ፑቲን ከአሜሪካ ጋር በዩክሬን ጉዳይ ከተነጋገሩ በኋላ ምንም ለውጥ እንደሌለ ክሬምሊን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ተደራዳሪ ለአምስት ሰዓታት ያህል የቆየ ውይይት ካደረጉ በኋላ በዩክሬን የሰላም ስምምነት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ ተገለፀ።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ የሞስኮው ስብሰባ "ገንቢ" ቢሆንም የዕቅዱ ክፍሎች ለሩሲያ ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።
የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ያሬድ ኩሽነር፣ ከፑቲን ጋር የተገናኙት ጦርነቱን ለማስቆም ያስችላል የተባለ ለሳምንታት የቆየ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው።
የአሜሪካ ልዑካን ቡድን ሞስኮን ለቅቆ ከወጣ በኋላ የሰጠው አስተያየት የለም።
ቀደም ብሎ ማክሰኞ ዕለት ፑቲን በኪየቭ እና በአውሮፓ የሚደገፈው አሜሪካ ያቀረበችው የሰላም ረቂቅ ዕቅድ ላይ የተደረገው ለውጥ ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀዋል።
አክለውም አውሮፓ "ወደ ጦርነት መግባት ከፈለገች እና ከጀመረች አሁን ዝግጁ ነን" ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
ዩክሬን እና አጋሮቿ ዋይት ሐውስ የሰላም ዕቅዱ ላይ ማሻሻያ አንዲደረግ ግፉኢት ሲያደርጉ ነበር።
ክሬምሊን የሰላም ስምምነቱ ላይ ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት በሩሲያ ወገን ዕቅዱ ተቀባይነት አንዳለው አስታወቆ ነበር።
በኅዳር ወር ላይ ለመገናኛ ብዙኃን ሾልኮ የወጣው የሰላም ዕቅድ ለሩሲያ ያደላ አንደሆነ በሰፊው ከተነገረ በኋላ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ብዙ ለውጦች ተደርገውበታል።
ከሞስኮው ስብሰባ በኋላ ስለ ምክረ ሃሳቡ የተጠየቁት የፑቲን ከፍተኛ ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ ክሬምሊን "በአንዳንድ ነጥቦች ተስማምቷል… ግን አንዳንድ ነገሮች ላይ ያለንን ልዩነት አቅርበናል" ብለዋል። አክለውም "እስካሁን የሚያመቻምች የስምምነት አካል ይዘን አልመጣንም... ብዙ ሥራ ይጠብቃል።"
ለኪየቭ የደህንነት ዋስትና መስጠት እና ውጊያ በሚካሄድባቸው በርካታ የዩክሬን ምሥራቃዊ ክልሎች የሚደረግ ቁጥጥርን ጨምሮ ሩሲያ እና ዩክሬን አሁንም በጥልቀት የሚቃረኑባቸው አንዳንድ ጉዳዮች አልተፈቱም ተብሏል።
ሞስኮ እና ዩክሬን አጋሮች በሰላም ዕቅዱ ላይ የተለያየ አቋም ነው ያላቸው።
ዋይት ሐውስ አንጻራዊ ተስፋ አለው ቢልም፣ የአውሮፓ መሪዎች ግን ከአራት ዓመታት በኋላም የሁለቱን አገራት ጦርነት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት ስለመደረሱ ጥርጣሬ አላቸው።














