የአሜሪካ እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች ወደ ሰላም የሚደረገው "ትክክለኛ ጉዞ" የሚወሰነው በሩሲያ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ እና ዩክሬን ከፍተኛ ተደራዳሪዎች አርብ ዕለት በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ውጤታማ ውይይት ማካሄዳቸውን ከገለፁ በኋላ ወደ ሰላም የሚደረገው ጉዞ የሚወሰነው በሩሲያ መሆኑን ተናገሩ።
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ከዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር በመሆን በጋራ ባወጡት መግለጫ "የትኛውም ወደ ስምምነቱ የሚደረግ ትክክለኛ ውጤት የሚወሰነው ሩሲያ ለዘላቂ ሰላም ባላት ዝግጁነት ላይ ነው፤ ይህም ግጭቶችን ለማርገብ እና ግድያዎችን ለማስቆም የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያካትታል" ብለዋል።
በስብሰባው ወቅት ሁለቱ ወገኖች "በደህንነት ጉዳዮች ማዕቀፍ ላይ" የተስማሙ ሲሆን በመከላከያዎቹ ዙሪያም ተወያይተዋል።
ማክሰኞ ዕለት በሞስኮ የተደረገው ውይይት ለአራት ዓመት ገደማ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስቸል የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ አላስቻለም።
በዊትኮፍ እና ኩሽነር እንዲሁም በዩክሬን ብሔራዊ ደህንነት ፀኃፊ ሩስተም ኡሜሮብ እና ብርጋዴር ጄነራል አንድሪ ሀናቶቭ መካከል የተካሄደው የሁለት ቀን ስብሰባ በሁለት ሳምንት ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ የተደረገ ነው።
ተደራዳሪዎቹ ቅዳሜ ዕለት በድጋሚ ፍሎሪዳ ውስጥ ይገናኛሉ ተብሏል።
የአሜሪካ ልዑካን እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ የዩክሬን ቅድሚያ የምትሰጣቸው "ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ አካባቢዎቸን ማስጠበቅ፣ የዩክሬናውያንን ደህንንት ማረጋገጥ እንዲሁም ወደፊት ዲሞክራሲያዊ የሆነ ጊዜ እንዲኖር መሠረት መጣል" ናቸው።
የአሜሪካ ተወካዮች ማክሰኞ ዕለት ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ስለነበራቸው ንግግር አንስቶ የተወያዩ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዩክሬን ከጦርነቱ በኋላ ስለሚኖራት ዕድል፣ የፈራረሱትን የአገሪቱን ግዛቶች ስለመገንባት እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር ስለሚኖር የምጣኔ ኃብት ትስስር ተነጋግረዋል።
የተኩስ አቁም ላይ መድረስ እና ውጥረቶችን ማርገብ "ዳግም ወረራዎችን ለመከላከል እና የዩክሬን በአጠቃላይ መልሶ የማልማት ዕቅድን እውን ለማድረግ፣ አገሪቱ ከጦርነቱ በፊት ከነበረችው የበለጠ ጠንካራ እና የበለፀገች እንድትሆን" ያደርጋል ብለዋል።
በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል አሁንም መፍትሄ ያልተገኘላቸው ሁለት አጨቃጫቂ ጉዳዮች ይቀራሉ።
እነዚህም በሩሲያ ወታደሮች የተያዙ የዩክሬን ግዛቶች እና ለዩክሬን የሚሰጥ የደህንነት ዋስትና ናቸው።
ማክሰኞ ዕለት ዊትኮፍ እና ፑቲን ለአምስት ሰዓታት ያህል የተወያዩ ሲሆን ክሬምሊን ጦርነቱን ለማቆም "ምንም ማመቻመች እንደሌለ" አስታውቋል።
በትራምፕ የመጀመርያ የሥልጣን ዘመን በዋይት ሐውስ አማካሪ ሆኖ ያገለገለው የሪል ስቴት ኢንቬስተሩ እና ነጋዴው ኩሽነር በዚህ ውይይት ወቅት ተሳታፊ ነበር።
ትራምፕ የተደረጉት ውይይቶች "አጥጋቢ" ነበሩ ያሉ ሲሆን ነገር ግን ምን እንደሚፈጠር ለመናገር ጊዜው ገና ነው ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ "ዓለም ጦርነቱ የሚያበቃበት ዕድል መኖሩ ይሰማዋል" ነገር ግን ድርድሮቹ "ሩሲያ ላይ በሚደረግ ጫና የታገዙ መሆን አለባቸው" ብለዋል።















