ፕሬዝዳንት ፑቲን ምዕራባውያን ወታደሮች ዩክሬን ውስጥ የሚሰማሩ ከሆነ ዒላማ እንደሚሆኑ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, VLADIMIR SMIRNOV/TASS/HANDOUT
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን በፓሪስ ባካሄዱት ጉባዔ በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ "የደኅንነት መተማመኛ ኃይል" በማለት ወታደሮች ለማሰማራት ያቀረቡትን ምክረ ሃሳብ ውድቅ አደረጉ።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮን 26 የዩክሬን አጋር አገራት ጦርነቱ ከቆመ በኋላ የአገሪቱን ፀጥታ ለማረጋገጥ "በምድር፣በባሕር ወይም በአየር" ጦራቸውን ለማሰማራት በይፋ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
ማክሮን የትኞቹ አገራት ወታደሮቻቸውን ለማዋጣት ቃል እንደገቡ በዝርዝር አልተናገሩም።
ፑቲን የዩክሬን አጋሮች ገቡት የተባለውን ቃል ውድቅ በማድረግ ማንኛውም ዩክሬን ውስጥ የሚሰማራ ወታደር "ዒላማ" ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ምንም እንኳ ወታደሮቹን አሁን የማሰማራት ፍላጎት ባይኖርም፣ ይህ የሚሆን ከሆነ ግን ዒላማ ከመሆን እንደማያመልጡ ዝተዋል።
በዩክሬን እና በሩሲያ ጦር መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረሳል የሚለው ተስፋ እጅጉን የተመናመነ ነው።
ባለፈው ወር ፑቲን በአላስካ ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ከተገናኙ በኋላ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን አግኝተው የሰላም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል ተስፋ አጭሮ ነበር።
ፑቲን አርብ ዕለት የዩክሬኑን መሪ ለማግኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው፣ "ነገር ግን አስፈላጊነቱ አይታየኝም። ለምን? ምክንያቱም በቁልፍ ጉዳዩች ላይ በዩክሬን በኩል ከስምምነት ላይ ለመድረስ እጅጉን አዳጋች ነው" ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ትራምፕ መፍትሄ ለመፈለግ ያደረጉትን ጥረት "በጣም ገንቢ" ነው በማለት ካደነቁ በኋላ ነገር ግን "የአውሮፓ አገራት አሳፋሪ ጥረት ጦርነቱ እንዲቀጥል ያደርጓል" ብለዋል።
ከአላስካው ስብሰባ ጀምሮ "የፈቃደኞች ጥምረት" እየተባለ የሚጠራው እና በዩናይትድ ኪንግድም እና በፈረንሳይ የሚመራው ቡድን የሰላም ስምምነት ላይ ከተደረሰ ለኪየቭ መተማማኛ ለመስጠት ያለመታከት እየሠሩ ቆይተዋል።
ይህ መተማመኛ የዩክሬንን ጦር ማጠናከር እንዲሁም ስምምነቱን ለመቃኘት "የመተማመኛ ኃይል" መመደብ ይገኙበታል።
ማክሮን የትኛውም ሠራዊት የሚላከው "ማንኛውንም አዲስ ጥቃት ለመከላከል እንጂ በግንባር ላይ ተሰማርቶ እንዲዋጋ አለመሆኑን" ተናግረዋል።
ጦሩ "ሩሲያ ላይ ጦር የማወጅ ዓላማ ወይም ፍላጎት የለውም" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ሐሙስ ዕለት በፓሪስ የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ የተላለፈውን ውሳኔ አንድ ተጨባጭ የሆነ እርምጃ ሲሉ አሞካሽተዋል።
አሜሪካ በዚህ ውሳኔ ላይ የሚኖራት ተሳትፎ ምን ያህል እንደሆነ አልተናገረችም።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ በቅርቡ አሜሪካ "ምናልባት" የአየር ኃይል ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ጠቁመው ነበር።
ዜሌንስኪ የአሜሪካ ፕሬዝዳንትን "የዩክሬን ሰማይ ከፍተኛውን ከለላ" በሚያገኝበት መንገድ ላይ ማነጋገራቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ከፑቲን ጋር "በጣም ጥሩ ውይይት" ማድረጋቸውን ገልፀው፣ በቅርቡ ዳግም ለመነጋገር ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።
ፑቲን አርብ ዕለት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር "ግልጽ ውይይት" ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።
ዩክሬን ምንም እንኳን ሩሲያ ባትስማማም ሰፋ ያለ የሰላም ስምምነት ላይ ከመድረሱ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት መደረግ እንዳለበት ታምናለች።
በሩሲያ በተካሄደ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ፑቲን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ወደ ዘላቂ ሰላም የሚመራ ውሳኔዎች ላይ ከተደረሰ...የውጭ ወታደሮች መግባት ፋይዳው አይታየኝም" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም ሩሲያ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚያመራ ማንኛውንም ውሳኔ "በሙሉ" ታከብራለች ብለዋል።
ፑቲን በሞስኮ ከዩክሬን ጋር የመሪዎች ጉባኤ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን እና የፀጥታ ጥበቃን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ በበኩላቸው ፑቲን በጉዳዩ ላይ ኮስተር ያለ አቋም የላቸውም ሲሉ ተሳልቀዋል። በምትኩ በርካታ ገለልተኛ ዋና ከተማዎች ቢጠቁሙም ፑቲን ግን "የበዛ ፍላጎት" በማለት ቅሬታ አቅርበዋል።
ዜሌንስኪ አክለውም "በማንኛውም ዓይነት መንገድ፣ የሁለትዮሽ፣ የሦስትዮሽ ስብሰባ በማድረግ እንስማማለን፤ ሩሲያ እሱን ለማዘግየት ሁሉንም ነገር እንደምታደርግ አምናለሁ" ብለዋል።
የምዕራባውያን መሪዎችም ሩሲያ ለ40 ወራት የዘለቀው ጦርነት እየተፋፋመ በመምጣቱ ተጨማሪ የዩክሬን ግዛትን ለመያዝ ጊዜ እየገዛች ነው ብለው ያምናሉ።
ረቡዕ ዕለት ከቻይናው ዢ ጂንፒንግ እና ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ያሳለፉት ፑቲን የአገራቸው ጦር በዩክሬን በሁሉም ግንባር ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑን አረጋግጠዋል።















