የትራምፕ አስተዳደር አውሮፓ "የሥልጣኔ መጥፋት" ተጋርጦባታል አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አውሮፓ "የሥልጣኔ መጥፋት" እንደሚጠብቃት አዲስ ባወጣው የስትራቴጂ ሰነድ አስጠነቀቀ።
ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ሰነድ፤ አንዳንድ አገሮች አስተማማኝ አጋር ሆነው ስለመቀጠላቸው ያለውን ጥርጣሬም ገልጿል። አዲሱ የስትራቴጂ ሰነድ አውሮፓን ትኩረት ሰጥቶ ተመልክቷታል።
ባለ 33 ገፁ የብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለዓለም ያላቸውን ራዕይ እና እንዴት የአሜሪካን ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኃይል ተጠቅመው ይህንን ለማስፈጸም እንደሚሰሩ ይተነትናል።
ትራምፕ ሰነዱን አሜሪካ "በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታላቅ እና ስኬታማ አገር" ሆና እንድትቀጥል የሚያደርግ "ፍኖተ ካርታ" ሲሉ ገልጸውታል።
ሰነዱን በሚመለከት የአውሮፓ ፖለቲከኞች ምላሽ የሰጡ ሲሆን የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆአን ዋዴፑል አገራቸው "ከውጭ የሚመጣ ምክር" እንደማያስፈልጋት ተናግረዋል።
የአሜሪካ መደበኛ የብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ በፕሬዝዳንቶቹ በእያንዳንዱ የሥልጣን ዘመን አንድ ጊዜ ይፋ ይደረጋል።
ሰነዱ ለወደፊት ፖሊሲዎች እና በጀቶች ማዕቀፍ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያሳይ ነው።
አዲሱ ሰነድ ትራምፕ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካደረጉት ንግግር ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው የምዕራብ አውሮፓ አገራት በስደት እና በንፁህ ኢነርጂ አቅርቦት ላይ በሚከተሉት ፖሊሲ በመጥቀስ ከባድ ትችት ሰንዝረዋል።
አዲሱ ሰነድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም የያዙትን አቋም የሚያጠናክር ሲሆን "የምዕራባውያን ማንነት እንዲታደስ" ጥሪ ያቀርባል።
የውጭ ተጽዕኖን ለመዋጋት፣ የጅምላ ስደትን ለማስቆም እና አሜሪካ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው አንዱ የሆነውን የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ለመግታት የሚሰሩ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጓል።
በአውሮፓ ላይ በማተኮርም አሁን ያለው አዝማሚያ ከቀጠለ አህጉሪቱ "በ20 ዓመታት ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ የማትታወቅ" እንደምትሆን ይጠቅሳል። የአውሮፓ "ሥልጣኔ" ላይ የተጋረጠው "የመጥፋት" አደጋ የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ካስከተሉት ችግር ይልቅ "እውነተኛ እና ይበልጥ ግልጽ" ሆኖ እንደሚታይም ያብራራል።
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቿ "በእውነተኛው እና በይበልጥ ግልጽ በሆነው የሥልጣኔ መጥፋት የተጋረጠበት" መሆኑን ይዘረዝራል።
ሰነዱ "የተወሰኑ የአውሮፓ አገራት አስተማማኝ አጋር ሆነው ለመቀጠል የሚያስችል አስተማማኝ ኢኮኖሚ እና ወታደራዊ ኃይል ይኖራቸው እንደሆነ ግልፅ አይደለም" ይላል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት እና "ሌሎች የሽግግር አካላት" ያላቸውን አካላት "የፖለቲካ ነፃነትን እና ሉዓላዊነትን የሚያንኳስሱ" ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነ በማንሳት ከስሷል።
አክሎም የስደት ፖሊሲዎች "ምሬትን እየፈጠሩ ነው" ያለው ሰነዱ "የመናገር ነፃነትን ይገደባል፤ እንዲሁም የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ይታፈናሉ" ሲል ይዘረዝራል።
ከዚህም በተጨማሪም "የልደት መጠን መወሰን፣ ብሄራዊ ማንነትን ማጣት እና በራስ መተማመን" በሰነዱ ላይ የአውሮፓ ኅብረትን በሚመለከት ከሰፈሩት መካከል ይገኙበታል።
በአንጻሩ ሰነዱ እያደገ የመጣውን "የአውሮፓ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ፓርቲዎች" ተጽዕኖን የሚያወድስ ሲሆን "አሜሪካ የአውሮፓ አጋሮቿ ይህን የመንፈስ መነቃቃትን እንዲያበረታቱ ታበረታታለች" ብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር በጀርመን ደህንነት ተቋማት ዋልታ ረገጥ ተብሎ ከተፈረጀው አክራሪ የቀኝ ዘመም ፓርቲ ኤኤፍዲ ጋር ግንኙነት ፈጥሯል።
የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋዴፑል "ዩናይትድ ስቴትስ በኔቶ ጥምረት ውስጥ በጣም አስፈላጊ አጋር ናት እና ሆናም ትቀጥላለች። ይህ ጥምረት ግን የደህንነት ፖሊሲ ጉዳዮችን ለመፍታት ያተኮረ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ወይም ነፃ ማኅበረሰቦቻችን የማደራጀት ጥያቄዎች በምንም መልኩ ቢሆን ቢያንስ በጀርመን [በስትራቴጂው] ውስጥ አይገቡም ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ አስመልክቶ ሰነዱ አውሮፓ ከሩሲያ ጋር ባለው ግንኙነት "በራስ መተማመን" እንደሌላት ገልጿል።
ሰነዱ የአውሮፓ እና ሩሲያ ግንኙነት በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ የአሜሪካ ተሳትፎ ይጠበቃል ካለ በኋላ በዩክሬን ውስጥ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ የአሜሪካ ዋና ፍላጎት መሆኑን ጠቅሷል።















