ዘለንስኪ በአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ላይ በሚደረገው ውይይት መሻሻል እንደታየ ፍንጭ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ የሰላም ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት አማች ያሬድ ኩሽነር ጋር "በጣም ገንቢ" የስልክ ጥሪ እንዳደረጉ ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ያላትን ጦርነት ለማስቆም የሚደረግ ስምምነትን ተግበራዊ ማድረጓን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል መወያየታቸውን እና ከአሜሪካ ጋር መሥራት ለመቀጠል "ቁርጠኛ" መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ ለሦስተኛ ቀን ውይይት ላይ ከሚገኙበት ከማያሚ የስልክ ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
ሞስኮ ምንም ዓይነት ስምምነት ያደረገች አይመስልም። በዩክሬን ላይ ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ ማድረጓንም ቀጥላለች።
"ዩክሬን ሰላምን ለማምጣት ከአሜሪካ ጎን በቅን ልቦና መሥራቷን ለመቀጠል ቆርጣ ተነስታለች" ሲሉ ዘለንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
"ብዙ ገጽታዎችን ሸፍነናል፤ የደም መፋሰስን ለማስቆም እና አዲስ የሩሲያ ሙሉ ወረራ ስጋትን ለማስወገድ የሚያስችሉ ቁልፍ ነጥቦች ላይም ተወያይተናል።"
ሩሲያ በአንድ ሌሊት በዩክሬን ላይ ተጨማሪ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃቶችን ያደረገች ሲሆን የዩክሬን የአውሮፓ ኅብረት አጋሮች ጥቃቶቹን አውግዘዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በማኅበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልዕክት ከዘለንስኪ ጋር እንደተነጋገሩ እና "ሙሉ አጋርነታቸውን" እንዳቀረቡ ተናግረዋል።
"ፈረንሳይ ግጭቶችን ለማርገብ እና የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ከሁሉም አጋሮች ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ ነች" ሲሉ ማክሮን አክለዋል።
ቀደም ሲል ማክሮን ሰኞ ዕለት በለንደን በሚደረገው ውይይት ከዘለንስኪ፣ ከዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እና ከጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርዝ ጋር እንደሚቀላቀሉ አረጋግጠዋል።
አራቱ መሪዎች የዩክሬንን ከጦርነት በኋላ ደኅንነት ለማረጋገጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ የታለሙ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት መካከል ስለሚደረጉ ውይይቶች ይነጋገራሉ።
ከሁለት ሳምንታት በፊት አራቱ መሪዎች በበይነ መረብ ተገናኝተው የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደረግ ወደ ዩክሬን ሊሰማራ ስለሚችል የአውሮፓ የሰላም አስከባሪ ኃይል ተወያይተዋል።
ሰር ኪር ዩክሬን የራሷን የወደፊት ሁኔታ መወሰን እንዳለባት በተደጋጋሚ አፅንዖት ሰጥተዋል። የበጎ ፈቃደኞች የሰላም አስከባሪ ኃይል ጥምረት የአገሪቱን ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ "ወሳኝ ሚና" እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወደ ዩክሬን የተሰማሩ ወታደሮች "የጥቃት ዒላማዎች" ይሆናሉ በማለት እንዲህ ዓይነቱን ኃይል የሚደግፍ ሐሳብ ውድቅ አድርገዋል።
ሩሲያ አርብ ምሽት 653 ድሮኖች እና 51 ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች ሲሉ የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
አንድ ጥቃት በኪየቭ ደቡብ ምዕራብ ፋስቲቭ ከተማ በሚገኝ የባቡር መስመርን በመምታቱ ዋናውን የጣቢያ ሕንፃ አውድሟል።
የዩክሬን የኢነርጂ ሚኒስቴር የሩሲያ ጥቃቶች በስምንት ክልሎች ውስጥ ባሉ የኢነርጂ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በመግለጽ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አስከትሏል ብሏል።
ሩሲያ ወታደራዊ-ኢንዱስትሪ ቦታዎችን እና የኢነርጂ እና የወደብ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ እንዳደረገች ተናግራለች።
የአሜሪካ እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩሲያ በሞስኮ የተካሄደው ውይይት ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ "ለረዥም ጊዜ ሰላም ከፍተኛ ቁርጠኝነት" እንድታሳይ አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን በአሜሪካ የቀረበውን ሰላም ዕቅድ እንድትቀበል ለማሳመን በፍሎሪዳ በዩክሬን እና በአሜሪካ ባለሥልጣናት መካከል የሚደረገው ውይይት ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።
አርብ ዕለት በወጣ መግለጫ ዊትኮፍ የዩክሬን ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ፀሐፊ ከሩስቴም ኡሜሮቭ ጋር ለሁለት ቀናት የተደረገው ውይይት "ገንቢ" እንደነበር ተናግረዋል።
የጋራ መግለጫቸው ዊትኮፍ እና ኡሜሮቭ "በደኅንነት ዝግጅቶች ማዕቀፍ ላይ ተስማምተዋል" እና "ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስፈልጉትን የመከላከያ አቅም ተወያይተዋል" ሲል ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ጠቁሟል።
ጦርነቱን የማቆም ተስፋ ያለው ሩሲያ "ግጭቶችን ለማርገብ እና ግድያ ለማስቆም" እርምጃዎችን ለመውሰድ ባላት ዝግጁነት ላይ ነው ሲል መግለጫው አክሏል።















