ታዋቂው የዩክሬን ፓርላማ አባል እቃ አድራሽ መስሎ በቀረበ ሰው ተገደሉ

ፖለቲከኛው አንድሪ ፓሩቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዋቂው የዩክሬን ፖለቲከኛ አንድሪ ፓሩቢ ላይ ግድያ እንደፈጸመ የተጠረጠረ ግለብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አስታወቁ።

የ54 ዓመቱ የፓርላማ አባል ቅዳሜ ዕለት በምዕራባዊው ሉቪቭ ከተማ ውስጥ እቃ አድራሽ መስሎ የቀረበ ግለሰብ በፈጸመው ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ ተጠርጣሪውን ለመያዝ አደን ሲካሄድ ቆይቷል።

የዩክሬን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢጎር ክሊሜንኮ ሰኞ ጠዋት በሰጡት መግለጫ፤ ተጠርጣሪው በምዕራባዊው ክሜልኒትስኪ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

የፓርላማ አባሉ ፓሩቢ፤ ዩክሬን ከአውሮፓ ህብረት ጋር የጠበቀ ትስስር እንዲኖራት ሲጠየቅ በነበረበት እና የሩስያ ደጋፊ የሆኑት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች በ2014 ከስልጣን እንዲወርዱ ባደረገው 'ዩሮሜዳን' ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ታዋቂነትን ያገኙ ፖለቲከኛ ናቸው።

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የፖሊስ ቅድመ ምርመራው ግድያው "በጥንቃቄ የተዘጋጀ" እንደሆነ አሳይቷል።

የፖለቲከኛውን ፓሩቢ የጉዞ መርሃ ግብር፣ የሚጓዙበትን መንገድ እንዲሁም የማምለጫ እቅድ ጭምር ያካተተ እቅድ መገኘቱንም ተናግረዋል።

የዩክሬን ብሔራዊ ፖሊስ ኃይል ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች ይፋ እንደሚያደርግም አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ከሀገሪቱ ዋና ዐቃቤ ህግ ጋር መነጋገራቸውን እንዲሁም ተጠርጣሪው የመጀመሪያ የምስክርነት ቃሉን እንዲሰጥ መደረጉ እንደተገለጸላቸው አስታውቀዋል።

"በአሁኑ ሰዓት ይህ ግድያ የተፈጸመባቸውን ሁኔታዎች በሙሉ ለማረጋገጥ አስቸኳይ የምርመራ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው" ብለዋል። አክለውም የህግ አስከባሪዎችን እና ዐቃቢያነ ህግ ያለ እረፍት መስራታቸውን በመጥቀስ አመስግነዋል።

ተኩሱ ከተፈፀመበት ቦታ የተወሰደ ነው የተባለ አንድ ያልተረጋገጠ ቪድዮ፤ አንድ ሰው እንደ እቃ አድራሽ ሠራተኛ ለብሶ እና መሳሪያ ይዞ መንገድ ላይ ከበስተጀርባ ወደ ፓሩቢይ ሲቀርብ እንዲሁም መሳሪያውን ከፍ ሲያደርግ አሳይቷል።

የሉቪቭ ፖሊስ አዛዥ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥቃት ፈጻሚው በያዘው "ጦር መሣሪያ ስምንት ጥይቶች ገደማ መተኮሱን" ተናግረዋል።

በዩክሬን የህግ አስከባሪ ተቋማት ውስጥ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የጥቃት ፈጻሚው አለባበስ ግሎቮ የተሰኘውን የእቃ አድራሽ (ዴሊቨሪ) ኩባንያ ሠራተኛ ይመስል ነበር።

ኩባንያው በበኩሉ በተፈጸመው ወንጀል "እጅግ መደናገጡን" እና ምርመራው ላይ ሙሉ በሙሉ እንደሚተባበር ገልጿል።

ፓሩቢ ከሚያዝያ 2016 እስከ ነሐሴ 2019 ድረስ የሀገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ነበሩ።

ፖለቲከኛው፤ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የጠበቀ ትስስር እንዲኖር በመጠየቅ ከ2013 እስከ 2014 የተካሄዱት ሰልፎች መሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

በተቃውሞው ወቅት በዋና ከተማዋ ኪየቭ መሃል ተዘርግቶ የነበረውን የሰልፈኞች የድንኳን ካምፕ የሚጠብቁትን "ሰልፍ ዲፌንስ" የተባሉ ቡድኖችን በማደራጀት ባደረጉት እንቅስቃሴም ይታወቃሉ።