የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ለመቋጨት የሚደረገው ድርድር "ውጤታማ" ቢሆንም ተጨማሪ ስራዎች እንደሚቀሩት ተገለጸ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የዩክሬን ዋና ተደራዳሪ ሩስቴም ኡሜሮቭ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ለመቋጨት ከኪየቭ ጋር የሚደረገው ድርድር ውጤቶችን ቢያስገኝም "መከናወን ያለበት ተጨማሪ ስራ" እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተናገሩ።

በአሜሪካ ፍሎሪዳ የተካሄደው ድርድር አዲሱ የዩክሬን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የአገሪቱ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ጸኃፊ ሩስቴም ኡሜሮቭ የተገኙበት ነው።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነርም ተሳትፈዋል። ዊትኮፍ በሚቀጥለው ሳምንት ለንግግር ወደ ሞስኮ እንደሚያመሩ ይጠበቃል።

ኡሜሮቭ የዩክሬን ዋና ተደራዳሪ ሆነው የተሾሙት የቀድሞ ተደራዳሪ አንድሪ የርማክ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጸረ ሽብር ብርበራ ከተደረገ በኋላ ከኃላፊነት በመልቀቃቸው ነው።

እሁድ ዕለት ተደረገው ስብሰባ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲካሄድ ለነበረው ውጥረት የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አንድ እርምጃ ነው።

ይህ ውጥረት የተፈጠረው በአሜሪካ የተዘጋጀ ባለ 28 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ሾልኮ በመውጣቱ ነበር። የአሜሪካ ዕቅድ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ዩክሬን ላይ ወረራ ለፈጸመችው ሩሲያ የሚያደላ ሆኖ መታየቱ ዩክሬንን እና አውሮፓውያን አጋሮቿን አስደንግጧል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ ከስብሰባ በኋላ በሰጡት መግለጫ "[ድርድሩ] ውጊያን ስለሚያስቀሩት ነጥቦች ብቻ አይደለም" ብለዋል። "[ድርድሩ] ዩክሬን የረዥም ጊዜ ብልጽግና እንድታገኝ ስለሚያደርጉት ነጥቦችም ነው... ዛሬ ያንን ያደረግን ይመስለኛል፤ ግን ገና ብዙ የሚከናወን ስራ አለ" ሲሉ የድርድሩን ውጤት አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ከሩሲያ ጋር የሚደረገው የሰላም ንግግር ዓላማ ዩክሬን "ሉዓላዊ፣ ነፃ እና የበለጸገች" እንድትሆን ማድረግ እንደሆነም ለዩክሬን ልዑክ ገልጸዋል።

የእሁድ ዕለቱ ውይይት በጀመረበት ሰዓት የዩክሬኑ ተደራዳሪ ኡሜሮቭ ባደረጉት ንግግር፤ "እየተወያየን ያለው ስለ ዩክሬን የወደፊት ዕድል፣ ስለ ዩክሬን ደህንነት፣ ዩክሬን ላይ እየተደጋገመ ስላለው ወረራ፣ ስለ ዩክሬን ብልጽግና፣ ዩክሬንን እንዴት መልሶ መገንባት እንደሚቻል ነው" ብለዋል።

"አሜሪካ እያዳመጠችን ነው። አሜሪካ እየደገፈችን ነው። አሜሪካ ከጎናችን እየሰራች ነው" ሲሉም የዋሽንግተንን ድጋፍ ገልጸዋል። በኋላ ላይ ደግሞ ንግግሩ "ውጤታማ እና የተሳካ" እንደነበር ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት፤ በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች አውሮፕላን በሆነው 'ኤርፎርስ ዋን' ውስጥ ጋዜጠኞችን ያነጋገሩት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የሰላም ንግግሩ "በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ" መሆኑን ተናግረው ነበር። ጦርነቱን የሚያስቆም ስምምነት ላይ የመደረስ ጥሩ እድል እንዳለም ጠቁመዋል።

ትራምፕ፤ ማሻሻያዎች የተደረጉበትን አዲሱን የሰላም ዕቅድ በተመለከተ ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ንግግር እንዲያደርጉ በሚል መልዕክተኛቸውን ዊትኮፍን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሞስኮ እንደሚልኩ አስቀድመው ተናግረው ነበር። የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባል የሆነው ኩሽነርም አብሮ ሊጓዝ ይችላል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ውይይቶቹ ገንቢ አካሄድ እንዲኖራቸው፤ ሁሉም ጉዳዮች በግልጽ እና የዩክሬንን ሉዐላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሞች በማረጋገጥ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱን ለመቋጨት እያደረጉ ላለው ጥረትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።