የኔቶ አገራት ከሩሲያ ነዳጅ መግዛት ካቆሙ ትራምፕ ሞስኮ ላይ ማዕቀብ ለመጣል "ዝግጁ" መሆናቸውን ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት የሩሲያን ነዳጅ መግዛት ማቆምን ጨምሮ የተወሰኑ መስፈርቶችን ካሟሉ ብቻ ሞስኮ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ለመጣል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ትሩዝ በተባለው ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባጋሩት ጽሑፍ የኔቶ አባል አገራት "ተስማምተው ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ" በሩሲያ ላይ ትልቅ ማዕቀብ ለመጣል ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ትራምፕ በሞስኮ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጥሉ በተደጋጋሚ የዛቱ ሲሆን፤ ክሬምሊን የሚያስቀምጡትን የድርድር ቀነ ገደብ እና የማዕቀብ ዛቻ ወደ ጎን ቢልም እስካሁን ግን የወሰዱት እርምጃ የለም።

የሩሲያን የነዳጅ ሽያጭ "አስደንጋጭ" ሲሉ የገለፁት ትራምፕ፤ የአገሪቱን "ጠንካራ ቁጥጥር ለማዳከም" የኔቶ አባል አገራት ቻይና ላይ ከ50 እስከ 100 በመቶ የሚሆን ታሪፍ እንዲጥሉ ሀሳብ አቅርበዋል።

ለኔቶ አባላት ደብዳቤ ባሉት ጽሑፍ ትራምፕ "እናንተ ዝግጁ ስትሆኑ፤ እኔ ዝግጁ ነኝ። ቀኑን ብቻ አሳውቁኝ" ብለዋል።

ትራምፕ አክለውም "በአንዳንዶች እየተፈፀመ ያለው የነዳጅ ግዢ አስደንጋጭ ነው።ሩሲያ ላይ የድርድር አቋማችሁን እና የመደራደሪያ ኃይላችሁን በእጅጉ አዳክሞታል" ሲሉም ተችተዋል።

የሩሲያን አቅም ለማዳከም የነዳጅ ግዥን ማቆም፤ቻይና ላይ ከሚጣል ታሪፍ ጋር ተዳምሮ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም "በእጅጉ ይረዳል" ብለዋል።

ሩሲያ ላይ ጥገኛ የነበረው የአውሮፓ የኃይል ግዢ ሞስኮ ዩክሬን ላይ ሙሉ ለሙሉ ወረራ መጀመሯን ተከትሎ ግን አሽቆልቁሏል።

እ.አ.አ በ2022 የአውሮፓ ኅብረት 45 በመቶ ጋዝ ከሩሲያ ያገኝ ነበር። በዚህ ዓመት ይህ አሃዝ ወደ 13 በመቶ ዝቅ እንደሚል ቢጠበቅም የትራምፕ አገላለፅ ግን አሃዙ በቂ እንዳልሆነ ነው።

የትራምፕ መልዕክት ባለፈው ረቡዕ በርካታ ድሮኖች የፖላንድን አየር ክልል ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ በኔቶአባል አገራት እና በሩሲያ መካከል ውጥረት በጨመረበት ወቅት የመጣ ነው።

ፖላንድ የድሮን ወረራው ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ያለች ሲሆን፤ ሞስኮ ግን ሁነቱን በማጣጣል በአገሪቱ ተቋማትን ዒላማ ለማድረግ እቅድ የለኝም ብላለች።

ዴንማርክ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ በምሥራቃዊ ቀጠና ትብብርን ለማሳደግ አዲስ የኔቶ ተልዕኮን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ወደ ቀጠናው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪም የአውሮፓ አገራት የሩሲያን ነዳጅ እና ጋዝ ግዢን በሚመለከት ጥሪ አቅርበዋል።

ከኤቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ከሩሲያ የትኛውንም ዓይነት ኃይል [መግዛት] ማቆም አለብን። [ሞስኮን] ለማስቆም የምንፈልግ ከሆነ ምንም ስምምነት ማድረግ የለብንም" ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ2022 ጀምሮ የአውሮፓ አገራት ለሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ 210 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ አድርገዋል።አብዛኛው ይህ ገንዘብ የዩክሬንን ወረራ ለመደጎም ውሏል የሚል እምነት አለ።

የአውሮፓ ኅብረት ከዚህ ቀደም ከሩሲያ የሚገዛውን ኃይል እስከ 2028 ድረስ ቀስ በቀስ ለማስቆም ዕቅድ ነድፎ ነበር።

አሜሪካ ይህ ውጥን በአፋጣኝ እንዲፈፀም ፍላጎት ያላት ሲሆን በምትኩ ከፊሉን የኃይል አቅርቦት ከዋሽንግተን እንዲገዙ ሀሳብ አቅርባለች።