ዩክሬን ጦርነቱን ለማስቆም በቀረበው የሰላም ዕቅድ ላይ ከአሜሪካ ጋር 'መግባባት' ላይ ደረሰች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገች ያለውን ጦርነትን ለማስቆም በተዘጋጀ የሰላም ስምምነት ላይ ከአሜሪካ ጋር "የጋራ መግባባት" ላይ መድረሳቸውን አስታወቀች።
ሃሳቡ የተመሠረተው ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ለኪየቭ ባቀረበችው 28 ነጥብ ዕቅድ ላይ ሲሆን የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ቅዳሜና እሁድ በጄኔቫ በተካሄደው ውይይት ላይ ተነጋግረውበታል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጡት ጽሑፍ የመጀመሪያው ዕቅድ "ከሁለቱም ወገኖች በተገኘ ተጨማሪ ግብዓት በጥሩ ሁኔታ ተስተካክሏል" ብለዋል።
ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በሚቀጥለው ሳምንት በሞስኮ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እንዲያነጋግሩ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የጦር ሠራዊት ፀሐፊ ዳን ድሪስኮል በዚህ ሳምንት የዩክሬን መሪዎችን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ማክሰኞ ዕለት ከትራምፕ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፤ አስተዳደራቸው ከወሩ መጨረሻ በፊት ስብሰባ ለማድረግ አቅዷል።
"ከአሜሪካ እና ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የበለጠ ንቁ ትብብር አደርጋለሁ የሚል እምነት አለኝ። አብዛኛው በአሜሪካ ላይ የተመሰረተ ነው፣ ምክንያቱም ሩሲያ ለአሜሪካ ጥንካሬ ከፍተኛ ትኩረት ትሰጣለች" ብለዋል።
ከአንድ ቀን በፊት፣ ዜሌንስኪ የ28 ነጥብ ዕቅዱ ለዝቧል፤ አንዳንድ ድንጋጌዎችም ተወግደዋል ብለዋል።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከዜሌንስኪ እና ከፑቲን ጋር ለመገናኘት በጉጉት እንደሚጠባበቁ እና ይህ የሚሆነው ግን " ይህንን ጦርነት ለማስቆም የተደረገው ስምምነት ሲጠናቀቅ ወይም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻ" እንደሆነ ጽፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ስምምነቱ "በሁለቱም በኩል" የግዛት ስምምነቶችን እና "ድንበሩን ነጻ ለማድረግ መሞከርን" ያካትታል።
ትራምፕ "ለእኔ የጊዜ ገደቡ [ጦርነቱ] ሲያበቃ ነው" በማለት ለሁለቱም ወገኖች የመጨረሻ የሚሉትን ቀን እንዳልሰጡ ተናግረዋል።
ሩሲያ በአዲሱ ረቂቅ ስምምነት ላይ ማንም እንዳላማከራት በመግለጽ በዕቅዱ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ላትቀበል እንደምትችል አስጠንቅቃለች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሞስኮ የመጀመሪያውን የአሜሪካ ማዕቀፍ ብትደግፍም፣ ዕቅዱ ጉልህ ለውጥ ከተደረገበት ሁኔታው "በመሠረቱ የተለየ" እንደሚሆን ተናግረዋል።
እስከ ማክሰኞ ጠዋት ድረስ ክሬምሊን የአዲሱን ዕቅድ ቅጂ እንዳልደረሰው ላቭሮቭ ተናግረዋል። አውሮፓ የአሜሪካን የሰላም ጥረቶች እያዳከመች ነው ሲሉም ከስሰዋል።
ድራይስኮል እና የሩሲያ ተወካዮች ሰኞ እና ማክሰኞ በአቡ ዳቢ ስብሰባ ቢያደርጉም የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሩሲያን ስጋቶች በይፋ አላነሱም።
ለኪየቭ የደህንነት ዋስትና መስጠት እና ውጊያ በሚካሄድባቸው በርካታ የዩክሬን ምሥራቃዊ ክልሎች የሚደረግ ቁጥጥርን ጨምሮ ሩሲያ እና ዩክሬን አሁንም በጥልቀት የሚቃረኑባቸው አንዳንድ ጉዳዮች አልተፈቱም ተብሏል።
ዋይት ሐውስ አንጻራዊ ተስፋ አለው ቢልም፣ የአውሮፓ መሪዎች ግን ከአራት ዓመታት በኋላም የሁለቱን አገራት ጦርነት የሚያስቆም የሰላም ስምምነት ስለመደረሱ ጥርጣሬ አላቸው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ሩስያ ተኩስ ለማቆም ፍላጎት የላትም" ሲሉ የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ "ረዥም መንገድ ይቀራል እና ከፊት ያለው መንገድ ደግሞ አስቸጋሪ ነው" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ማክሮን እና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በአውሮፓ የዩክሬን አጋሮች ቡድን ስብሰባን መርተዋል።
በዚህ ጥሪ ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም ተቀላቅለው፤ መሪዎቹ ለዩክሬን ሊሰጡ በሚችሉ የደህንነት ዋስትናዎች ላይ ስራውን "ለማፋጠን" ከአሜሪካ ጋር ግብረ ኃይል ለማቋቋም ተስማምተዋል።
የደህንነት ዋስትናዎች ጉዳይ ሞስኮ እና ኪየቭ ከሚጋጩባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ብቻ ነው።
ሰኞ ዕለት ዜሌንስኪ ሰላምን የሚያደናቅፈው "ዋናው ችግር" ፑቲን በኃይል የያዙትን ግዛት ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ያቀረቡት ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።















