖ እንደሚታይም ያብራራል።

"አንዳንድ የአውሮፓ አገራት አስተማማኝ አጋር ሆነው ለመቆየት የሚያስችል ጠንካራ ኢኮኖሚና ወታደራዊ አቅም ያላቸው መሆን አለመሆናቸው ግልጽ አይደለም" ብሏል።

ሰነዱ ባልተጠበቀ ሁኔታ "አርበኛ የአውሮፓ ፓርቲዎች" የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ አድንቆ አቅርቧል። "አሜሪካ፤ በአውሮፓ የሚገኙ የፖለቲካ አጋሮቿ የሚያቀነቅኑትን ይህንን የመንፈስ መነቃቃት ታበረታታለች" ሲል ለብሔርተኛ ፖለቲከኞች አጋርነቱን አሳይቷል።