ፑቲን የዩክሬን ወታደሮች ዶንባስን እንዲለቁ ካልሆነ ሩሲያ በኃይል እንደምትቆጣጠረው አስጠነቀቁ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Alexander Nemenov/Pool via REUTERS

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን ወታደሮች ምሥራቃዊ ዶንባስን መልቀቅ እንዳለባቸው በድጋሚ አስጠነቀቁ። ይህ ሳይፈጸም በዩክሬን ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ሊቆም እንደማይችል ይፋ አድርገዋል።

"የዩክሬን ወታደሮች እነዚህን ግዛቶች ለቅቀው ይወጣሉ ወይም በኃይል ነፃ እናወጣቸዋለን" ሲሉ ለኢንዲያ ቱዴይ ተናግረዋል። ሞስኮ 85 በመቶው የሚሆነውን የዶንባስ ክፍል ትቆጣጠራለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ግዛታቸውን መልቀቅን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል።

የፑቲን አስተያየት የተሰማው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን የሰላም ዕቅድ ተደራዳሪዎች በሞስኮ ከተደረገ ውይይት በኋላ የሩሲያው መሪ "ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋሉ" ብለው መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።

ሞስኮ የነበሩት የትራምፕ ተወካይ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬን ልዑካንን በፍሎሪዳ ለማገናኘት አቅደዋል።

ማክሰኞ በክሬምሊን የተደረጉት ውይይቶች "ጥሩ የሚባሉ" እንደሆኑ የተናገሩት ትራምፕ፤ "የሁለቱንም አካላት ፍላጎት" ስለሚጠይቅ ምን እንደሚፈጠር ለመናገር በጣም ገና እንደሆነ አክለዋል።

የአሜሪካ የመጀመሪያው የሰላም ዕቅድ አሁንም በዩክሬን ቁጥጥር ስር ያሉ የዶንባስ ቦታዎችን ጨምሮ ለፑቲን ለማስረከብ ሀሳብ ቢቀርብበትም፤ የዊትኮፍ ቡድን በሞስኮ አዲስ ሃሳብ ማቅረባቸው ታውቋል።

ፑቲን በዴልሂ ከሚያደርጉት ይፋዊ ጉብኝት በፊት ከኢንዲያ ቱዴይ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ በዊትኮፍ እና በጃሬድ ኩሽነር የቀረበውን አዲሱን ዕቅድ እንዳላዩ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ለዚህም ነው እያንዳንዱን ነጥብ መከለስ የነበረብን፣ ይህም ረዥም ጊዜ ፈጅቷል" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ሞስኮ ከአንዳንድ የአሜሪካ ሃሳቦች ጋር እንደማትስማማ ተናግረዋል።

"አንዳንድ ጊዜ አዎ ስለዚህ ጉዳይ መወያየት እንችላለን ብንልም ግን ላንስማማበት እንችላለን" ሲሉ ፑቲን ተናግረዋል።

ነጥቦቹን ግን አልጠቀሱም። በሩሲያ ኃይሎች የተያዙት የዩክሬን ግዛቶች ዕጣ ፈንታ እና የዩክሬን የደህንነት ዋስትናዎች ዋነኛዎቹ አከራካሪ ነጥቦች ናቸው።

የፑቲን ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ አማካሪ እና ቁልፍ ተደራዳሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ቀደም ሲል ከውይይቱ በኋላ እንደተናገሩት ጦርነቱን ለማስቆም "ምንም ዓይነት የሃሳብ ለውጥ" እንዳላደረጉ ተናግረዋል።

ኡሻኮቭ አክለውም ሞስኮ በቅርቡ በጦር ሜዳ ላይ ባሳየቻቸው ስኬቶች ምክንያት የሩሲያ የመደራደር አቋም ተጠናክሯል ብለዋል።

ሩሲያ ማንኛውንም የተኩስ አቁም ስምምነት በተደጋጋሚ አቋርጣ ተጨማሪ የዩክሬን ግዛት ለመያዝ ትፈልጋለች ስትል ዩክሬን ትከሳለች።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢያ "የዓለምን ጊዜ እያባከኑ ነው" ሲሉ ፑተንን በመውቀስ ለክሬምሊን ሃሰቦች ምላሽ ሰጠዋል።

ዩክሬን ማንኛውም ስምምነት ለዩክሬን ጠንካራ የደህንነት ዋስትናዎችን ሊሰጥ ይገባል ስትል ለረጅም ጊዜ አጥብቃ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ረቡዕ ዕለት ዜሌንስኪ "ዓለም ጦርነቱን ለማስቆም እውነተኛ ዕድል እንዳለ በግልጽ ይሰማዋል" ብለዋል። ነገር ግን ድርድሩ "በሩሲያ ላይ ባለው ጫና በማሳደር ሊደገፍ ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።

ኪየቭ እና የአውሮፓ አጋሮቿ ሩስያ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ሆን ብላ ታቋርጣለች ሲሉ ይከሳሉ።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ ተደራዳሪዎቻቸው ለሞስኮ የሚደግፍ ነው በተባለው ዋናው የአሜሪካ የሰላም ዐዕቅድ ላይ አንዳንድ ቁልፍ ለውጦችን ማድረግ ችለዋል ብለዋል።

የአሜሪካ እና የዩክሬን ተደራዳሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ "የተሻሻለ የሰላም ማዕቀፍ" እንዳዘጋጁ ተናግረዋል። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።

ከአውሮፓ የመጡ ከፍተኛ ተደራዳሪዎች ባለፈው ሳምንት በስዊዘርላንድ ከዩክሬን እና ከአሜሪካ ቡድኖች ጋር ለብቻቸው ተገናኝተዋል።

የጀርመን ዴር ስፒገል የዜና ድረ-ገጽ የአውሮፓ መሪዎች በአሜሪካ የሠላም ዕቅድ ላይ ያላቸውን ስጋት የገለጹበትን ሚስጥራዊ ቅጂ እንዳገኘ ዘግቧል።

"አሜሪካ በደህንነት ዋስትናዎች ላይ ግልጽነት ሳይኖር የዩክሬን ግዛቶችን አሳልፋ ልትሰጥ ትችላለች" ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሰኞ ዕለት በተደረገው ስብሰባ ላይ መናገራቸውን የእንግሊዝኛው ቅጂ ያመለክታል።

የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ በበኩላቸው ዜሌንስኪ "በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ" እንዳለባቸው ማስጠንቀቃቸውም ተጠቅሷል።

"ከእርስዎም ሆነ ከእኛ ጋር እየተጫወቱ ነው" ሲሉ ሜርዝ መናገራቸው ተዘግቧል።

የፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስቱብ ደግሞ "ዩክሬንንና ቮሎዲሚርን ብቻቸውን ከእነዚህ ሰዎች ጋር መተው የለብንም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ቢቢሲ የተጠቀሰው የስብሰባ ቅጂ አላገኘም።